BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ምርጫ፡ የትግራይ ክልል የምርጫ ሥርዓት ለውጥና አንድምታው

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የምርጫ ሥርዓት ለውጥና እንዳደረገና በክልሉ ምክር ቤት ውስጥ ያለው የመቀመጫ ብዛት ላይ 38 በመጨመር ወደ 190 ከፍ እንዲል አድርጓል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት በመቀየር በ"ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት" እንዲተካ በማድረግ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

በዚህም በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ መቀመጫዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ የአብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት የሚያዝ ሲሆን፤ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ለተወዳዳሪ ድርጅቶች እንደሚከፋፈል ተገልጿል።

በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?

በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክንፈ ሃዱሽ ከመጀመሪያ ጀምሮ የምርጫ ሥርዓቱ መቀየር አለበት የሚል አቋም እንደነበራቸውና "ተመጣጣኝ ውክልና" እንዲኖር ሃሳብ አቅርበው እንደነበር ያስታውሳሉ።

"ይሁን እንጂ ዛሬ ምክር ቤቱ ያፀደቀው በገዢው ፓርቲ የቀረበውን 'ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት' ነው" ይላሉ። እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ያቀረቡት ሃሳብም በአዋጁ እንዳልተካተተ ይናገራሉ።

ይህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ምክር ቤት የሚገቡበትን እድል የሚያጠብና የገዢው ፓርቲ እድል የሚያሰፋ ነው ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

አቶ ክንፈ 38 ወንበር ለሚኖረው 20 በመቶ ውክልናም ገዥው ፓርቲ ስለሚወዳደር በምክር ቤቱ የፀደቀው ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት አካታች እንዳልሆነ እንደሚያስቡ ይናገራሉ።

"በዚህ የምርጫ ሥርዓትም ተጠቃሚ የሚሆነው ገዢው ፓርቲ ነው። እኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ገዥው ፓርቲ የተደራጀ መዋቅር የለንም። የመንግሥት ሃብት የምንጠቀምበት እድል የለም" ሲሉ ምክር ቤቱ በገዥው ፓርቲ በኩል የሚቀርቡ ሃሳቦችን እንደሚያፀድቀው የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

ክልሉ አካሂደዋለሁ ያለው ምርጫውም ፍትሃዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የምርጫ ሕጉ አካታች መሆንና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በመሰረታዊ ጉዳይ የተስማሙበት መሆን ቢኖርበትም የምርጫ ሕጉ ግን ይህንን ባካተተ መልኩ አይደለም የተዘጋጀው ይላሉ።

ከዚህም ባሻገር "ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ተቋማት መኖር አለባቸው" የሚሉት አቶ ክንፈ፤ እስካሁን ባለው ሂደት እነዚህ አካላት ነፃ ናቸው ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ።

የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶሪ አስገዶም ግን ከዚህ የተለየ ሃሳብ ነው ያላቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በክልሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ሕጉ መለወጡና ቁጥሩ ከፍ ማለቱ እነርሱን ለማካተት ይጠቅማል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የትግራይን ምክር ቤት ወንበር ሙሉ በሙሉ የያዘው ገዥው ፓርቲ መሆኑን የገለፁት አቶ ዶሪ፤ አሁን ግን በምርጫው ያሸነፈው ፓርቲ አብላጫ መቀመጫ እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል። ወደፊት ይህ ቁጥር መሻሻል እንዳለበት አቶ ዶሪ ሃሳብ ሰጥተዋል።

የክልሉ እርምጃ በሕገ መንግሥት ባለሙያ ዕይታ

በሕገ መንግሥት ላይ ጥናት የሰሩት አደም ካሴ (ዶ/ር) በክልሉ በተሻሻለው የምርጫ ሥርዓትና የምክር ቤት መቀመጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወሰነ ቦታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ይላሉ።

ነገር ግን የሚያሸንፈው ፓርቲ ከ20 በመቶውም መቀመጫ ስለሚወስድ ለተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ።

የምርጫ ሕግን የማውጣት ሥልጣን የፌደራል መንግሥት ነው የሚሉት አደም (ዶ/ር) ያለ ፌደራል መንግሥቱ እውቅና ይህንን መቀየር ሥልጣን አላቸው ወይ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን ያነሳሉ።

"ሕገ መንግሥቱ የምርጫ ሥርዓቱ በአብላጫ ድምፅ የተመሰረተ የሚያደርገው የፌደራል ፓርላማውን ብቻ ነው፤ የክልሎቹን በምርጫው ሕግ እንዲወጣ ነው የሚለው፤ በመሆኑም እንደ ክልል ይህንን ሕግ ማውጣት ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይፃረራል" ይላሉ።

ይሁን እንጂ ክልሎች ይህ ሥልጣን ቢሰጣቸው እንደ ራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ እንዲያካሂዱና በምክር ቤቱም የተለያዩ አካላትን ማካተት እንደሚያስችል ሃሳብ ይሰጣሉ።

ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም "ለፌደራል ያለው የምርጫ ሥርዓትና ግብዓቶች በክልል ካሉት ጋር አንድ አይነት አይደለም" ይላሉ።

በቅርቡ ምርጫውን ለማራዘም የወጣው የሕገ መንግሥት ትርጓሜም የምርጫ ሕግን የማውጣት ሥልጣን የፌደራል መሆኑን ይጠቅሳል ያሉት አደም (ዶ/ር)፤ በመሆኑም ክልሎች ይህን የማድረግ ሥልጣን ቢኖራቸው ክልሉ ያደረገው ጥሩ ጅማሮ ይሆን ነበር ብለዋል።

"በ2007 አገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ መቀመጫ አግኝቷል። ይህ ማለት ግን መቶ በመቶ የሕዝብ ድምፅ አግኝቷል ማለት አይደለም። ከ30 በመቶ በላይ ያለውን ድምፅ የተለያዩ ተቃዋሚዎች ናቸው ያገኙት፤ ነገር ግን አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ መቀመጫ አላገኘም" በማለት የሚያስታውሱት አደም (ዶ/ር)፤ የምርጫ ሥርዓት ለውጥ መኖሩ አንድ ፓርቲ በምክር ቤት ያለው መቀመጫና በሕዝቡ ውስጥ ያለው ድጋፍ የማይመጣጠን እንዳይሆን ያደርጋል ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደምም ወደዚህ ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ጥያቄዎች እንደነበሩ አቶ አደም (ዶ/ር) አስታውሰዋል።

Report Page