#BBC

#BBC


በአማራ ክልል ሞረትና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሊሰጡ የመጡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የሐይማኖት ስብከት ለምን ያካሂዳሉ በሚል ጥቃት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ወደ ከተማዋ ያቀናው የሕክምና ቡድን 18 የውጪ አገር ዜጎች የተካተቱበት ከ200 በላይ አባላት ያሉት መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ ቦጋለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት የሆኑት መጋቢ ይልማ ሙሉጌታ በበኩላቸው በእነዋሪ ከተማ ለ20 ዓመት የነበረ ቤተ እምነት ላይ ጥቃትና ዘረፋ መፈፀሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መጋቢ ይልማ አክለውም ጥቃቱ የተፈፀመው በሐይማኖት አክራሪዎች ነው ያሉ ሲሆን ንብረቶች መዘረፋቸውን፣ ሦስት ሰዎች ተደብድበው ሆስፒታል እንደሚገኙ እና ቃጠሎ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የተደበደቡት የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን ብርሃኑ ተስፋ፣ አያሌው ማሞ እንዲሁም ተፈራ ሊያስብሸዋ የሚባሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አክራሪ ያሏቸው ጥቃት አድራሾች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥበቃ ደብድበው መሳሪያውን በመንጠቅ ቤተ እምነቱ ላይ ውድመት ማድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

ዋና ኢንስፔክተ ወጋየሁ እንዳሉት የሕክምና ቡድኑ በከተማዋ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የመጣው ባለፈው ቅዳሜ እለት ነው።

ቡድኑ ከእሁድ ጀምሮ በእነዋሪ ጤና ጣቢያ በመገኘት ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ለሕክምናው አገልግሎት ጎን ለጎን ከገጠር ቀበሌዎችና ከከተማው ለሚመጡ ተገልጋዮች የሐይማኖታዊ ስብከት ይደረግ እንደነበር ተገልጿል።

መጋቢ ይልማ በከተማዋ ለነጻ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መጡ የተባሉትን ቡድኖች በተመለከተ እንደተናገሩት ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትም ሆነ እውቅና እንደሌላቸው አስረድተዋል።

ቡድኑ የሕክምና አገልግሎቱን ሊሰጥ የመጣው ከእሁድ እስከ አርብ ድረስ ሲሆን ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን በመጣል ሐይማኖታዊ ስብከት ሲያካሄዱ እንደነበር ይናገራሉ።

የከተማው ነዋሪ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ተቃውሞ ነበር ያሉት በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳኜ አምታታው ሲሆኑ፤ የሕዝቡን ቅሬታ ይዘው ስብከቱን እንዳያደርጉ ለማነጋገር መሞከራቸውን አስታውሰዋል።

ዋና ኢንስፔክተሩ በበኩላቸው ሕዝቡ የሐይማኖት ስብከቱ በከተማዋ በሚገኘው የፕሮቴስታንት የእምነት ተቋም ቅጽር ግቢ ውስጥ ቢሰጥ ችግር የለብንም ማለቱን በማነሳት፤ ከጤና ጣቢያው ጎን ድንኳን ጥለው ስብከት ማካሄዳቸውና የሐይማኖት መጻህፍት ማደላቸው ቁጣን እንደቀሰቀሰ አመልክተዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ አክለውም ከእሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ አገልግሎቱ በሰላም ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ከገጠር ቀበሌዎችና ከከተማው ተቆጥተው የመጡ ወጣቶች በድንኳኑ እንዲሁም በሙሉ ወንጌል ቤተ እምነት ላይ የድንጋይ ድብደባና ቃጠሎ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልፀዋል።

አቶ ዳኜ በበኩላቸው "የተቆጣው ሕዝብ ከቁጥጥር ውጪ ነበር የሆነው" በማለት በወቅቱ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ይገልፃሉ።

ዋና ኢንስፔክተር ወጋየሁ አክለውም ዋነኛ ትኩረታችን የነጻ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ከተማችን የመጡ ባለሙያዎችና ባልደረቦቻቸው ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል ነበር፤ ያንንንም ማድረግ ችለናል በማለት ቡድኑን እስከ ደብረብርሃን ድረስ አጅበው በመሸኘት እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ።

በጥቃቱ የቤተክርስቲያኒቱ ማምለኪያ አዳራሽ እንዲሁም ስድስት ለቢሮነት የሚያገለግሉ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የገለፁት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት መጋቢ ይልማ ሙሉጌታ የተዘረፉባቸውና የተቃጠሉ ንብረቶች ግምት አንድ ሚሊየን ብር እንደሚደርስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

መጋቢ ይልማ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ቢናገሩም ዋና ኢንስፔክተሩ ወጋየሁ ግን አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ብቻ በድንጋይ መጎዳቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከንብረት አንጻር ስብከት ሲካሄድነበት የነበረ ድንኳን፣ እንግዶቹ ለመቆያ የሰሩት ካምፕና ልብስ እንዲሁም የሙሉ ወንጌል የቀድሞ ቢሮዎች መቃጠላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።

ዋና ኢንስፔክተሩ አክለውም እስከአሁን ድረስ በጉዳዩ ተጠርጥሮ የተያዘ አንድም ግለሰብ እንደሌለ በመግለጽ ክትትል እያደረጉና መረጃ እያሰባሰቡ መሆኑነን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የካቲት 25 እና 26/2012 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ጉራጌ ዞን ኮኪር ገደባኖ ጉታዘር ወረዳ፤ መሃል አምባ ከተማ የሚገኝ የሙሉ ወንጌል አጥቢያ ላይ ጥቃት መድረሱን መጋቢ ይልማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቤተክርስቲያኒቷ በአካባቢው ከ25 ዓመት በላይ የኖረች መሆኗን ጠቅሰው "በአካባቢው የሚገኙ የሐይማኖት አክራሪዎች ከምሽቱ 3፡30 ላይ አፍርሰዋታል" ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በወቅቱ በቦታው ላይ የነበሩ ምዕመናን ላይም ድብደባ መፈፀሙንና ሰባት ምዕመናን መታሰራቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ ባሻገርም ቀደም የነበረው የአምልኮ ቦታ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉንና የነበረው ንብረት መውደሙን ተናግረዋል።

ታስረው ከነበሩት ሰባት ምዕመናን መካከል ስድስቱ ትናንት መፈታታቸውን የሚናገሩት መጋቢ ይልማ፣ አንዱ ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በከተማው የሚገኙ ከ40 በላይ የቤተክርስቲያኒቷ አባላት ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ጎረቤት ወደ ሆነው የኦሮሚያ ክልል በመሸሽ በሀርቡ ጩልሌ ሙሉ ወንጌል ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ከተሰደዱት መካከል ሕፃናትና ሴቶች እንደሚገኙበት የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ አንዳንዶቸቹ ወደ ወልቂጤ ዞን መሰደዳቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

መጋቢ ይልማ አክለውም በጥቃቱ 500 ሺህ ብር በማውጣት እየተገነባ የነበረው አዲስ የማምለኪያ ስፍራ መውደሙን በመጥቀስ በቤተክርስቲያኒቷ ላይ በተለያየ ቦታዎች የሚደርሰውን ጥቃት መደጋገመ መምጣቱን አመልክተዋል።

#BBC


Report Page