#BBC

#BBC


በምዕራብ ኦሮሚያ የስልክና ኢንተርኔት ከተቋረጠ ቀናቶች ተቆጠሩ!

አጭር የምስል መግለጫ
በአሁኑ ወቅት በአራቱም የወለጋ ዞኖች፤ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ የኢንተርኔት አገልግሎት የለም

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ በሁለቱ የወለጋ ዞኖች (ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች) የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የምዕራብ ኦሮሚያ ዲስትሪክት ባልደረባ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት የኢንተርኔት አገልግሎቱ ከተቋረጠ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ "ሞባይል ዳታም ሆነ ዋይፋይ መስራት ካቆመ ቆይቷል። እዚህ ካለው ቴሌም ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" ብለዋል።

እኚህ ነዋሪ ጨምረው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ለከፍተኛ የትምህርት ዕድል ወደ ውጪ ሃገር መላክ ያለባቸው ማመልከቻ ጊዜ ሊያልፍባቸው ተቃርቧል።

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ሻምቡ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ አምስት ቀናት ማለፉን ጠቅሰው የስልክ አገልግሎትም ቢሆን አልፎ አልፎ እንጂ አብዛኛውን ጊዜ እንደማይሰራ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት በአካባቢው የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ማግኘት አልቻለም።

አጭር የምስል መግለጫ
ከኢንተርኔት በተጨማሪ የስልክ አገልግሎት የሌለባቸው ደግሞ ምዕራብ ወለጋና የቄለም ወለጋ ዞኖች ናቸው

ምዕራብ ኦሮሚያ በኮማንድ ፖስት ሥር መተዳደር ከጀመረ ወራት አልፈዋል። አካባቢው በኮማንድ ፖስት መተዳደር ከጀመረ ወዲህ የስልክ፣ ኢንተርኔትና የሰዎች እንቅስቃሴ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገደብ እንደሚጣል ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የስልክና የኢንትርኔት አገልግሎቶች ለምን እንደተቋረጡ ለማወቅ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ብንደውልም ምላሽ የሚሰጠን በማጣታችን ጥረታችን አልተሳካም። ይሁን እንጂ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኢትዮ ቴሌኮም ባልደረባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ "የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ የተደረገው በቴሌ ከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ ነው።"

በአሁኑ ወቅት በአራቱም የወለጋ ዞኖች ማለትም፤ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ የኢንተርኔት አገልግሎት የለም።

ከኢንተርኔት በተጨማሪ የስልክ አገልግሎት የሌለባቸው ደግሞ ምዕራብ ወለጋና የቄለም ወለጋ ዞኖች ናቸው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉን በዞኖቹ ውስጥ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ለምን እንደተቋረጠ ቢጠየቁም አሁን አስተያየት መስጠት እንደማይችሉና በቅርቡ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

(BBC AMHARIC)

Report Page