BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

119 ቤተ እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ማቅናታቸው ተገለጸ። እንደ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ከሆነ ቤተ እስራኤላውያኑ ከቀናት በፊት ነው የተጓዙት።

ይህንኑ በኢትዮጵያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አረጋግጧል። ጥር ላይ የእስራኤል ካቢኔ 400 የሚጠጉ ቤተ እስራኤላውያንን እና የሃገሪቱ የስደተኞች ህግ የሚያሟሉ ሰዎችን ለመወስድ የቀረበውን ዕቅድ ማጽደቁን ኤምባሲው ገልጿል።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም ነው 119ኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ሃገሪቱ ያቀኑት። በኢትዮጵያ ያለው የአይሁዳዊያን ድርጅት ቅርንጫፍም የካቢኔውን ውሳኔ ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን ሲያስታውቅ በተመሳሳይም በኢትዮጵያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲም ውሳኔውን በማስፈጸም ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ሰዎቹ እስራኤል ሲደርሱም የአይሁዳዊያን ድርጅት ሊቀመንበር አይዛክ ሄርዞግ እና አዲሷ የስደተኞች እና ውህደት ሚንስትር ፕኒና ታማኖ-ሻታ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕኒና “አዲሱን ሥራዬን በምጀምርበት ወቅት 119ኙን ሰዎች በመቀበሌ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል” ሲሉ ገልጸዋል። ቤተ እስራኤላውያኑ “ህልማቸው የሆነው ጉዞ እንዲሳካ ለዓመታት ጠብቀዋል። አሁን ሃገራቸው ደርሰዋል በዚህም ደስታ ተስምቶኛል” ብለዋል።

አዲሱን ህይወታቸውን እንዲጀምሩ ለመርዳት በሁሉም ረገድ ድጋፍ ይደረግላቸዋልም ሲሉ ተናግረዋል። ቤተ እስራኤላውያኑ የገበቡበት ቀን ወደ እስራኤል ሲያቀኑ ህይወታቸው ያለፉ ቤተ እስራኤላውያን በሚታሰቡበት ዕለት ላይ መሆኑ ተዘግቧል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሃገሪቱ ጤና ሚንስትር እና የትራንስፖርት ባለስልጣን ካወጧቸው ደንብ ጋር በተጣጣመ መልኩ ቤተ እስራኤላውያኑ በልዩ በረራ ነው እስራኤል የደረሱት ተብሏል።

ቤተ እስራኤላውያኑ ወደተዘጋጀላቸው የለይቶ ማቆያ እንደገቡም ነው የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ያስታወቁት።

ከሁለት ወራት በፊት እስራኤል በተመሳሳይ 72 ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ወስዳለች።

ባለፉት ጥቂት ቀናት እስራኤል 111 ስደተኞችን ከዩክሬን እንዲሁም 41 ደግሞ ከሩሲያ ተቀብላለች። ፕኒና ታማኖ-ሻታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱ ቤተ እስራኤላዊ ሲሆኑ በቅርቡ ነበር በሚኒስተርነት የተሾሙት።

Report Page