#BBC

#BBC


የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የግድያ ዛቻ እና የዘረኛ ንግግር ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ተናገሩ።

ዶ/ር ቴድሮስ "የግድያ ዛቻ ደርሶብኛል፤ እኔ ግን ግድ አይሰጠኝም" ሲሉ የተቃጣባቸውን ጥቃት ጠንከር ባሉ ቃላቶች ዛሬ በሰጡት መግለጫ አጣጥለዋል።

"ከሁለትና ከሦስት ወር በላይ ዘረኛ ጥቃቶች ተሰንዝረውብኛል። ጥቁር፣ ባርያ ተብያለሁ። እውነቱን ለመናገር እኔ በጥቁርነቴ እኮራለሁ። የሚባለው ነገርም ግድ አይሰጠኝም" ሲሉም አክለዋል።

ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ላለፉት ሦስት ወራት እሳቸው ላይ ያነጣጠሩ ዘለፋዎች እንደተሰሙ ገልጸዋል። ሆኖም ግን እሳቸውን የሚያሳዝናቸው አህጉሪቱ ላይ የተቃጡ ጥቃቶች እንደሆኑ አክለዋል። "መላው ጥቁር ሕዝብ እና መላው አፍሪካ ሲዘለፍ ግን አልታገስም፤ ያኔ ሰዎች መስመር እያለፉ ነው እላለሁ። እኔ የግድያ ዛቻ ሲደርስብኝ ምንም አልመሰለኝም፤ መልስም አልሰጠሁም። እንደ ማኅበረብ ሲሰድቡን ግን መታገስ የለብንም" ብለዋል።


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት፤ የዓለም ጤና ድርጅትን "በዋነኛነት በአሜሪካ ቢደጎምም፤ በጣም ለቻይና የወገነ ድርጅት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። ለድርጅቱ ድጋፍ ማድረጌን ላቆም እችላለሁ ሲሉም አስፈራርተዋል።

ይህንን ንግግር ተከትሎ የአፍሪካ መሪዎች ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምን ከትራምፕ እየተከላከሉ ነው።

የሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ፣ የናሚቢያው ፕሬዘዳንት ሀጌ ጄኒግቦ፣ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሞሳ ፋኪ ማሐማት ለዶ/ር ቴድሮስን ድጋፋቸው ከገለጹ መሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሞሳ ፋኪ ማሐማት ከዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ጎን ነኝ ማለታቸውን ተከትሎ፤ ፖል ካጋሜ "እኔም እስማማለሁ፤ ትችቱ ለዶ/ር ቴድሮስ፣ ለዓለም ጤና ድርጅት እና ለቻይና ነው ወይስ በጋራ ነው ጥቃት የተሰነዘረባቸው?" ብለዋል።

የናሚቢያው ፕሬዘዳንት ሀጌ ጄኒግቦ "የመላው ዓለም ትብብር አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት አብሮነትን ያሳዩ እውነተኛ መሪ" ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስን ገልጸዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የማደርገውን ድጋፍ አቋርጣለሁ ስለማለታቸው የተጠየቁት ደ/ር ቴድሮስ፤ "ኮሮናቫይረስን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የለብንም" ብለዋል። ሁሉም አካላት ቫይረሱን መከላከል ላይ ማተኮር እንጂ ኮሮናቫይረስን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ማዋል የለብንም ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ቴድሮስ አሜሪካ ለድርጅቱ ለምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ይቀጥላል ብለው እንደሚተማመኑም ገልጸዋል።

"በአገራችን ድንበር ውስጥ ብቻ ልንኖር አንችልም። ዓለም እጅግ እየጠበበች ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ አብሮነት ያስፈልገናል" ሲሉም ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page