#BBC

#BBC


በሌባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ስምንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው እየተነገረ ነው!

የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በሌባኖስ ውስጥ ስላለው የኮሮናቫይረስ ክስተት መረጃዎችን በሚያቀርብበት ድረ ገጽ ላይ ስምንት ኢትዮጵያዊያን በበሽታው እንደተያዙ ያመለከተ ሲሆን፤ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ግን ስለተጠቀሰው አሃዝ ከአገሪቱ መንግሥት የተሰጠው መረጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በሌባኖስ እስከ አሁን ድረስ 886 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከእነዚህ መካከል ስምንቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ካወጣው የህሙማኑ ዜግነት ዝርዝር መረዳት ይቻላል።

እንደ አገሪቱ መንግሥት መረጃ ከሆነ በሌባኖስ በቫይረሱ ከተያዙ አጠቃላይ ሰዎች ሰባት በመቶው ያህሉ ውጪ አገራት ዜጎች ሲሆኑ የስምንቱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከፍተኛው መሆኑን አመልክቷል።

በጉዳዩ ላይ BBC ያነጋገራቸው በሌባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ፤ አንድም ኢትዮጵያዊ በቫይረሱ አለመያዙን ተናግረው የነበረ ሲሆን፤ ቢቢሲ የወጣውን አሃዝ ለማረጋገጥ ዛሬ ወደ ቆንስሉ ደውሎ "እኛ የምናውቀው በበሽታው የተያዙ ኢትዮጵያውያን አለመኖራቸውን ነው" ብለዋል።

አጭር የምስል መግለጫ
በዚህ ግራፍ መሰረት በመጨረሻው መስመር ላይ ያለው የኢትዮጵያውያንን ቁጥር የሚያመለክት ነው

ቆንስሉ በየጊዜው ከሌባኖስ መንግሥት መረጃ እንደሚደርሳቸው፤ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዘም ሆነ የሞተ ኢትዮጵያዊ ስለመኖሩ የደረሰን ነገር የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቆንስሉ አክለውም መረጃውን አጣርተው ዳግም እንደሚገልፁ አስታውቀው የኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አቶ አክሊሉ ከትናንት በስቲያ በተከታታይ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው ኢትዯጵያውያን የነበረባቸውን ውዝፍ የቀራማ ክፍያ /ቅጣት/ ወደ አንድ ዓመት ዝቅ እንዲል ማስደረጉን ገልፀው ነበር።

ቆንስላው ለሊባኖስ መንግሥት በተደጋጋሚ ይህ የአንድ ዓመት የቀራማ ክፍያ /ቅጣት/ ክፍያ እንዲቀር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አቅርቦ ዛሬ (ግንቦት 14/2020 ) ከሊባኖስ መንግስት የደህንነትና ኢሚግሬሽን ጉዳዮች ባለስልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት ይህ የአንድ ዓመት የቀራማ/ቅጣት/ ክፍያ እንደሚቀር ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

አቶ አክሊሉ አክለውም ከሊባኖስ መውጣት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የጉዞ ሰነድ በማውጣትና የመውጫ ቪዛቸውን በማግኘት መሄድ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። "ለዜጎቻችንንም ከእንንግዲህ በኋላ የቀራማ ክፍያው ነጻ መሆኑን ቆንስላው ለማሳወቅ ይወዳል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያናገራቸው በሌባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል ጀምሮ ይደርሱባቸው የነበሩ እንግልቶችን በተመለከተ ለሚያቀርቡት አቤቱታ ቆንስላው ምንም አይነት ድጋፍም ሆነ ከለላ አይሰጠንም ሲሉ ሲወቅሱ ቆይተዋል።

በሊባኖስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል። የተጣለው የሰዓት እላፊ እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ ይቆያል ተብሏል።

በቤሩት ሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንስል የሆኑት አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ ለቢቢሲ እንደገለፁት፤ በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ "በሕገ ወጥ መልኩ" እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

(BBC)

Report Page