#BBC

#BBC


በኮቪድ-19 የተያዘው የምዕራብ ሀረርጌው ወጣት!

(በቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት)

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አራት ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጾ ሦስቱ ከፑንትላንድ መምጣታቸውን፤ አንዱ በምዕራብ ሐረርጌ ጉባ ኮሪቻ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ግን ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪም ሆነ የጉዞ ታሪክ እንደሌለው በመግለጽ ቫይረሱ እንደተገኘበት ካስታወቀ በኋላ ጉዳዩ እየተጣራ ነው ተብሎ ነበር።

በምዕራብ ሐረርጌ በጉባ ኮሪቻ በኮቪድ-19 እንደተያዘ የተነገረው ወጣት፣ እንዴት በቫይረሱ ሊያዝ ቻለ በማለት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወጣቱ ተኝቶ ወደሚታከብት ሂርና ሆስፒታል በመደወል አነጋግረውታል።

በአሁኑ ሰዓት በሂርና ሆስፒታል ለይቶ ማከሚያ ውስጥ የሚገኘው ወጣቱ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ከእርሱ ውጪ ሌላ የኮቪድ-19 ታማሚ እንደሌለ ገልጿል። የጤና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን እንክብካቤ በሙሉ እያደረጉለት መሆኑን ተናግሯል።

አሁን ስላበት ጤንነት ሁኔታም ሲናገር "ይህ በሽታ እንዴት እንደያዘኝ አላውቅም፤ ምንም የሚያመኝ ነገር ስለሌ ተይዣለሁ ብዬም አላስብም" ብሏል። በምዕራብ ሐረርጌ ነዋሪ የሆነው ይህ ወጣት ጤና ሚኒስቴር የጉዞ ታሪክ የለውም ይበል እንጂ እርሱ ግን በጅቡቲ በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ሲሞክር ጅቡቲ ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ ተናግሯል።

"ጅቡቲ ደሂል የምትባል ቦታ 11 ቀን ነው የቆየነው። ከዚያ ፖሊስ [የጅቡቲ] ይዞን ወደ ኢትዮጵያ መለሰን" ካለ በኋላ፣ እርሱና ጓደኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ለ12 ቀናት በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መቀመጣቸውን አስረድቷል። የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ቆይታ በኋላ ወደ ጭሮ ከዚያም ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ስፍራ እንዳቀና እና እዚያም ለ14 ቀናት እንደቆየ ተናግሯል።

በጤና ሚኒስቴር መግለጫ ላይ 23 እንደሆነ ቢገለጽም እርሱ ግን "19 እንኳ አልሞላኝም" ብሏል። "ድሬዳዋ እንዳለን አትጨባበጡ፣ የምግብ እቃዎችን በጋራ አትጠቀሙ፤ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አትቀላቀሉ ተብሎ ምክር ተሰጥቶን ነበር በዚህም ምክንያት ከቤተሰቦቼ ጋር አልተቀላቀልኩም፤ ሰላምም ያልኳቸው በሩቁ ነው" ብሏል።

ነገር ግን በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ቤተሰቦቹን ጨምሮ ከእርሱ ጋር ንክኪ አላቸው ተባለው የተጠረጠሩ ከ70 በላይ ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው። እንዴት የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገለት የተጠየቀው ይህ ወጣት፣ በጉባ ኮሪቻ 12 ቀናት ከቆየ በኋላ ከእርሱ ጋር አብሮ የነበረ ጓደኛው ስለታመመ ወደ ጭሮ እንዲመጣ በጤና ጽህፈት ቤት ሰዎች እንደተደወለለትና እንደተመለሰ ይናገራል። ጭሮ ከደረሰ በኋላ ናሙና ተወስዶ ሲመረመር ቫይረሱ እንዳለበት እንደተነገረው ገልጿል።

በምዕረራብ ሐረርጌ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የሂርና ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አሊይ አደም፤ ወጣቱ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ ገልፀው ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 75 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል። "ምንም ህመም የለውም፤ የኮቪድ-19 ምልክቶች የሉትም፤ አልፎ አልፎ ሳል ብቻ ይታይበታል" ሲሉ ገልፀዋል።

የሂርና ሆስፒታል የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ሆኖ እየተደራጀ ሲሆን 100 አልጋዎችና ሁለት መካኒካል ቬንትሌተሮች አሉት። ሆስፒታሉ በአጠቃላይ 110 ሠራተኞች ሲኖሩት 67 የጤና ባለሙያዎች፣ 43 ደግሞ ተጨማሪ ህክምና ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው። ሆስፒታሉ በአንዴ እስከ 100 ሰው ማስተናገድ ሚችል ቢሆንም ያሉት ግን 60 አልጋዎች ናቸው።

@tikvahethiopiaBot @tikvahethiopia

Report Page