BBC

BBC


እነአቶ ጃዋር መሐመድ ከሦስት ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በአካል ቀረቡ



በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ የሚነገረው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ዛሬ ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት ለነበራቸው ቀጠሮ ሲቀርቡ አካላቸው ደክሞ እና ከስተው ታዩ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ የ24 ሰዎችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ዛሬ ጠዋት ላይ ቀጠሮ ይዞ ነበር። ከእነዚህ መካከል እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ሰዎች በፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር።

ይኹን እንጂ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ የረሃብ አድማ ከጀመሩ 33 ቀናት እንዳለፋቸው ለፍርድ ቤት ተናግረው፤ ደንበኞቻቸው አሁን ባሉበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት አይችሉም በማለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግም ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥ እንደማይቃወም ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

በዚህም መሠረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ችሎት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለመጋቢት 6/2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት እና ክስ ተመስርቶባቸው በእስር የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሸምሰዲን ጠሃ እና ሃምዛ አዳነ በፖለቲከኞች እና በቤተሰብ አባላቶቻቸው ላይ የሚደርሰውን እስር እና ወከባ በመቃወም የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ከ33 ቀናት በላይ እንዳስቆጠሩ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።


የተከሳሽ ጠበቆች ምን አሉ?

የተከሳሽ ጠበቆች "መንግሥት እና ሕግ ባለበት አገር ደብዳቤ ስናመላልስ ደንበኞቻችን ሕይወታቸው ሊያልፍብን ነው" በማለት የደንበኞቻቸው በሕይወት የመኖር መብት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ከደንበኞቻቸው መካከል አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ ሐምዛ አዳነን ጨምሮ አራት ተከሳሾች በጠና ታምመው እንደሚገኙ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ጠበቆች ለችሎቱ አስረድተዋል።


ተከሳሾች የሚገኙበት ሁኔታ

የቢቢሲ ሪፖርተር እንደተመለከተው ዛሬ ጋዜጠኞች ወደ ፍርድ ቤቱ ሲገቡ፤ አቶ በቀለ ገርባ ጭንቅላታቸውን በተከሳሽ አረፋት አቡበከር ላይ እንዲሁም እግራቸውን ደግሞ በአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ አድርገው በአግዳሚ ወንበር ላይ በጀርባቸው ተኝተው ነበር።

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐምዛ አዳነ ሰውነታቸው እጅጉን ከስቶ እና ጸጉራቸውን ተላጭተው ታይተዋል።

አቶ ሐምዛ አዳነ በሰዎች ድጋፍ ወደ ችሎቱ ሲገቡ የቢቢሲ ሪፖርተር ተመልክቷል።

ችሎቱ ሲጀመር አቶ በቀለ ገርባ በሰዎች ድጋፍ በጀርባቸው ተኝተው ከነበሩበት አግዳሚ ወንበር ተነስተው ተቀምጠዋል።

የተከሳሽ ቤተሰብ አባላት መካከል አንዳንዶቹ በችሎት ውስጥ ሲያለቅሱ ሪፖርተራችን ተመልክቷል።

እነ አቶ ጃዋር ለመጨረሻ ጊዜ ጋዜጠኞች እና ታዳሚዎች በተገኙበት በፍርድ ቤት ቀርበው የታዩት ጥር 27/2013 ዓ.ም ነበር። በዕለቱ የችሎት ውሎውን ለመዘገብ እና ለመከታተል በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሠራተኞች ተፈትሸው ወደ ችሎቱ ከገቡ በኋላ በጸጥታ አስከባሪዎች ከችሎቱ እንዲወጡ ተደርገው ነበር።

'የደረሰብን ክፍት ከፍተኛ ነው'



Report Page