BBC

BBC


የሚዲያ ሰራተኞች አዋሽ 7 ነው የሚገኙት ተባለ።

አካልን ነፃ የማውጣት ማመልከቻ አስገብተው የነበሩት 14 የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች ወደ አዋሽ 7 መዘዋወራቸውን ፖሊስ ፍርድ ቤት አሳወቀ።

ፖሊስ ለልደታ ዘጠነኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት ትላንት በጽሁፍ ባቀረበው ምላሽ ተጠርጣሪዎቹ በቦታ ጥበት ምክንያት አፋር ክልል፣ ፈንታሌ ወረዳ አዋሽ ሰባት ኪሎ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ወስጃቸዋለሁ ብሏል።

ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበ አቤቱታ እስከ ሐምሌ 26 ድረስ ለምርመራ ጊዜ መፈቀዱን ፖሊስ አክሏል።

ለችሎቱ በማስረጃነት የተያያዘው ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረበው የፖሊስ ማመልከቻ እንደሚያመለክተው ጋዜጠኞቹ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ "በማኅበራዊ ድረ ገጽ፤ ማለትም በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቴሌግራም እና ዋትስአፕን በመጠቀም በውጭ አገር ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፤ ሕብረተሰቡ ላይ ጫና ለመፍጠር፤ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጋጩ፣ ሕዝቡ ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሰራ፤ ጦርነት ቀስቃሽ መልዕክቶችን አሰራጭተዋል" የሚሉትን ጨምሮ በተመሳሳይ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል ለፈንታሌ ወረዳ ችሎት አመልክቷል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን በመጣስ ብሎም ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የሚያስረዳው ክሱ እነዚህን ወንጀሎች ለመመርመር ጊዜ ይሰጠኝ ሲል አመልክቶ ነበር።

ሐምሌ 12 ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል የጠየቀው ፖሊስ በተሰጠኝ ጊዜ ውስጥ አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት ዘርዝሮ ለችሎቱ አቀርቧል።

በዚህም ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ማናገር፣ የምስክርነት ቃል መቀበል፣ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ማስረጃ መሰብሰብና ከመረጃ እና ደኅንነት የቴክኒክ ማስረጃ የመጠየቅ ሥራዎች ሰርቻለሁ ብሏል።

የቀሩ ከተባሉ ተግባራት መካከልም የተጠርጣሪዎቹን ቀሪ ግብረ አበሮች መያዝ መሆኑን ፖሊስ ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል በጠየቀበት ማመልከቻ ላይ ጠይቋል።

አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታውን ለሚመለከተው ችሎት እነዚህን ሰነዶች ያቀረበው ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያዎችን እንጂ በአፋር ክልል ፈንታሌ ወረዳ የሚገኘው ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደበትን ሰነድ አላያያዘም ተብሏል።

ችሎቱም የጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደበት ሰነድ እንዲያያዝ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በጉዳዩ ላይ ፖሊስ ይዞ የሚመጣውን መልስ ለመመልከትም ለፊታችን ሐሙስ ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

(BBC)


Report Page