#BBC

#BBC


የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ በነጭ ፖሊስ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ ጉዳይ መመርመር ጀምሯል፡፡

ክስተቱ ባሳለፍነው ሰኞ የተፈጸመ ሲሆን አንድ ነጭ የፖሊስ መኮንን ጥቁር አሜሪካዊን በእግሩ ጉልበት አንገቱ ላይ ቆሞ ሲያሰቃየው ከቆየ በኋላ መተንፈስ አቅቶት ሲዝለፈለፍ ያሳያል።

ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በአስደንጋጭ ፍጥነት በተዘዋወረው ምሥል ላይ ነጭ ፖሊስ የዚህን ጥቁር አሜሪካዊ አንገት በጉልበቱ ተጭኖት እያለ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ተጠርጣሪው በበኩሉ ‹‹መተንፈስ አልቻልኩም እባክህን አትግደለኝ›› እያለ ሲማጸነው ይሰማል፡፡

ሟቹ የ40 ዓመት ጎልማሳ ጥቁር አሜረካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ይባላል።

ሆኖም ተጠርጣሪው በፎርጂድ ምርት ተግባር ላይ እንደተሰማራ ጥቆማ ደርሶት ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሊያውለው እንደመጣ ተጠቅሷል፡፡

ይህ ዘግናኝ ክስተት ከዓመታት በፊት በተመሳሳይ ቁጣን የቀሰቀሰውና በነጭ ፖሊስ ጭካኔ የሞተውን ኤሪክ ጋርነርን ያስታወሰ ሆኗል፡፡ ኤሪክ በወቅቱ በፖሊስ አንገቱ ተቆልፎ ‹‹እባካችሁ መተንፈስ አልቻኩም›› እየለ በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር የሞተው፡፡

ሰኞ ለታ የሞተው የአርባ ዓመቱ ጎልማሳ ማጅራቱን ከቆለፈው ፖሊስ ጋር ግብግብ አልባ የስቃይ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ስለመሞቱ የሚኒሶታ ፖሊስ አምኗል፡፡

ይህ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ በኋላ የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጊቱ ሰቅጣጭና አሳፋሪ ብለውታል፡፡

አጭር የምስል መግለጫ
ሟች ጆርጅ ፍሎይድ

‹‹ያየሁት ነገር አስቀያሚ ነገር ነው፡፡ ያየሁትን ነገር በየትኛውም መስፈርት ስህተት ነው። ጥቁር አሜሪካዊ መሆን የሞት ፍርድን ሊያሰጥ አይገባም›› ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

በአሜሪካ ነጭ ፖሊሶች በጥቁሮች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው ሲኮነኑ ይሄ የሰኞ ለታው ክስተት አዲስ አይደለም፡፡

በቅርቡ እንኳ በሜሪላንድ አንድ የፖሊስ ባልደረባ ፓትሮል መኪና ውስጥ የነበረን ጥቁር አሜሪካዊ ተኩሶ ገድሏል፡፡

ሰኞ በሚኒሶታ ሜኒያፖሊስ ያጋጠመው ክስተት ለ10 ደቂቃ ያህል የቀረጹ የአይን እማኞች ፖሊሱ ጉልበቱን ከተጠርጣሪው አንገት እንዲያነሳ ሲጠይቁት በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ይታያል፡፡

በምሥሉ ላይ ሟችም መተንፈስ አልቻልኩም ከማለቱም በላይ እባክህን አትግደለኝ እያለ በተደጋጋሚ ሲማጸን ያሳያል፡፡

ሌላ የዐይን እማኝ ‹‹እባክህን አፍንጫውን እየነሰረው ነው›› ሲል ፖሊሱን ይማጸነዋል፡፡ ፖሊሱ ምንም ምላሽ አይሰጥም፤ ሆኖም ሌላ የፖሊስ ባልደረባ ቀረጻውን በመከለል ለማስተጓጎል ሲሞክር ይታያል፡፡

በቪዲዮው ላይ ሌላ የዐይን እማኝ ‹‹አሁን የገደልከው ይመስለኛል፤ ይህ ድርጊትህ ሕይወትህን ሙሉ ይከተልሃል›› ሲል ይሰማል፡፡

ከዚህ በኋላ ተጠርጣሪው እንቅስቃሴ አልባ ሆኖ ይዝለፈለፋል፡፡ አምቡላንስ መጥቶም ይወስደዋል፡፡ ምናልባት ግለሰቡ በዚያው ቅጽበት ሞቱ እንደሆነም ተጠርጥሯል፡፡

ፖሊስ ግን ግለሰቡ የሞተው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ነው ይላል፡፡

ኤፍ ቢ አይ ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተሳታፊ ናቸው የተባሉት አራት ፖሊሶች ከስራቸው ተባረዋል።

ኤሪክ ጋርነት በ2014 በተመሳሳይ ከተገደለ በኋላ መተንፈስ አቃተኝ የሚለው ድምጹ የጥቁር አሜሪካዊያን የመብት ተሟጋቾች መሪ ቃል ሆኖ ጸንቷል፡፡

ጋርነት ፖሊስ ማጅራቱን ቆልፎት ሳለ ከመሞቱ ቀደም ባሉ ደቂቃዎች ሁሉ ‹‹ መተንፈስ አቃተኝ›› የሚለውን ቃል ለ11 ጊዜ ደጋግሞ ሲለው ነበር፡፡

ለጋርነር ሞት ተጠያቂ የተደረገው ፖሊስ ከሥራው የተባረረው ከክስተቱ አምስት ዓመታትን ቆይቶ መሆኑ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል፡፡

#BBC

Report Page