BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በሺህዎች የሚቆጠሩ አህዮች በሕገ ወጥ መንገድ ለእርድ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እየተጓጓዙ መሆኑ ተነገረ።

አህዮች በቆዳቸው ምክንያት ከመቼው ጊዜ በላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል። በተለይም በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ የአህያ እርድ ዳግም መፈቀዱን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አህዮች በየቀኑ በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እየተወሰዱ እንደሆነ ይነገራል።

ከአህያ ቆዳ ምን ይገኛል?

የአህያ ቆዳን በመቀቀል ‘ኤህጌዮ’ (Ejiao) ተብሎ የሚጠራ ጄል ይሰራል። ይህ ጄል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጣም ይነገራል።

“በብዙ ዶላር ነው የሚሸጠው። በርካታ ሰዎች ስለሚፈልጉት ዋጋው በጣም ጨምሯል። የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በርካታ አህዮች እየታረዱ ነው” በማለት በኢትዮጵያ ‘ዘ ዶንኪ ሳንክቱአሪ” ኃላፊ ዶ/ር ቦጂዓ ኢንዳቡ ይናገራሉ።

ኤህጌዮ ጄል በሞቀ ውሃ ወይም በአልኮል ሊበጠበጥ ይችላል። ከዚያም የምግብ እና መጠጥ ግብዓት ሊሆን ይችላል። እንደ የፊት ክሬም ያሉ የመዋቢያ ምርቶች ለማዘጋጀትም እጅግ ተፈላጊ ግብዓት ነው።

ዶ/ር ቦጂዓ አህዮች ከኢትዮጵያ በሕገ ወጥ ምክንያት መውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል ይላሉ፤ ይህም በአገሪቱ በሚገኙ የአህያዎች ቁጥር ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ጫና በተጨማሪ የአህዮች ቁጥር መመናመን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን ያስከትላል፡፡

ኢትዮጵያ 9 ሚሊዮን አህዮችን በመያዝ በዓለማችን ቁጥር አንድ በርካታ አህዮች የሚገኙባት አገር መሆኗን የሚናገሩት ደግሞ ‘ዘ ብሮክ’ የተሰኘ አህዮች ተንከባካቢ ድርጅት ኃላፊ አቶ ደስታ አረጋ ናቸው።

“ይህ ‘ኤህጌዮ’ የተሰኘው መድኃኒት ያለውን ፍላጎት ለማሟላት 5.6 ሜትሪክ ቶን የአህያ ቆዳ ያስፈልጋል። በዚህም የበርካታ አህዮች መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያ ዒላማ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል” ይላሉ አቶ ደስታ።

ከዚህ ቀደም በቢሾፍቱ እና አሰላ ከተሞች ተከፍተው የነበሩት የአህያ እርድ ማከናወኛ ማዕከላት በአከባቢው ነዋሪዎች ቁጣ መዘጋታቸው ይታወሳል። በኬንያም ተከልክሎ የነበረው የአህያ እርድ በቅርቡ ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል።

የኬንያ የአህያ እርድ ማከናወኛ ማዕከላት በአገሪቱ የአህያ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጋቸው በስፋት ይነገራል።

“በኬንያ ባሉ አራት የአህያ እርድ ማከናወኛ ቄራዎች ውስጥ በየቀኑ 1ሺህ 200 የሚሆኑ አህዮች ይታረዳሉ። ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ የሚሄዱት ናቸው” በማለት አቶ ደስታ አረጋ ይናገራሉ።

አቶ ደስታ እንደሚሉት አህዮቹ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚጓጓዙበት ሁለት ዋነኛ መንገዶች አሉ። የመጀመሪያው በወልቂጤ- ወላይታ ከዚያም በዳውሮ አድርገው ወደ ኬንያ የሚገቡት ናቸው።

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ከደቡብ ክልል እና ከኦሮሚያ በማሻገር በያቤሎ በኩል ወደ ኬንያ ድንበር ያቋርጣሉ ይላሉ።

አህዮቹ በብዛት እየተጓጓዙ ያሉት ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከአማራ እና ከትግራ ክልሎች መሆኑን እና በሕገ ወጥ መንገድ አህዮቹን ከአገር የሚያስወጡ ደላሎች፤ አህዮቹ ከከብት ገብያ እና በየመንደሩ እየዞሩ እንደሚገዙ አቶ ደስታ ይናገራሉ።

“ከዚህ ቀደም የነበረን መረጃ እንደሚያሳያው በየቀኑ 1ሺህ አህዮች በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ያሳያል” የሚሉት አቶ ደስታ፤ “ይህ ቁጥር ግን ድንበሮች አቅራቢያ ታርደው ቆዳቸው ብቻ የሚላክ አህዮችን አይጨምርም” ይላሉ።

ሕገ ወጥ የአህያ ንግድን መቆጣጣር አይቻልም?

አቶ ደስታ “መንግሥት በቂ ቁጥጥር እያደረገ አይደለም" ይላሉ።

አያይዘውም "በኢትዮጵያ የአህዮች ቁጥር በፍጥነት እየተመናመነ ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ አህያ ሲጠፋ የሚቸገሩት እናቶች እና ሴቶች ናቸው። እነሱ ናቸው አደጋ ላይ የሚወድቁት” በማለት ያስረዳሉ።

በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመጣመር የተለያዩ ሥራዎችን ቢሰሩም፤ የሚፈለገውን ውጤት አለማስገኘታቸውን ጠቅሰው በግብርና ሚንስቴር እና በጉምሩክ ኮሚሽን መካከል በጥምረት ያለመስራት ችግር እንዳለ አቶ ደስታ ተናግረዋል።

Report Page