BBC

BBC


ዛሬ አርብ ማለዳ የባሕር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋለው ችሎት በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉ 55 ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ በሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ ስማቸው የተዘረዘሩ 55 ተከሳሾች ውስጥ 6ቱ በሌሉበት፣ 49 በተገኙበት ፍርዳቸው ሲታይ የነበረ ሲሆን ዛሬ ፍርድ ቤቱ 20ዎቹን በነጸ አሰናብቷል።

በነጻ እንዲሰናበቱ ከተበየነላቸው ተከሳሾች መካከል አቶ ዘመነ ካሴ ይገኝበታል።

1ኛ ተከሳሽ የሆኑት ሻምበል መማር ጌትነት ፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይሰው ሰፊነው፣ 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ሰፊነው በሌሉበት የጥፋተኝነት ብይን የተሰጠ ሲሆን አቃቤ ሕግ ዛሬ ከሰዓት በ3ቱ ዋና ተከሳሾች ላይ የቅጣት አስተያየት እንዲሰጥ ታዝዟል።

ፍርድ ቤቱ በተቀሩት 31 ተከሳሾች ሐምሌ 5 የክስ መቃወሚያ እና መከላከያ ምስክር እንዲያሰሙ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅዳሜ ሰኔ 15 2011 ዓ. ም "በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ሕይወታቸውን ካጡት መካከል አንዱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ናቸው።

በአማራ ክልል የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንንና አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጡረታ ላይ የነበሩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጄኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የአማራ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ "የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው" መሪ እንደሆኑ ከተነገረ በኋላ ባህር ዳር አቅራቢያ በጸጥታ ኃይሎች ተመትተው መገደላቸው ታውቋል።

ችሎቱ የጥፋተኝነት ብይን ሲሰጥ ምን አለ?

ችሎቱ ለብይኑ መነሻ 74 ምስክሮችን እንደሰማ፣ የግል ተበዳዮች የሕክምና ማስረጃዎችን እንደፈተሸ፣ ከብሔራዊ መረጃ ደኅንነት፣ ከፌዴራል ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘውን የሰነድና የቪዲዮ ማስረጃ በግብአት መጠቀሙን ገልጿል።

ሰኔ 15/2011 በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ላይ የተፈፀመው ግድያን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ "ከድርጊቱ ሒደትና አፈጻጸም አንጻር ሲታይ የተከሳሾቹ ዓላማ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ ነበር" ብሏል።

አክሎም በብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ አደራጅነት ሰኔ 15 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ በሻምበል መማር ጌትነት፣ በሻምበል ውለታው አባተ እና በሻለቃ አዱኛ ወርቄ የሚመራ 3 ሻምበል ኃይል በማደራጀት፣ በአማራ ክልል ስራ አመራር ኢንስቲትዩት፣ አባይ ማዶ እየሩሳሌም ሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እና በአማራ ክልል ጣና ሆቴል አቅራቢያ በሚገኘው ገስት ሀውስ አካባቢ በማደራጀትና ስምሪት በመስጠት፣ ማንነቱ ካልታወቀ ከአንድ ግለሰብ ምንጩ ባልታወቀ ሁኔታ ከ5ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶችን በመቀበል የነፍስ ወከፍና የቡድን የጦር መሣሪያ በመጠቀም፣ ወደ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ በፖሊስ ኮሚሽንና ብአዴን ጽሕፈት ቤት በማምራት 14 ከፍተኛ አመራሮችን ለመግደል እቅድ በመያዝ መንቀሳቀሳቸውን አስረድቷል።

በዕለቱ በተለይ ወደ ርዕሰ መስተዳደሩ ቢሮ 3ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 80 በማምራት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የነበሩትን አቶ ምግባሩን ከበደን እንዲሁም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ እዘዝ ዋሴን በጦር መሳሪያ ደጋግሞ የሰውነት ክፍላቸውን በመምታት ገድለዋቸዋል ብሏል ፍርድ ቤቱ።

እንዲሁም ግለሰቦቹ ወደ ርዕሰ መስተዳደሩ ቢሮ ባቀነቡት ወቀት የፕሬዝዳንቱን ጠባቂዎች በማነቅ የጦር መሳሪያቸውን በመቀማት፣ በጦር መሳሪያ በመምታት የግድያ ሙከራ አድርገውባቸዋል ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በሕዝብ ደህንነት ላይ ሁከት በመፍጠር፣ የክልሉን አመራሮች በመግደል፣ የሕዝብ ኑሮና ደኅንነት ላይ አደጋ በመፍጠር፣ በሕገ መንግስት የተቋቋመ ስርዓት ለማፍረስ በመሞከር፣ የክልሉን ስልጣን ለመቆጣጠር ግብ ያደረገ እንደነበር ለዚህም ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ የክልሉን ማስሚዲያ ጨምሮ ዋና ዋና ተቋማትን በመቆጣጠር ሥልጣን ለመያዝ አቅደው ነበር ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡

ሶስት ከፍተኛ የክልሉን አመራሮች ከመግደል ባሻገር የወቅቱ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደሲዬ ደጄና ጥበበ ኃይሉ መኖርያ ቤት በመሄድ የግድያ ሙከራ አድርገዋል፣ ቤተሰባቸውን አውከዋል፣ የንብረት ጉዳትም አድርሰዋል ተብሏል፡፡

'የአማራን ሕዝብ ጥቅም የምናስጠብቀው እኛ ነን፡፡ ይህንን መከላከያ እንዳያከሽፍብን እርምጃ መውሰድ አለብን' በማለት በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ሰዓረ መኮንንና ምክትላቸው ብርሃኑ ጁላ ላይ ግድያ ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡

አብዛኛዎቹ ተከሳሾች ከመከላከያ ሰራዊት በስነ ምግባር የተባረሩና በአሳምነው ጽጌ የተሰባሰቡና ናቸው ሲል ችሎቱ ገልጿል።

ችሎቱ ዛሬ አርብ፣ የጥፋተኝነት ብይን የሰጠው ለሁለት ዓመታት ያህል ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ ነው፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ


Report Page