BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ባለፈው የምዕራባውያን ዓመት ልዩ ልዩ መንግስታዊ የፀጥታ ኃይሎች እና ከእነርሱ ጋር በትብብር የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኢመደበኛ ቡድኖች አሰቃቂ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ሲል ወነጀለ።

አምነስቲ ዛሬ ይፋ ባደረገው የሰባ ሁለት ገፅ ጥናታዊ ዘገባው ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱ ክልሎች ባደረግኩት ምርመራ በኦሮሚያ ምስራቅ እና ምዕራብ ጉጂ እንዲሁም በአማራ ምዕራብ እና መካከለኛ ጎንደር ዞኖች የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ፖሊስ፣ የየአጥቢያ ባለስልጣናት እና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው የወጣት ቡድኖች አባላት በመብት ጥሰቶቹ ተሳትፈዋል ብሏል።

"ከሕግ ማስከበር ባሻገር፣ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀሙ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች" የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀሙ ህገወጥ ግድያዎች፣ የጅምላ እስሮች፣ በግዳጅ ማፈናቀል እና የንብረት ማውደሞች በአፋጣኝ መቆም እንዳለባቸው በይፋ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ጠይቋል::

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን መምጣት በኋላ በአገሪቱ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር ረገድ ከታዩ አዎንታዊ እርምጃዎች ጎን ለጎን ፖለቲካዊ እና ብሔር ተኮር ውጥረቶች አብረው ታይተዋል፤ እነዚህ ውጥረቶችም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሃረሪ፥ ድሬዳዋ እና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሎች እና አስተዳደሮች የትጥቅ እንቅስቃሴዎች እና የማኅበረሰብ ግጭቶች መቀስቀስ ምክንያት ሆነዋል ይላል አምነስቲ።

ኦሮሚያ

በጎርጎሳውያኑ 2019 መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ፀጥታ ማስከበርን ግብ ያደረገ ግብረ ኃይል አቋቋሟል። ግብረ ኃይሉ የቀበሌ ሚሊሻዎችን፥ የኦሮሚያ ልዩ እና መደበኛ ፖሊስ ኃይሎችን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር በሁለቱ ዞኖች ያለውን የቀድሞውን የኦሮሞ ነፃነት ጦር (ኦኤልኤ) የተባለውን ታጣቂ ቡድን የመመከት ዓላማ እንዳለው ይገለፃል አምነስቲ በኦሮሚያ ተፈፅመዋል ያላቸውን ጥሰቶች ሲዘረዝር።

በጎርጎሳውያኑ በጥር 2019 በምስራቅ ጉጂ ዞን በምትገኘው ጉሮ ዶላ ወረዳ እና በምዕራብ ጉጂ ዞን በምትገኘው የዱግዳ ዳዋ ወረዳ 39 ሰዎች መገደላቸውን በምርመራዬ ደርሸበታለሁ ይላል አምነስቲ። ከእነዚህም መካከል 23 ያህሉ በጎሮ ዶላ ወረዳ በመከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሚያ ፖሊስ የተገደሉ ናቸው ሲል የሚከሰው የመብት ተሟጋቹ ሪፖርት 16 ያህሉ ደግሞ በዱግዳ ዳዋ ወረዳ ርሸና ከችሎት ውጭ በሚመስል አኳኋን ለመገደላቸው ተዐማኒ ማስረጃ አለኝ ይላል።

ዘገባው ቀጥሎም ከወራት በኋላ፣ በወርሃ ጥቅምት በጎሮ ዶላ ወረዳ በምትገኘው ራሮ ቀበሌ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጨደቻ መኢሳ፣ አብዱላሂ ጎሉ ሃላኬ እና ቃንቄ ኡታራ ሹሬ ከታሰሩባቸው ህዋሳት ካወጧቸው በኋላ የተባሉ ዘመዳማቾችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋቸዋል ይላል። ዘመዳማቾቹ ለእስር የተዳረጉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የቀድሞው የኦሮሞ ነጻነት ጦርን በመደገፍ ተጠርጥረው ነው::

በነሐሴ ወርም ቢሆን ቦዲሻ ጩሉቃ የተባለ የእነ አብዱላሂ የቅርብ ዘመድ እንዲሁ በመከላከያ ሠራዊት ከታሰረ በኋላ ተገድሏል- እንደ አምነሰቲ። በታሰረ በቀጣዩ ቀን ቤተሰቦቹ በጥይት መበሳሳቱ የሚታይ ሬሳውን ቁጥቋጦ ውስጥ አግኝተውታል።

"ወታደሮች በሬ እናራርድ እና ወደቀብር ስፍራውም [በአካባቢው ልማድ እንደሚደረገው] ምግብ እንዳንወስድ ከልክለውናል። ለሸኔ ወታደሮች ምግብ ልትወስዱ ነው አሉን፤ ምንም እንኳ የተቀበረው ከተማው ውስጥ ቢሆንም" ስትል የቦዲሻ ዘመድ የሆነችው ቦናኒ ጃለታ ነግራኛለች ይላል አምነስቲ።

መሰል ግድያዎች በጎርጎሳውያኑ ታህሳስ 4 ቀን (በኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ኃይል)፣ የካቲት 3 ቀን 2019 (በመከላከያ ሠራዊት)፣ በነሐሴ 2019 (በመከላከያ ሠራዊት)፣ በጥር እና ግንቦት 2019፣ በታህሳስ 2018 (በመከላከያ ሠራዊት) ተፈፅመዋል ይላል የመብት ተሟጋቹ ድርጅት።

ይቀጥልናም ከግድያዎቹም ባሻገር ዘፈቀዳዊ እስር ተፈፅሟል፤ በእስር ወቅትም ስቅይት ተከናውኗል፤ ገና ምርመራ ላይ ብሆንም የአስገድዶ መደፈር ክስም ቀርቦልኛል ብሏል።

ከቀያቸው በግድ የተፈናቀሉ እና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸውም አሉ- እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል።

አማራ

በጎርጎሳውያኑ ከመስከረም 2018 እስከ ጥቅምት 2019 ድረስ በምዕራብ እና መካከለኛው ጎንደር ዞኖች በሚገኙ የቅማንት እና አማራ ማኅበረሰብ አባላት መካከል ግጭት ጨምሮ እንደነበር በመጥቀስ ነው አምነስቲ በአማራ ክልል ተፈፅመዋል ያላቸውን የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች መዘርዘር የሚጀመረው።

በቋራ፣ መተማ እና ጭልጋ ወረዳዎች የክልሉ ፖሊስ አባላት እና የአካባቢው ሚሊሻዎች የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚለው የመብት ተሟጋቹ በአቅራቢያ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አሃዶች ጉዳዩን ለማስቆም የወሰዱት ምንም ዓይነት እርምጃ የለም ይላል። በጎርጎሳውያኑ በጥር 10 እና 11 እንዲሁም በመስከረም 2019 የጣልቃ ግቡልን ተማፅኖ ቢቀርብላቸውም የሠራዊቱ አባላት ከቸልታቸው አልተናጠቡም ይላል አምነስቲ።

እንደ አምነስቲ ዘገባ ከሆነ በጥር 2019 ቢያንስ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 58 ሰዎች ተገድለው በጅምላ መቀበራቸው ተዘግቧል።

ከጎንደር ከተማ የፀጥታ ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ በመመስረትም በጎርጎሳውያኑ በመስከረም እና ጥቅምት 2019 በከተማዋ ዙርያ ተቀስቅሶ የነበረውን ማኅበረሰባዊ ግጭት ለ43 ሰዎች ሞት እና ለ12 ሰዎች መቁሰል ምክንያት ሆኗል።

የክልል የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የፀጥታ ኃይሎች፣ በተለይም የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በስፍራው ባይሰማሩ ኖሮ የተጠቂዎች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ ይችል እንደነበር ነግረውኛል ብሏል።

በጎርጎሳውያኑ ጥር 10 ቀን 2019 ከሰዐት በኋላ ላይ በመተማ ዮሃንስ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጎበዝ አለቃ እና ፋኖ የሚባሉ ኢ-መደበኛ የወጣት ቡድኖች ቀበሌ ሦስት የሚባለውን መንደር በመክበብ ነዋሪዎችን በጠመንጃ፣ በድንጋይ እና በፈንጅ አጥቅተዋል- ይላል የአምነስቲ ዘገባ። ይህም መንደር በብዛት የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት የሚኖሩበት ነው። የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቦታው ደርሰው ነዋሪዎቹን ሲታደጉ ጥቃቱ ለ24 ሰዓት ገደማ ተከናውኖ ነበር።

የዐይን ምስክሮች እንደነገሩኝ ጥቃቱን ለማድረስ ለቀናት ያህል ዝግጅት ሲደረግ ነበር፤ የወጣት ቡድኖቹ ጥቃት በክልሉ ልዩ ፖሊስ እና በአጥቢያው ሚሊሻዎች የታገዘ ነበር፤ ከመንደሩ አቅራቢያ ባለፈው የሰፈራ ጣብያቸው የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ለሃያ አራት ሰዐታት ያህል ምንም አላደረጉም ነበር ይላል።

በለጠ መንግስቱ የተባሉ የዐይን እማኝ "ሠራዊቱ የመጣው፤ ጉዳቱ ሁሉ ከደረሰ በኋላ ነው። 1600 የሚሆኑ የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት ወደጦር የሰፈራ ጣብያ ተወስደዋል" ብለውኛል ይላል አምነስቲ። በጎርጎሳውያኑ ጥር 12 ቀን 2019 "የሞቱትን መተማ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስትያን ስንቀብር 58 ሬሳ ቆጥሬያለሁ" ብለዋል በዘገባው የተካተቱት እኝሁ የዐይን እማኝ።

አምነስቲ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም በጎርጎሳውያኑ ጥር 11 ቀን ብዙ የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት በሚኖሩበት መንደር እሳት እና ጭስ እንደነበርና በከተማዋ ሰሜን ምዕራባዊ አቅጣጫ ያሉ ሁለት አካባቢዎች የተቃጠሉ እንደሚመስል ደርሼበታል ብሏል።

ከጎንደር ከተማ በስተስሜን በሚገኙ እና በብዛት የቅማንት ነዋሪዎች ባሉባቸው አርባባ፣ ወለቃ እና ሳይና ቀበሌዎች የበቀል የሚመስል ጥቃት በአማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ደርሷል ያሉ ሰዎችንም አናግሬያለሁ ይላል ዘገባው። ይህ የምላሽ ጥቃትም ጥቅምት 14 ጀምሮ፣ እስከ ጥቅምት 16 ቀጥሏል።

በእነዚህ ማኅበረሰባዊ ግጭቶች ቢያንስ 130 ሰዎች መገደላቸውን ለዚህም የፀጥታ ኃይሎች ቸልታ አስተዋፅዖ እንዳለው ያትታል አምነስቲ።

የመንግስት አካላት አስተያየት

አምስነቲ ለልዩ ልዩ የመንግስት አካላት እንደየሚናቸው ምክረ ኃሳቦችን ያቀረበ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለመከላከያ ሚኒስትር፣ ለሰላም ሚኒስትር፣ ለፖሊስ ኮሚሽን እና ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፀጥታ ኃይሎችን የሚቆጣጠር ተዐማኒ፣ ገለልተኛ እና ሲቪል ተቋም ስለመመስረት፣ ጥቃት አድራሾቹን ስለመለየት እና ለፍርድ ስለማቅረብ፣ በጥቃቶች ላይ በቀጥታ የተሳተፉ የሠራዊት አካላትን ስለመበተን፣ በየጊዜው መንግሥት ህገ ወጥ ግድያዎችን ለመመርመር እና ለፍርድ ለማቅረብ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ይፋ ስለማድረግ የሚያወሱ ይገኙባቸዋል።

ዘገባውን በሚያጠናቅርበት ጊዜ በአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ አይከል፣ አይምባ፣ ወለቃ እና ሃዋሳ የሚገኙ ከ80 በላይ ግለሰቦችን ማናገሩን የሚገልፀው አምነስቲ፣ በግኝቱ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡት የሰላም ሚኒስትርን፣ የመከላከያ ሚኒስትርን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን፣ የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ጉዳዮች ፅህፈት ቤትን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን፣ የአማራ ፀጥታ ቢሮን እና የአማራ ፖሊስ ኮሚሽንን መጠየቁን ይናገራል።

ይሁንና ለጥያቄው ምላሽ ያገኘው ከአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ ብቻ መሆኑንን ገልፆ ቢሮውን ያመሰግናል።

Report Page