#BBC

#BBC


የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አስተዳደር በትግራኛ ቋንቋ ክፍል ላይ ያልተገባ ተጽእኖ እያሳደረ ነው ሲሉ የትግራኛ ክፍል ባልደረቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የትግራኛ ክፍል ባልደረቦች እንደሚሉት ከሆነ ትግራይን የተመለከተ ፖለቲካዊ ዘገባዎች እንዳይሰሩ በአስተዳደሉ ክልከላ ይደረጋል።

እንደምሳሌም ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ጉባኤ ሽፋን እንዳይሰጠው ማድረጉን የኮርፔሬሽኑ የትግረኛ ክፍል ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ይህ ክልከላ ሲያደርግ የመጀመርያው እንዳልሆነና ከዚህ ቀደምም 50 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈውንና 'የፌዴራሊዝም ስርዓት የማዳን ጉባኤ' የሚል ስም የተሰጠውን ኮንፈረንስ ሽፋን እንዳይሰጠው ተደርጓል ሲሉ እኚሁ የትግረኛ ክፍል ሠራተኞች ቅሬታቸውን ተናግረዋል።

ስማቸውን እንዲጠቀስ የማይሹት ባልደረቦች አዲሱ የለውጥ መንግሥት ከመጣ ወዲህ በትግርኛ ክፍል ላይ ሳንሱር እና ጫና ይደረጋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሤ ምትኩ ግን ከዚህ የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል።

''ከኮንፈረንሱ ጋር በተያያዘ ማንም እንደዚህ የከለከለ ሰው የለም። በአማርኛ የዜና እወጃ በኩል የፌዴራሊዝም ስርዓት የማዳን ጉባኤ የተባለውን ኮንፈረንስ መክፈቻውን ዘግበናል። የትግርኛውም ክፍል እንደዘገበው ተከታትያለሁ'' ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ውጪ የተደረገ ምንም አይነት ክልከላ አለመኖሩን ያስረዳሉ።

''ማንም ቢሆን ይህንን ክልከላ ያደረገ ሰው የለም። ነገር ግን ከኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን ጋር የሚጣረስ ነገር ሲኖር በደንብ ይታያል እንጂ አትዘግቡም ወይም ይህንን ብቻ ዘግቡ የሚባል ነገር የለም።'' ይላሉ።

"አሁን ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር የሚጣረስ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ ወይም የህዝቦችን ባህል፣ ማንነትና አብሮ መኖር አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲሆን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን መሰረት ውሳኔ እናስተላልፋለን።''

''ከዚህ ውጪ ግን የትግራይን ህዝብ የሚመለከት፣ የትራይን ህዝብ ጥቅም የሚመለከት፣ በክልሉ የሚሰሩ የልማት ስራዎች፣ ህዝቡ የሚያነሳቸው ችግሮችና ሌሎች መዘገብ ያለባቸው ጉዳዮች ሁሉ ሽፋን ያገኛሉ፤ በክልሉም ወኪል አልን።'' የሚሉት ዶ/ር ንጉሴ ናቸው።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው እንደተናገሩት፤ ይህን መሰል ቅሬታ እስካሁን ወደርሳቸው ጋር እንዳልመጣ እና ቅሬታ ያለው ሠራተኛ ካለ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል ጨምረው አስረድተዋል።

(BBC)

Report Page