BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከሰሞኑ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ የክልሉን ፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው አንድ የሳር ክዳን ጎጆ ቤትን ሲያቃጥሉ የሚያሳያውን ተንቀሳቃሽ ምስል እያጣራ መሆኑን ገለጸ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጉዳዩ የት፣ መቼ እና በማን እንደተፈጸመ የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ጉጂ ዞን ተልኳል ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ግርማ ምንም እንኳ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ወደ ስፍራው መላኩን ቢጠቁሙም፤ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየውን አይነት የደንብ ልብስ የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ኃይል አባላት እንደማይለብሱ ገልጸዋል።

"የጸጥታ ችግር ባለባቸው በወለጋ፣ በጉጂ እና በቦረና ዞኖች ይህን አይነት (ሽሮ መልክ ያለው ቡራቡሬ የፖሊስ የደንብ ልብስ) እንዳለይለበስ ሲል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከስድስት ወራት በፊት መመሪያ አስተላልፏል" ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።

አቶ ግርማ ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ፤ "ይህን ዩኒፎርም በብዛት እየለበሱ ያሉት የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ በጉጂ ዞን ውስጥ ይህን እየለበሱ ያሉት የሸኔ አባላት ናቸው። የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የሚለብሱት የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል" ብለዋል።

አቶ ግርማ "ይህ ቪዲዮ የቆየ ከሆነ ብለን አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው ልከናል። ውጤቱ ሲታወቅ ይፋ እናደርጋለን። እስከዚያው ግን እነዚህ ሰዎች የእኛ አባላት ናቸው ወይም አይደሉም ማለት እንችልም። ምክንያቱም ልክ እንደናንተው ነው ቪዲዮን የተመለከትነው" ብለዋል።

የተንቀሳቃሽ ምስሉ ይዘት ምን ነበር?

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በጉጂ ዞን ውስጥ ተፈጸመ በተባለው እርምጃ፤ 'የሸኔ አባል ቤት ነው' የተባለ የሳር ክዳን ቤት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት የደንብ ልብስን በለበሱ እና የአካባቢው ሚሊሻ ናቸው በተባሉ ሰዎች ሲቃጠል ታይቷል።

ቢቢሲ ምሰሉ የት እና መቼ እንደተቀረጸ እንዲሁም የሳር ክዳን ቤቱ እንዲቃጠል የተደረገው በየትኛው አካል እንደሆነ እና የቤቱ ባለቤት ማን እንደሆነ በገለልተኛነት አላረጋገጠም።

ወደ ሰባት ደቂቃ ገደማ በሚረዝመው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ቁጥራቸው ከ10 በላይ የሚሆኑ ሽሮ መልክ ያለው ቡራቡሬ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የሳር ክዳኑን ቤት ሲያቃጥሉ፤ እንዲሁም ቁጥራቸው ያነሰ ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ ዩኒፎርም የለበሱ እና የታጠቁ ሰዎች ሰዎች ቆመው ያሳያል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ሽሮ መልክ ያለው ቡራቡሬ የደንብ ልብስ የለበሱት ሰዎች "ቤቱ የሸኔ ነው ይቃጠል"፣ "ፎቶ አንሳን" ሲሉ ይሰማል።

አንድ የቡድኑ አባል በቤት ውስጥ "ሞፈር አለ" ሲል ሌላኛው ደግሞ "ተወው ማን አርሶ ሊበላ ነው ይቃጠል" ሲል ይሰማል። ከዚያም የታጠቁት ሰዎች ከጎጆው ፊት ለፊት ሆነው በድል አድራጊነት ሲጨፍሩ እና ፎቶግራፍ ሲነሱ ይታያሉ።

ሁለተኛው ቪዲዮ

ከዚህ ቪዲዮ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች አንድን ግለሰብ ከበው ሲያንገላቱ የሚያሳየው ምስል በስፋት ተሰራችቷል።

ቢቢሲ ይህም ተንቀሳቃሽ ምስል የት እና መቼ እንደተቀረጸ እንዲሁም ጥቃት አድራሾቹን እና ጥቃት የደረሰበት ግለሰብን ማንነት በገለልተኛነት አላረጋገጠም።

በምስሉ ላይ የሳር ክዳኑ ቤት ሲያቃጥሉ የነበሩ ሰዎች የለበሱትን አይነት የደንብ ልብስ የለበሰቡ ቢያንስ አምስት የሚሆኑ የታጠቁ ሰዎችን አንድ ግለሰብን ሲያንገላቱ ይታያሉ።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ "የሸኔ አባል ነህ፤ መሳሪያውን የት ነው የደበቅከው አውጣ" ይላሉ ታጣቂዎቹ። ግለሰቡም "የአከባቢውን ሰው ጠይቁ እኔ ከምኑም የለሁበትም" ሲል ይሰማል።

ከዚያም "በለው በጥይት" ይላለ ምስሉን የሚቀርጸው ግለሰብ፤ ከታጣቂዎቹ አንዱም መሳሪያውን አንስቶ ግለሰቡ ላይ ሲያነጣጠር ይታያል። ከዚያም ታጣቂዎቹ ግለሰቡን ተነስቶ እንዲቆም ይነግሩታል። በደብደባ ምክንያት በሚመስል መልኩ ግለሰቡ ተነስቶ በእግሩ ለመቆም ሲታገል ይታያል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ግርማ ገላን፤ ይህ ሁለተኛው ቪዲዮ ላይ የሚታየው ድርጊት እንደተባለው በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት አለተፈጸመም።

"ይህ በእኛ አባላት አለመፈጸሙን አረጋግጠናል ብለዋል" ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ገልጸው በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

Report Page