#BBC

#BBC


የትግራይ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችለው አዋጅ እንዲሁም የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አዘጋጅቶ ለውይይት ማቅረቡን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አመለከተ።

በአገሪቱ በዚህ ዓመት ማብቂያ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ ባለው የወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር ቢወሰንም የትግራይ ክልል ግን ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ እንደወሰነ ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህም በክልሉ ለማካሄድ ዕቅድ ከተያዘለት ክልላዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ሁለት የሕግ ረቂቅ ሰነዶች ተዘጋጅተው ነገ ማክሰኞ በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመወየያያት ቀጠሮ መያዙን ለማወቅ ተችሏል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ከሚደረግባቸው ረቂቅ ሰነዶች አንዱ የምርጫና የምርጫ ሥነምግባር ረቂቅ አዋጁ 130 አንቀጾችን የያዘ ነው ተብሏል።

ሁለተኛው ሰነድ ደግሞ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም ለማደራጀት እንዲሁም ስልጣኑንና ተግባሩን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ነው።

ይህ አዋጅ 33 አንቀጾችን የያዘና 27 ገጾች ያሉት ሰነድ መሆኑን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ የአገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ነሐሴ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ ማካሄድ እንደማይችል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።

ምርጫው ወደ 2013 ዓ.ም ሲራዘም ተቃውሟቸውን ካሰሙ አካላት መካከል የትግራይ ክልል አንዱ ሲሆን በክልሉ ወቅቱን ጠብቆ ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን በማስታወቅ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ለማካሄድ የጠየቀውን የክልላዊ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችለው ሁኔታ የለም ቢልም፤ የትግራይ ክልል የሚያቋቁመው አካል ምርጫውን እንደሚያስፈጽም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ በወቅቱ ገልፀዋል።

ይህንንም ተከትሎ በትግራይ ክልል 6ኛው ምርጫ እንዲካሄድ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳታፊ የሚያደርጋቸው የጋራ ምክር ቤትና የምርጫ ተቋም እንዲቋቋም ለክልሉ መንግሥት ጥያቄ አቅርበው ነበር።

የክልሉ ምክር ቤትም የመስከረም ወር ከማብቃቱ ቀደም ብሎ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

ምንጭ፦ BBC

Report Page