BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የህዳሴው ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሆኗል ተባለ

በሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የቆየው የህዳሴ ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ መሄዱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

እኚህ ምንጫችን ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን በመጠቆም አሁን ላይ ጉዳዩ "4 ለ 1" ሆኗል በማለት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በግድቡ ዙሪያ እጃቸውን እንዲያስገቡ መፈቀዱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት እንደሆነ እኚህ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከሁለት ቀናት በፊት ተደራዳሪ ቡድኑ ''በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከረ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል'' ብለው ነበር።

Twitter post BY@fitsumaregaa
"ቡድኑ በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከረ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል::
ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን: በአባይ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም!"

ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት የሰነዱ አብዛኛው ክፍል የቀረበው በአሜሪካ በመሆኑ፤ ትኩረቱም ስለ ግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በመሆን ፈንታ፤ "ማን ምን ያህል የውሃ ድርሻ ይኑረው? የሚለው ላይ የሚያተኩር በመሆኑ" ከስምምነት መድረስ እንዳልተቻለ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት እኚህ ባለሙያ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አክለውም በግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂ ቡድን አሁንም አሜሪካ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ በውሃ ክፍፍል ላይ ለመነጋገር እንደ አገር ዝግጁ አይደለንም፤ የድርድሩ አላማም ይህ አይደለም ብለውናል።

እሳቸው እንደሚሉት ከግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ በድርቅ፣ በረዥም ጊዜ ድርቅ እና በተከታታይ ድርቅ በሚሉት በሰነዱ ላይ በሰፈሩት ቃላቶች ትርጓሜ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ስለዚህም የኢትዮጵያ የህግ አርቃቂች በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሰነዱ ላይ የሰፈሩ በርካታ ነጥቦችን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስቀመጥ ተገድደዋል።

"ትልቁ ነገር ሰነዱ የውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። ወደ አሜሪካ የሄደው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ቡድንም በዚህ ላይ [የውሃ ድርሻ ክፍፍል] ለመነጋገር ስልጣን አልተሰጠውም። ስለ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከአስሩም የተፋሰሱ አገራት ጋር ነው መነጋገር ያለባት" ይላሉ።

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍን ፈርማ ያፀደቀች አገር መሆኗን እና ይህ ስምምነት ሳይጣስ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ባሉበት መነጋገር እንደሚገባት ያስታውሳሉ።

ታዛቢ ወደ አደራዳሪ

ሶስቱ አገራት በሚያደርጉት ድርድር ላይ የሶስተኛ አካል ጣልቃ መግባት ይኖርበታል ብላ ሃሳብ ያቀረበችው ግብጽ መሆኗ ይታወቃል። ፕሬዝደንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ታሸማግለን ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ኢትዮጵያ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን እንደማትቀበል ገልጻ ነበር። ለዚህም እንደምክንያትነት ያስቀመጠችው በሶስቱ አገራት የተደረሱ ''አበረታች'' ስምምነቶችን ያፈርሳል እንዲሁም ሶስቱ አገራት እአአ 2015 ላይ የፈረሙት የመርህ ስምምነትም ይጥሳል የሚል ነበር።

የኋላ ኋላ ግን ዓለም ባንክ እና አሜሪካ በሶስቱ አገራት መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው ይሳተፋሉ ሲባል ቆየ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጥር 25 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ የአሜሪካ መንግሥት እና ዓለም ባንክ 'ለማደራደር' ጥያቄ አቅርበው 'ሲያደራድሩ' ቆይተዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ "ለአሜሪካ እና ዓለም ባንክ ምስጋና ማቅረብ የሚያስፈልገው፤ በሚያውቁን እና አቅም ባላቸው ፊት ስንነጋገር መስማማት ጀምረናል" ሲሉም ተደምጠዋል።

እኚህ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚሉትም የአዲስ አበባ የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ በታዛቢነት ተቀመጡ፣ ካይሮ ላይ በታዛቢነት ቀጥለው ሱዳን ካርቱም ላይ ግን አደራዳሪ ሆኑ። ከዚያም ተመልሰው አዲስ አበባ ላይ አደራዳሪ መሆናቸውን ቀጠሉ።

"አሁን እኮ ዋሽንግተን ላይ የሕግ እና የቴክኒክ ቡድኑ ተገኝቶ፤ ሰነድ ቀርቦ ግልፅ ድርድር ነው እየተካሄደ ያለው" በማለት ያስረግጣሉ።

እነዚህ አካላት ከታዛቢነት ራሳቸውን ወደ አደራዳሪነት ከማሸጋገራቸውም በላይ ኢትዮጵያ ላይ "ከፍተኛ ጫና ማሳደርና ማስፈራራትም ደረጃ ደርሰዋል" ይላሉ ባለሙያው።

እርሳቸው እንደሚሉት አሜሪካና አለም ባንክ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል የሚነሱ ሃሳቦችን ለመቀበል በፍጽም ፍላጎት አያሳዩም። ይልቁንም እየተቀበሉ ያለው የግብፅና የሱዳንን ሃሳብ ብቻ ነው።

በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለራሷ ጥቅም ስትል ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ የነበረችው ሱዳን አቋሟን ቀይራ ከግብፅ ጎን መሰለፏንም ያረጋግጣሉ።

እሳቸው እንደሚያብራሩት በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት የምትፈልገው ሱዳን ይህን ፍላጎቷን ይዛ ስትመጣ አሜሪካ በበኩሏ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።

ምናልባትም የሚሉት እኚህ ምንጭ ከትናንት በስቲያ እንደተሰማው የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አል-በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ መሰጠት ሱዳን ያሟላችው አንድ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ከግብፅ ጎን መቆም ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ይህንንም ሱዳን እየፈፀመች ነው።

"ሶስተኛ ወገን ማስገባት ካስከፈለው ከባድ ዋጋ አንዱ ይሄ ነው" በማለት ድርድሩ ለኢትዮጵያ አጣብቂኝ መንገድ ላይ እንዳለ ይገልፃሉ።

አሜሪካ ለግብጽ ለምን ወገነች?

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ሰላም ለብልጽግና [ፒስ ቱ ፕሮስፔሪቲ] የተሰኘውን የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይህ የትራምፕ እቅድ እየሩሳሌም ያልተከፋፈለች የእስራኤል መዲና ትሆናለች ከማለቱም ባሻገር ፍሌስጤማውያን እና የተቀረው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕገ-ወጥ የሚለውን የእስራኤልን የዌስት ባንክ ሰፈራ እውቅና ይሰጣል።

ይህ የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ በፍልስጤማውያን ወዲያው ውድቅ የተደረገ ሲሆን እንደ ኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ የሰላም እቅዱን በይፋ ከተቃወሙት አገራት መካከል ይገኙበታል።

ቀላል የማይባሉ የአረቡ ዓለም አገራትም የትራምፕን የሰላም እቅድ በጥርጣሬ ዕይን መመልከታቸው አልቀረም። ታዲያ በአረቡ ዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነችው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ፤ የትራምፕ ዕቅድ በአረቡ አገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የሆነ የራሷን አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች።

እኚህ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚሉት፤ የፕሬዝደንት ትራምፕ እቅድ እንዲሰምር ግብጽ የበኩሏን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች።

ሱዳን እና እስራኤል

ለእስራኤል እውቅና ከማይሰጡ የአረብ ሊግ አባል አገራት መካከል ሱዳን አንዷ እና ተጠቃሽ ነች።

ሁለቱ አገራት ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግነኙነት የላቸውም።

እአአ 1967 የአረብ አገራት ያካሄዱት ታሪካዊ ስብሰባ ይታወሳል። በሱዳን ካርቱም በተካሄደው በዚህ ስብሰባ የአረብ አገራቱ 'ሶስቱ እምቢታዎች' ["Three No's"] ተብሎ የሚታወቀውን በእስራኤል ላይ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀው ነበር።

ለእስራኤል እውቅና አለመስጠት፣ ከእስራኤል ጋር ከስምምነት አለመድረስ እና ከእስራኤል ጋር አለመደራደር።

ዛሬም ድረስ በርካታ የአረብ ሊግ አባል አገራት ለእስራኤል እውቅና አልሰጡም። ከእነዚህም መካከል ሱዳን አንዷ ነች።

ከአንድ ሳምንት በፊት ግን ታሪካዊ በተባለ ሁኔታ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ካውንስል ሰብሳቢ አብድል ፈታህ አል-ቡረሃን በኡጋንዳ ኢንቲቤ ተገናኝተው ነበር።

ሁለቱ መሪዎች ለሰዓታት ከተነጋገሩ በኋላ ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ኔታኒያሁ ከውይይቱ በኋላ ሱዳን አዲስ እና አዎንታዊ ወደሆነ አቅጣጫ እያመራች ነው ማለታቸውን የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የእስራኤል ወዳጅ የሆኑት ትራምፕ፤ የኔታኒያሁ አገር በመካከለኛው ምስራቅ እና በአረብ ሊግ አባል አገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራት ይሻሉ።

ሱዳን ይህንን የአሜሪካንን ፍላጎትን ማሳካት የምትችል ከሆነ በግድቡ ድርድር ዙሪያ ያላት ፍላጎት ሊጠበቅላት እንደሚችል ይታመናል።

ለቢቢሲ ምልከታቸውን የሰጡት ባለሙያ እንደሚሉት ደግሞ፤ በግድቡ ድርድር ዙሪያ ሱዳን ከግብጽ ጋር አብራ የምትቆም ከሆነ፤ ተጥሎባት የሚገኘውን ማዕቀብ ሊነሳላት እንደሚችል ይጠቁማሉ።

የሱዳን ከግብጽ ጎን መቆም ማለት፤ የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ እንዲተገበር፣ የአረብ ሊግ አባላት በእስራኤል ላይ ያላቸውን አቋም ማለሳለስ ማለት ሊሆን ይችላል ይላሉ።

አሜሪካ ዋና ዓላማዋ ሶሰቱን አገራት ማስማማትም ሳይሆን የራሷን እና የእስራኤልን ፍላጎት ማሳካት ዋነኛ ግቧ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በዚህ ከባድ ድርድር ውስጥ በኢትዮጵያ በኩል መታለፍ የሌለበት መስመር የቱ ነው? ለባለሙያው ያቀረብነው ጥያቄ ነበር።

"እየተሄደበት ያለው መንገድ በሙሉ አደገኛ ነው" በማለት ድሮም ስለ ውሃ ክፍፍል ኢትዮጵያ ለብቻዋ ከግብፅና ሱዳን ጋር ድርድር አላደርግም ያለችው ለሁለት ጫና ያሳድሩብኛል በሚል ፍራቻ እንደነበር ያስታውሳሉ።

"አሁን ግን ብሶ አራት ለአንድ ሆኗል" በማለት ግብፅ፣ ሱዳን፣ አሜሪካና አለም ባንክ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ደግሞ በሌላ ወገን አጣብቂኝ ውስጥ መውደቋን ያስረዳሉ።

በጫና ውስጥ የሚደረግ ስምምነት አለም አቀፍ ተቀባይነት እንደማይኖረው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስምምነት ላይ መድረስ ቢቻል እንኳ በኢትዮጵያ በኩል በቀጣይ የሚመጡ መንግሥታትና ትውልድ የሚቀበሉት ነገር ስለማይሆን ነገሩ ወደ ፊት አገራቱን የባሰ ግጭት ውስጥ የሚከት ሊሆን እንደሚችልም ምልከታቸውን ያስቀምጣሉ ባለሙያው።

በኢትዮጵያ በኩል አሁን መወሰድ ያለበት እርምጃ ምን መሆን አለበት? ለሚለው ጥያቄያችን "አሁን ያለውን ሂደት መቆም ያለበት ይመስለኛል።

ወደ ኋላ ተመልሶ ተመካክሮና ነገሮችን አጢኖ ሁሉንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነገር ላይ መስራት [የተሻለ] ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገሮች በ2015 አገራቱ በተፈረሙት 'ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ' ስምምነት መሰረት መቀጠል አለባቸው ይላሉ። ስምምነቱ አገራቱ መመሪያ አዘጋጅተው በግድቡ ውሃ አያያዝና አለቃቅ ላይ ከስምምነት መድረስ እንደሚያዋጣ ያትታል።

ከዚያ አንፃር አሁን እየተደረገ ያለው ድርድር ትኩረቱን ስቶ ከግድቡ ውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ወደ የውሃ ድርሻ ክፍፍል የሄደ እንደሆነ ያስረግጣሉ ባለሙያው።

የኢትዮጵያ መሪዎች ምን ይላሉ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት ሶስቱ አገራት የመጨረሻ የተባለለትን ስምምነት ለመፈረም ከተዘጋጁ በኋላ፤ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ዝርዝር ዕይታ እና ውይይት ስለሚያስፈልገው እንዳይፈረም የሚል አቅጣጫ በመስጠታቸው ፊርማው እንዲዘገይ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ፕሬዝደንት ትራምፕ፣ የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ ፋይናንስ ሚንስትሩ ጋር በስልክ ተገናኝተው ረዘም ላለ ጊዜ መነጋገራቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከእርሳቸው በፊት አገሪቱን ይመሩ የነበሩ መሪዎች ጋርም ተመሳሳይ አቋም እንደነበራቸው በማስታወስ፤ የድርድሩ ውጤት ኢትዮጵያን የሚጎዳ እንዳይሆን እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

              Skip Twitter post by @seleshi_b_a

" The follow up meeting of Foreign and Water Affairs Ministers with the prescence of US Secretary of Treasury and World Bank is planned to commence on Wednesday. We, the Ethiopian team, continue to work vigilantly in advancing our national interest."

ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩት የውሃ መስኖ እና ኢንርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለም ከሁለት ቀናት በፊት "የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት ባማከለ መልኩ ጠንክረን እንሰራለን" ብለዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋም፤ ኢትዮጵያ "በአባይ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም!" ብለዋል።

የግብጹ አህራም ኦንላይን በበኩሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እንዳይፈረም አድርጌያለሁ ያሉትን ስምምነት ግብጽ መፈረሟን በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

አህራም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ፊርማቸውን ከማኖራቸው በፊት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ውይይት ማድረግን መርጠዋል ያለ ሲሆን፤ ሱዳንም በተመሳሳይ መልኩ ስምምነቱን እንዳልፈረመች ዘግቧል።

"በግድቡ አሞላል እና ውሃ አለቃቀቅ ላይ በካርቱም እና በካይሮ መካከል ጉልህ ልዩነት የለም" ሲል አህራም ጨምሮ ዘግቧል።

Report Page