BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

ያስቀመጡትን ዕቃ እየረሱ ተቸግረዋል? ቁልፍ፣ ስልክ፣ ቦርሳ፣ . . . እንደዋዛ እንዳስቀመጡት ረስተው የወጡበትንና የተቸገሩበትን ጊዜ ያስታውሱታል? የረሱትን ዕቃ ለማምጣት ወደ ቤትዎ አሊያም ወደ ሥራ ቦታዎ ምን ያህል ጊዜ ተመላልሰዋል?

ሕፃን ልጆችዎ ለጨዋታ በወጡበት ከዐይንዎ ተሰውረው ሲባዝኑ አልደነገጡም? "ሁለተኛ እነዚህን ልጆች ወደ ሕዝብ መዝናኛ ይዤ አልወጣም" ብለው አልዛቱም?

ለአዕምሮ እድገት ውስንነት የተጋለጡ ልጆችዎ አሊያም ቤተሰብዎ ከዕይታዎ እየተሰወሩ ተቸግረዋል? አዎ ምን አልባትም ለቁጥር የሚታክት ጊዜ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ወጣት ፍቅርተ ሙሉዬ እና ጓደኛዋ ይህ ችግር የማኅበረሰብ ችግር ነው በማለት መላ ዘይደዋል።

ፍቅርተ ሙሉዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ናት። የምትማረውን የትምህርት ዘርፍ ገና ያልመረጠች ቢሆንም የኮምፒዩተር ሳይንስ አጥንታ እንደ ሰው የሚያስብ ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ [አርተፊሻል ኒዩራል ኔትወርክ] ላይ መስራት የወደፊት ህልሟ ነው።

ፍቅርተ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በባህር ዳር ከተማ ነው የተከታተለችው። በትምህርቷ የደረጃ ተማሪ እንደነበረች የምትናገረው ወጣቷ፤ እዚያው ባህር ዳር በሚገኘው ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ማበልፀጊያ ማዕከል (STEM CENTER) ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘች፡፡

ማዕከሉ የ8ኛ ክፍል ውጤት ላይ ተመስርቶ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚመርጥ ሲሆን ዕድሉን የሚሰጠው የመግቢያ ፈተናውን ለሚያልፉ ተማሪዎች ነው።

ፍቅርተም ይህንን አጋጣሚ ያገኘችው ተቋሙ ያወጣውን ማስታወቂያ በመከታተል ነው። በማስታወቂያው መሠረት የተጠየቀውን መሥፈርት አሟልታ፤ ይህንን መልካም ዕድል የራሳቸው ካደረጉ ተማሪዎች መካከል አንዷ ሆነች። እርሷ እንደምትለው በወቅቱ ማዕከሉን የተቀላቀሉት 100 የሚሆኑ ተማሪዎች ነበሩ።

እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉትም እዚያው ነው።

ለመደበኛ ትምህርታቸውንም ቤተ ሙከራዎችን በተለይ የተግባር ሥራዎችን የሚጠይቁ ትምህርቶችን ይማሩበታል። ትምህርቱም በዩኒቨርሲቲ መምህራን ይሰጣል።

ማዕከሉ ውስጥ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የተግባር ልምምዶችንም ይወስዳሉ።

ታዲያ ለፈጠራ ሥራና ለቴክኖሎጂ ፍላጎት የነበራት ፍቅርተ፤ በማዕከሉ ውስጥ በነበራት ቆይታ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። በተለይ በየዓመቱ ለወላጆች በዓል በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ የፈጠራ ሥራዎቿን ታቀርብ ነበር።

ትኩረቷ ወደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሳያዘነብል በፊት በኬሚስትሪ እና ሌሎች የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ፍላጎት ነበራት።

ከዚህ ቀደም ምንም የሳይንስና ቴክኖሎጅ ክህሎቷን የምታዳብርበት አጋጣሚው እንዳልነበራት የምትናገረው ፍቅርተ፤ ይህንን ዕድል ካገኘች በኋላ ግን በሚሰጣቸው ትምህርትና እገዛ ፍላጎቱ እያደረባት መጣ።

ውድድሮች

በትምህርት ቤታቸው በተሳተፈችበት የመጀመሪያ ውድድሯ ላይ ሽቶ በመሥራት አሸናፊ ሆና ሽልማት ተበርክቶላታል። በግቢ ውስጥ የነበሩ የብርቱካን፣ የናና እንዲሁም የጤና አዳም ቅጠሎችን በመጠቀም ነበር ሽቶ የሠራችው። ያኔ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበረች።

ፈጠራዋንም በወላጆች በዓል ዝግጅት ላይ አቀረበች። ፍቅርተ ሽቶዎቹን እያርከፈከፈች፤ እርሷም እየተቀባች በመዓዛው እንግዶችን አስደምማለች። በጊዜው የሞባይል ስልክ ሽልማትም ተበርክቶላታል።

የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለችም እንዲሁ ከጓደኞቿ ጋር ሆና አንድ ፕሮጀክት ሠሩ። ፕሮጀክቱ የአልኮል መጠጦችን አልኮል አልባ ማድረግና በተቃራኒው አልኮል አልባ መጠጦችን ደግሞ ወደ አልኮል መጠጥነት መቀየር ነበር።

ኮካን ወደ ወይን፤ ወይንን ወደ ኮካ እንደማለት።

ፍቅርተ የፈጠራ ሥራው ባዮሎጂ መምህራቸው የተደሰተበት እንደነበርም ታስታውሳለች። የፈጠራ ሙከራዎቿ በዚህ መልኩ እየተቃኘ ቆይቶ 11ኛ ክፍል ላይ እያለች የአይኮግላብስ ወድድር ወደ ማዕከሉ መጣ። የሶልቭ አይቲ' ማስታወቂያ ፖስተሮችም ተለጥፈው ነበር።

ውድድሩ ከ18 ዓመት በላይ ያሉ ወጣቶችን የሚያሳትፍ ቢሆንም ያኔ እርሷ 18 ዓመት አልሞላትም ነበር። ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራትም እድሜ ገደባት። መስፈርቱን የሚያሟሉ ጓደኞቿ ግን ተመዘገቡ። በሥልጠናው ወቅት ከአዳራሹ ደጅ ላይ ተቀመጠች።

ገለፃውን ከሚሰጡት መካከል ቤተልሔም ደሴ ከዚህ በፊት 'ፕሮግራሚንግ' ስላሰለጠነቻት እና ፍላጎቷን ታውቅ ስለነበር፤ ምናልባትም በቀጣዩ ዓመት እንድትሳተፍ ተስፋ ለመስጠት ብላ ገብታ ዝግጅቱን እንድትመለከት አደረገቻት።

በኦሬንቴሽኑ ላይ የፈጠራ ሃሳብ እንዲሰነዝሩ ተጠየቁ ሃሳብ መጣላቸው። በደንብ አሰቡበት። ሃሳቡም በጣም ተወደደ- አስተዋሽ መሣሪያ- 'ሃሎ ሪንማይንደር'።

'ሃሎ ሪንማይንደር'

ቀደም ብለው ፕሮጀክቱን ከመጠንሰሳቸው በፊት መጠይቅ አዘጋጅተው ነበር። በመጠይቁ ከተካተቱት 200 ሰዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕቃቸውን ይረሳሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከመርሳታቸውም በላይ ለችግራቸው ምንም ዓይነት መፍትሄ ያላገኙ ሰዎች ናቸው።

Image copyrightFIKRTE MULUYE
አጭር የምስል መግለጫየ'ሃሎ ሪማይንደር' [አስታዋሽ መሣሪያ] የተወሰኑ ሞዴሎች

የመርሳት ህመም ከዕድሜ ጋር ተያያዥነት ቢኖረውም፤ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙት ሰዎች መጠኑ ቢለያይም ችግሩ ያጋጥማቸዋል።

'ሃሎ ሪንማይንደር'፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ቁልፍ ረስቶ ቢሄድ ወደ ስልክ መልዕክት የሚልክ መሣሪያ ነው። መሣሪያው በብሉቱዝ የተገናኘ ስለሆነ ምናልባት ከቤትዎ ግቢ ሳይወጡ ሊደርስዎት ይችላል።

የሰው ልጅ የሚረሳቸው በጣም ብዙ ነገሮች አሉ። ስልክ፣ ቦርሳ፣ ፍላሽ ዲስክ፣ ቁልፍ፣ እንዲሁም የመርሳት በሽታ [አልዛይመር] የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎችም ልጃቸውን እስከ መርሳት ይደርሳሉ።

ይህ ሁኔታ የሚኣጋትመው የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ልጆች ራሳቸው በጨዋታ ቦታ፣ በሕዝብ ቦታዎች ድንገት ሊሰወሩ ይችላሉ።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት የፍቅርተና የጓደኛዋ ናትናኤል ቢተው ፕሮጀክት መፍትሔ ሆኖ ነበር የቀረበው። መሳሪያው ቁልፍ፣ የፀጉር ጌጥ፣ ቦርሳ፣ ጫማ፣ ቀበቶ ላይ የሚለጠፍ ወይም የሚንጠለጠል ነው።

ከዚያም ስልክ ላይ በሚጫን መተግበሪያ አማካኝነት በብሉቱዝ እንዲናበቡ በማድረግ "ረስተዋል" የሚል መልዕክት እንዲላክልዎት ያስችላል።

በዚህ ፕሮጀክትም ከሁለት ዓመት በፊት የመጀመሪያው የሶልቪት ውድድር አሸናፊ ሆነዋል።

እነፍቅርተ በአገር አቀፍ በተካሄደው ውድድር ላይ የተሳተፉት በክልል ደረጃ 4ኛ ወጥተው ሲሆን በውድድሩ ሦስተኛ በመውጣት የ25 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል።

ስልክ ብንረሳስ?

በቀጣይ በሚሰሩት ፈጠራቸው ላይ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እየተጉ ነው። መልዕክቱን ወደ መሳሪያው ጭምር እንዲልክ የሚያስችል ፈጠራ ለማከል ያስባሉ።

የፈጠራ ሥራውን በብሉቱዝ መገናኛ እንዲሰራ ያደረግነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት ችግርና እጦት ታሳቢ በማድረግ ነው የምትለው ፍቅርተ፤ የኢንተርኔት አቅርቦቱ እንደልብ የሚገኝና ፈጣን ሲሆን በአቅጣጫ አመላካች (ጂፒኤስ) ይህንኑ የፈጠራ ሥራ እቃው ወይም ግለሰቡ ያለበትን ቦታ የሚያመላክት አድርጎ መስራት እንደሚቻል ትናገራለች።

ወደፊትም ይህንን አገልግሎት በማካተት ለመሥራት ሃሳቡ አላቸው።

"አሁን ላይ ሊያሰራን የሚችል ትልቅ ሃሳብ ይዘን ነው የተጠቀምነው" የምትለው ፍቅርተ፤ የፈጠራ ሥራውን ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ እያፈላለጉ እንደሚገኙ ገልፃልናለች።

ፍቅርተ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ የአንጎል ቀዶ ህክምና ዶክተር መሆን ትፈልግ ነበር። ስለ አእምሮ በጥልቀት የማወቅ ፍላጎቷ ከፍተኛ ነበር። ለዚህም 'ዘ ዶክተርስ' የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ፕሮግራምም አብዝታ ትመለከት ነበር። አንደ አጋጣሚ ወደ ቴክኖሎጂው እየተሳበች ስትመጣ በ'አርቲፊሻል ኒዩራል ኔትወርክ' ሃሳቡ በጣም እንደተማረከች ትናገራለች።

አሁን ላይ የሕይወት ግቧ የአርተፊሻል ኢንተሌጀንስ ዴቨሎፐር መሆን ነው የምትፈልገው። በመሆኑም የሚያስፈልገውን ትምህርት በመማር አርተፊሻል ኒዩራል ኔትወርክ ላይ መሥራት ትፈልጋለች።

ናትናኤል ደግሞ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረ ሲሆን አሁን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው።

ስቴም ሶሳይቲ ምንድን ነው?

ስቴም ማዕከል በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ትኩረት በማድረግ ሥልጠና እና ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ነው። ተቋሙ እንደሚለው እነዚህ የትምህርት ዘርፎች ለአንድ ተማሪ ውጤታማ መሆን አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ሳይሆን አሁን ካለው እውናዊ ዓለም ጋር ቅርበት ስላላቸው ነው።

ዓላማውም በእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ያለውን እውቀት ማሳደግ እና በዩኒቨርሲቲ ለሚኖራቸው ትምህርት በጎ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው።

ማዕከሉ በዘርፉ ላይ ፈጣሪ የሆኑ አሊያም የተለየ አስተሳስበ ላላቸው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ትኩረቱ በትምህርት ቤቶች፣ በማኅበረሰቡ፣ ሥራ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ግንኙነት መፍጠር ነው።

ትምህርቱን ከአንደኛ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ እና በመሰናዶ ትምህርት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎችም ይሰጣል።

Report Page