BBC

BBC


በትግራይ ክልል ማይጸብሪ የሚገኙ 24 ሺህ ገደማ ኤርትራዊያን ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ስደተኞቹን የተሻለ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ለማዘዋወር የአደጋ ግዜ እቅድ ማዘጋጀቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

በማይጸብሪ በሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ እየተገነባ ወደሚገኘው አዲስ ጣቢያ እንደሚዘዋወሩ ተቋሙ ገልጿል።

ይህ በ91 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው የመጠለያ ካምፕ 25 ሺህ ስደተኞችን ለማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውም ታውቋል።

እስከ አሁን ድረስ 98 ስደተኞች አዲሱ መጠለያ ወደሚገነባበት አካባቢ የተወሰዱ ሲሆን፤ የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች እየቀረቡላቸው እንደሆነ የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ነቨን ከርቨንኮቪክ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ የዚህን አዲስ የስደተኞች ካምፕ ግንባታ ከጥቂት አጋሮች ጋር በመሆን መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

"ስደተኞቹ ከፊታቸው የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል"

ከሳምንታት በፊት ኤርትራውያን ስደተኞች እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ እና ለወደፊቱም የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው በመገልጽ መብታቸው እንዲከበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ አበባ ውስጥ መካሄዱ አይዘነጋም።

በሌላ በኩል የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በማይጸብሪ ባሉት ሁለት ካምፖች የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች ያሉበት ሁኔታ «እገታ» ነው ሲል ነበር የገለጸው።

ይህንን አገላለጽ ጠቅሰን ስለ ስደተኞቹ ደኅንነት የጠየቅናቸው የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ስደተኞቹ "የሰብዓዊ እርዳታ ተቋርጦባቸው በማያቋርጥ ፍርሃት ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ቢያንስ አንድ ስደተኛ በካምፑ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መገደሉን የሚያረጋግጥ የሚረብሽ እና ታማኝ ዘገባ ከማይ አይኒ ካምፕ ደርሶናል። ይህ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ሲሆን፤ ሐምሌ 14 ሌላ ስደተኛ መገደሉን የሚያመላክት ሌላ ሪፖርት ደርሶን ነበር" ብለዋል።

የድርጅቱ ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ሳምንታት ከስደተኞች መጠለያ ካምፖች ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን አስረድተው "ወጥመድ ውስጥ የገቡ ስደተኞች አስቸኳይ የሕይወት አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል" በማለት ስለ ስደተኞቹ ገልጸዋል።

በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያለቀ እንደሆነና እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ የጤና አገልግሎቶች እየተሰጡ እንደሆነም ተናግረዋል።

"ስደተኞቹ ከፊታቸው የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል" የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ በሁለቱም ካምፖች የመጨረሻው የምግብ አቅርቦት የደረሰው በሰኔ ወር መጨረሻ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህም ስደተኞቹን ከአንድ ወር በላይ እንደማያቆያቸው አክለዋል።

ወደ 24,000 የሚሆኑ ኤርትራዊያን ስደተኞች ማስፈራራት እና እንግልት እየገጠማቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግሥት ኤርትራውያን ስደተኞች እንግልት እና ማስፈራራት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው አስታውቆ፤ የስደተኞቹ መብት እንዲከበር ማሳሰቡ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በበኩሉ፤ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች የስደተኞች ካምፖች ሊከበርላቸው የሚገባውን የሲቪል ደንብ እንዲከተሉ ጠይቋል።

በተጨማሪም "የስደተኞች እና የሁሉም ሲቪሎች ከጦርነት የመጠበቅ መብትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሕግ ግዴታቸውን እንዲጠብቁ እንማጸናለን" ሲሉ የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ነቨን ከርቨንኮቪክ ለቢቢሲ ገልጸዋል።።

ስለ አዲሱ መጠለያ ጣቢያ

የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ አሁን ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር እነሱም ይሁን አጋሮቻቸው በአሁኑ ወቅት ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ ለመድረስ አልቻሉም።

የደኅንነት ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ግን ስደተኞችን ከአካባቢው ለማስወጣት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች ማስቀመጣቸውን አስረድተዋል።

"የጸጥታ ሁኔታው እስከሚሻሻል ድረስ ስደተኞቹ ከሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች በሰላም ስለሚወጡበት ሁኔታ ሁሉንም ወገኖች ለማሳመን እየሠራን እንገኛለን" ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሁለት ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነና የመጀመሪያው ስደተኞቹን ከአደጋ ቀጠና በማውጣት በግዜያዊነት በዳባት ከተማ ወደተለዩት መጠለያዎች ማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል።

በሕብረተሰቡ ትብብር የጋራ ማረፊያዎችን የመለየት ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ የትራንስፖርት፣ የውሃ፤ የኤሌክትሪክ፣ የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም የምግብ አቅርቦት የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን አክለዋል።

ቀሪ ወሳኝ ቁሳቁሶች ከአዲስ አበባ ወደ ቦታው እየተጓጓዙም ይገኛሉ።

ሌላው የአደጋ ግዜ ምላሽ የሚሰጡ ባለሙያዎችን ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን በመሬት ላይ ያለውን የሰው ኃይል የማጠናከር ሥራ ነው።

"በዳባት (አለማዋጭ) የሚገነባው አዲሱ መጠለያ ወደ ሥራ ሲገባ በርካታ ችግሮችን የሚያቃልል እና በማይ አይኒ እንዲሁም በአዲ ሃሩሽ ያሉ ስደተኞችን ሙሉ በሙሉ የመያዝ አቅም ይኖረዋል" ብለዋል የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ነቨን ከርቨንኮቪክ።

(BBC)


Report Page