#BBC

#BBC


በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት በስህተት ቫይረሱ የለብህም ከተባለ ከቀናት በኋላ የተነገረው ውጤት የሌላ ሰው መሆኑ ተገልጾ እሱን ጨምሮ ከእርሱ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸው ተነገረ።

ወጣቱ ህመም ተሰምቶት ወደ የግል የጤና ማዕክል ሁለት ጊዜ ሄዶ እንደነበረ የመንዲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ገመቹ ጉዲና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የበሽታውን ምልክት ማሳየቱን ተከትሎ ዓርብ ዕለት ወደ ሆስፒታላቸው መጥቶ እንደነበረ ዶ/ር ገመቹ ይናገራሉ። "እኛ ሆስፒታል እንደደረሰ ወደ ለይቶ ማቆያ አስገብተን፤ ናሙናው ለምርመራ ተላከ። ከዚያ ቅዳሜ ዕለት ቫይረሱ እንደሌለበት ተነገረን" ይላሉ።

ዶ/ር ገመቺስ እንደሚሉት ከሆነ ግለሰቡ ቫይረሱ እንደሌለበት ለሆስፒታሉ ያስታወቀው የዞኑ ጤና ቢሮ ነው። ነገር ግን "ሰኞ ደግሞ የደረሳችሁ ውጤት የሌላ ሰው ነው አሉን። ስህተት እንደሆነና ግለሰቡ በሽታው እንዳለበት ነገሩን። ከዚያም መልሰን ወደ ለይቶ ማቆያ አስገባነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቅርቡ ወጣቱ በአንድ በርካታ ሰው በሚሰበሰብበት ማህበራዊ ሥነ ሥርዓት ላይ መታደሙንና ከበርካታ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደነበረው የሚናገሩት ዶ/ር ገመቹ፤ በዚህም ሳበያ ከወጣቱ ጋር ንክኪ ሳይኖራቸው አይቀርም ተብለው ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቀስዋል።

"በከተማ ውስጥና በሆስፒታላችንም ከእርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ለይተናል። ከመጀመሪያው ጀምሮ የወጣቱን ቤተሰብ ጨምሮ ከእሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን በፍጥነት ለይተናል። ሰኞ ዕለትም ከእሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ተጨማሪ 30 ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ አስገብተናል። 15 የጤና ባለሙያዎችም ተለይተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወጣቱ "ምልክት ሳያሳይ ከብዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ስለነበረው በከተማው ውስጥና እኛ ጋርም ያለው ስሜት ጥሩ አይደለም" የሚሉት ዶ/ር ገመቹ፤ በቫይረሱ ስጋት ወደ ሆስፒታላቸው የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር መቀነሱንም ተናግረዋል።

በበሽታው መያዙ ከተረጋገጠው ወጣት ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የተደረጉ ሰዎች ቁጥር ወደ 300 እንደሚጠጋ ዶክተሩ አስታውሰዋል።

ጨምረውም "ከሰዎቹ ብዛት አንጻር በለይቶ ማቆያው ብዙ ያልተሟላላችወ ነገር አለ። በቂ ቦታ፣ ምግብና ውሃም እጥረት ይፈጠራል። የጤና ባለሙያዎችም በበሽታው ተይዘው ሊሆን ይችላል" ሲሉ ያላቸውን ስጋት ተናግተዋል።

ምንጭ፦ #BBC

Report Page