#BBC

#BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በምዕራብ ኦሮሚያ በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ ባለፈው ዓርብ አራት የመንግሥት ሠራተኞች በታጣቂዎች መገደላቸው ነገረ።

ከጥቃቱ የተረፉት የነጆ ወረዳ አስዳዳሪ እና ከሟች ቤተሰቦች ቢቢሲ እንደተረዳው ዓርብ ዕለት የሸኔ አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በ10 የመንግሥት ሠራተኞች ላይ በተፈጸመ ጥቃት አራቱ ሲገደሉ ሦስቱ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሦስት ሰዎች ደግሞ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከጥቃቱ ተርፈዋል።

ግንቦት 21/2012 ዓ.ም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለማከፋፈል ከተለያዩ ቢሮዎች የተወጣጣ ኮሚቴ አሞማ ዴገሮ ወደ ሚባል ቀበሌ ተጉዞ እንደነበነር የነጆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተፈራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የመንግሥት ሠራተኞቹ ከሄዱበት ስፍራ በሰላም ሥራቸውን ጨርሰው እየተመለሱ ዋጋሪ ቡና ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲደርሱ ጸረ ሰላም በሆኑት የሸኔ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶበናቸዋል" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል::

ለመስክ ሥራ ተሰማርተው የነበሩት ሰዎች በአጠቃላይ 10 እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ተሊላ በጥቃቱ ከመካከላቸው አራቱ ተገድለዋል።

"አንደኛው ሟች አብዲ አበራ የሚባል ሹፌር ሲሆን ሁለተኛው የእንስሳት ሐኪም የነበረው ዳዊት ተርፋሳ ሲሆን፤ ባሕሩ አየለ እና እስራኤል መርዳሳ የሚባሉት ሟቾች ደግሞ የወረዳው ሚሊሻ አባላት ናቸው" ብለዋል።

በታጣቂዎቹ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ሦስቱ በጥቃቱ የቆሰሉት ሲሆን፤ ከጥቃቱ ጉዳት ሳይደርስባቸው ያመለጡት ደግሞ ሦስት ናቸው።

የተፈጠረው ምን ነበር?

በመንግሥት ሠራተኞቹ ላይ ጥቃቱ የተሰነዘረው ዓርብ ከሰዓት በኋላ ላይ ነበር።

የአስሩ የመንግሥት ሠራተኞች መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ድጋፍ የተገኘውን የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ለማከፋፈል ወደ አሞማ ዴገሮ ይጓዛሉ።

እነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች ከወረዳው የአደጋ ዝግጁነት እና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት፣ ከእንስሳት ጤና፣ ከሚሊሻ የተወጣጡ ነበሩ።

ለመስክ ሥራ የተሰማሩት ሠራተኞቹ የሄዱበትን ሥራ ፈጽመው ወደ ነጆ ከተማ እየተመለሱ ሳለ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ከ35 ገደማ ዋጋሪ ቡና ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የሸኔ አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ ተከፍቶባቸዋል።

"በቅድሚያ የመኪናውን ጎማ በጥይት መቱ" ያሉት አቶ ተሊላ፤ መኪናው ሲቆም በመኪናው ውስጥ በነበሩት ሠራተኞች ላይ ተኩስ መከፈቱን ይናገራሉ። "ከዓይን እማኞች መገንዘብ እንደቻልነው ጥቃቱን የሰነዘሩት ታጣቂዎች በቁጥር ስምንት ይሆናሉ" ብለዋል::

"መኪናው በጥይት ተመትቶ እንደቆመ ሮጠው ማምለጥ የቻሉት ህይወታቸውን ማትረፍ ችለዋል። በመኪናው ውስጥ ከነበሩት መካከልም በጥይት ተመተው 'ሞተዋል' ብለው ያለፏቸውም አሉ" ይላሉ አቶ ተሊላ።

በጥቃቱ የተገደሉት አራቱ ሰዎች ህይወታው ያለፈው ወዲያ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ፈጽመው በመኪናው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ከገደሉና ካቆሰሉ በኋላ የመንግሥት ሠራተኞቹ ይዘዋቸው የነበሩትን 4 የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችን ዘረፍው መሄዳቸውን ገልጸዋል።

ከጥቃቱ በኋላ በአካባቢው ተሰማርቶ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአሮሚያ ልዩ ኃይል የጥቃቱን ፈጻሚዎች ለማግኘት አሰሳ እያካሄደ መሆኑን እና እስካሁን ግን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ እንደሌላ አስረድተዋል።

ሥራ በጀመረ በሦስተኛ ሳምንቱ የተገደለው ሹፌር

በታጣቂዎቹ ከተገደሉት መካከል አንዱ የሆነውና መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው አብዲ አበራ ነው። የአብዲ ታላቅ ወንድም ቴዲ አበራ "ወንድሜን ድንጋይ ተሸክሜ ነው ያሳደኩት፤ ሥራ ከጀመረ እንኳ ገና ሦስተኛ ሳምንቱ ነው" ይላል።

"ያለ አባት ነው ያደገው። ከተቀጠረ እንኳን ገና ሦስት ሳምንት አልሆነውም። የአንድ ወር ደሞዝ እንኳን አልበላም። የአንድ ዓመት ከሁለት ወር ወንድ ልጅ አለው። ይሄው ልጁም ልክ እንደሱ ያለ አባት ሊያድግ ነው" ሲል በመሪር ሐዘን ውስጥ ሆኖ ስለወንድሙ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቴዲ "አስክሬኑን አመጥተው ነው የሰጡን። ማን ገደለው? ለምን ተገደለ? ብለን የምንጠይቀው እንኳን የለም። ሰው ቀና ብሎ የማያይ፤ ሰዎች የሚወዱት ገና የ21 ዓመት ልጅ ነበረ" ሲል ታናሽ ወንድሙን ያስታውሳል።

ስለወንድሙ ሲናገር እምባ የሚቀድመው ቴዲ፤ ታናሽ ወንድሙ አብዲ ከሦስት ሳምንት በፊት ይህን የሹፍርና ሥራ በወረዳው ተቀጥሮ መስራት ከመጀመሩ በፊት በነጆ ከተማ የሰው ባጃጅ እየነዳ ይተዳደር እንደነበረ ገልጿል።

በሐዘን ክፍኛ የተጎዳው ቴዲ በመረረ ስሜት የወንድሙን ሞት "ተስፋዬ ነበር። ተስፋዬን ቀበርኩ። በእኛ ላይ የደረሰው በጠላት ቤት እንኳን አይግባ" ሲል የደረሰበት መከራ ሌሎች ላይ እንዳይደርስ ተመኝቷል።

የመንግሥት ሠራተኞች ስጋት ?

የነጆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተፈራ እንደሚሉት፤ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞችን ዒላማ ያደረገ መሰል ጥቃት በአካባቢው ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

"አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር እነዚህ ቡድኖች የልማት ሥራዎች ሲሰሩ አይደሰቱም። ከዚህ ቀደም የመንግሥት ሠራተኞችን ኢላማ ሲያደርጉ ነበር" ይላሉ።

ከዚህ በፊት የወረዳ፤ የቀበሌ አስተዳዳሪ ተገድሏል፣ ሚሊሻ ተገድሏል፣ ማዕድን አውጪ ባለሙያዎች መገደላቸውን የሚናገሩት አቶ ተሊላ "አሁን ጥቃት የተፈጸመባቸው ሠራተኞች በመንግሥት መኪና መንቀሳቀሳቸውንና ሚሊሻ ከእነሱ መሆኑ ሲያውቁ ነው ጥቃት የሰነዘሩባቸው" ይላሉ።

ይህ በአካባቢው የሚፈጸመው ተደጋጋሚ ጥቃት በመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩንም ተናግረዋል።

"የመንግሥት ሠራተኞች ስጋት አላቸው። በጸጥታ ኃይል ካልታጀቡ በቀር ወደ ገጠር ለሥራ የሚሰማራ የመንግሥት ሠራተኛ የለም። ሥራ የሚሰራው በጸጥታ ኃይሎች ትብብር ብቻ ነው" ይላሉ።

ማቆሚያ የሌለው የሚመስለው የምዕራብ ኦሮሚያ እሮሮ

በምዕራብ ኦሮሚያ በታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል በሚባሉ ጥቃቶች በርካታ ንጹሃን ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን፣ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በተለያዩ ጊዜያት ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

መንግሥት በአካባቢው በታጣቂዎች ለሚፈጸሙት ጥቃቶች የኦነግ ሸኔ አባላትን ተጠያቂ ያደርጋል።

የኦሮሚያ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ ዞኖች በኦነግ ሸኔ በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች ከ770 በላይ ሰዎች መገደላቸው እና 1300 በላይ የሚሆኑ ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ከዚህ ባሻገርም 72 ሰዎች ደግሞ ታፍነው የተወሰዱ እና የገቡበት ቦታ እስካሁን የማይታቅ መሆኑን ተገልጿል።

Report Page