#BBC

#BBC


የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ስጋት ምክንያት በአዲስ አበባ ሊካሄዱ ታቅደው የነበሩ ስብሰባዎች በመሰረዛቸው በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆቴሎች ገቢ ላይ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ተነገረ።

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ብስራት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ባይከሰትም በሌሎች አገራት ውስጥ ባለው ሁኔታ ሳቢያ ተጓዦች ቀደም ሲል የያዙትን እቅድ እየሰረዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለጊዜው ዝርዝር መረጃ ባይኖራቸውም የሚሰረዙት ከፍተኛ የቋማትና የግለሰብ መረሃግብሮች በአገሪቱና በሆቴሎች ገቢ ላይ የእራሳቸው የሆነ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው አመለክተዋል።

አቶ ቢኒያም እንደ አብነትም አዲስ አባባ ውስጥ ሚያዚያ ወር ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውና አንድ ሺህ ሰው እንደሚሳተፍበት የሚጠበቀው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ዓመታዊ ጉባኤ ተሰርዟል።

በዚህም እያንዳንዱ ተሳታፊ አራት ምሽቶችን አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚያሰልፍ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን አንድ ሰው በአማካይ በአንድ ምሽት 100 ዶላር የሚከፍል ቢሆን የ400 ሺህ ዶላር ገቢ ሳይገኝ እንደሚቀር ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አማካይነት ከመጋቢት 9 እስከ 15 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በከፍተኛ ሚኒስትሮች ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ጉባኤ አንዱ ነው።

ይህም በገንዘብ፣ በዕቅድና በምጣኔ ሃብታዊ ልማት ሚኒስትሮች አማካይነት የሚደረግና የ53ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጉባኤ አካል ነበር።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮም በኮሮናቫይረስ መስፋፋት ሳቢያ እየጨመረ በመጣው ስጋት ከአጋሮቹ ጋር በመመካከር ለጥንቃቄ ሲባል ተጨማሪያ ማስታወቂያ እስኪያወጣ ድረስ "ሁሉም ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለሌላ ጊዜ መተላላፋቸውን" ገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ አገራት ውስጥ በመስፋፋቱ ለሥራም ሆነ ለእረፍት ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች በሽታው ባስከተለው ስጋት ሳቢያ ዕቅዳቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል። በዚህም የሆቴል ዘርፉ ላይ የገቢ መቀነስ እንደሚያስከትል አቶ ቢያኒያም አመልክተዋል።

የበሽታው መስፋፋትና ስጋት በዚሁ ከቀጠለ ግንቦትና ሠኔ አካባቢ ፊፋ የሚያዘጋጀው ትልቅ መሰናዶ እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚ መድረክ ለመስከረም ወር የያዟቸው ትልልቅ ስብሰባዎችንም የመካሄድ ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባው እንደሚችል ጠቅሰዋል።

እስካሁን በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ባይከሰትም ከሚያሳጣው ገቢ በላይ አሳሳቢው ነገር የጤና ጉዳይ በመሆኑ ማኅበሩ በሆቴሎች የሚገኙ ሠራተኞች ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ስልጠናዎችንና የጥንቃቄ መመሪያዎችን እየሰጡ ነው ብለዋል።

ይህ በዓለም ዙሪያ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን በገደለው የኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት የታላላቅ ጉባኤዎች መሰረዝ እያጋጠመ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍረካ አገራት ውስጥ ጭምር ነው።

ከእነዚህም መካከል በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በመጪው ሳምንት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው 'ዘ ኔክስት አይንስታይን ፎረም' የተባለው ስብሰባ ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ተነግሯል።

መድረኩ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ከ79 አገራት በላይ በመጡና ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት እንደነበር ተገልጿል።

ሌላው ደግሞ የአፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ፎረም የተባለውና በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን ውስጥ በሚቀጥለው ሳምንት ለሁለት ቀናት ሊካሄድ የነበረው ስብሰባም እንደዚሁ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር ተደርጓል።

ምንጭ፦ BBC

Report Page