#BBC

#BBC


ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራቅ ውስጥ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ በደረሰው ጥቃት ኢራን ዋጋዋን ታገኛለች ሲሉ ዛቱ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንደሚሉት ኢራቅ ውስጥ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ በደረሰው ጥቃት ኢራን እጇ አለበት።

በኢራቅ የሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ላይ በተናደዱ፣ በተቆጡ የተቃውሞ ሠልፈኞች ጥቃት የደረሰው በአሜሪካ የአየር ጥቃት የኢራቅ ወታደራዊ አባል መገደሉን ተከትሎ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአዲስ አመት ዋዜማ የትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ እንዳስታወቁት በኤምባሲው ላይ በደረሰው ውድመትና በጠፋው የሰው ሕይወት ምክንያት ኢራን "በትልቁ የእጇን ስራ ውጤት ታገኛለች" ብለዋል።

አክለውም "ይህ ማስጠንቀቂያ አይደለም፤ ዛቻ ነው" ሲል ስሜታቸውን ገልፀዋል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ማርክ ኤስፐር ወዲያውኑ እንደተናገሩት በቀጠናው 750 ወታደሮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።

"አሜሪካ ዜጎቿንና ጥቅሟን በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢሆን ትከላከላለች" ሲሉ በትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል።

ባለፈው እሁድ አሜሪካ በኢራንና ኢራቅ ድንበር ላይ ካደረሰችው የአየር ጥቃት ጋር ተያይዞ በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በተቆጡ የአገሬው ተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶበታል።

በምላሹ የአሜሪካ ወታደሮች ወደግቢው ለመግባት የሚሞክሩ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተጠቀሙ ሲሆን አካባቢው ከባድ ውጥረት ነግሶበታል ተብሏል።

ለግቢው ጠባቂዎች የተሠራ አንድ ማማ በተቃዋሚዎቹ በእሳት መቀጠሉም ታውቋል።

በባግዳድ የሆነው ምን ነበር?

ባለፈው እሁድ የአሜሪካ ወታደሮች ከካታይብ ሄዝቦላህ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የጦር ካምፖችን በአውሮፕላን ከደበደቡ በኋላ በትንሹ 25 ተዋጊዎች ሞተዋል።

አሜሪካ ካታይብ ሄዝቦላህ የተባለው ቡድን በአንድ የኢራቅ ኪርኩክ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ባለፈው አርብ ባደረሰው ጥቃት አንድ ወታደሬ ተገድሎብኛል ብላለች።

የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብዱል ማህዲ ''አሜሪካ የፈጸመችው የአየር ጥቃት የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚጥስና ከአሜሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንመረምረው ያስገድደናል'' ብለዋል።

የካታይብ ሄዝቦላህ አዛዥ አቡ ማህዲ አል ሙሃንዲስ በበኩሉ ቡድኑ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ኢራቅ የአሜሪካን እርምጃ ''ጥርት ያለ የሽብር ምሳሌ'' ነው ብላለች።

የትናንትናውን ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በአሜሪካው የአየር ጥቃት የሞቱ የቡድኑ አባላት የቀብር ስነ ሥርዓት በሚደረግበት ወቅት ነው።

ከፍተኛ ወታደራዊና የሚሊሻ ኃላፊዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሀዘንተኞች 'አረንጓዴው ክልል' ወደሚባለውና በርካታ ኢራቅ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች ወደሚገኙበት ቦታ አቅንተዋል።

ኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹ ወደ ክልሉ እንዲገቡ ሲፈቅዱላቸው በቀጥታ ያመሩትም ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ነበር።

ተቃዋሚዎቹ የካታይብ ሄዝቦላህ እና ሌሎች የሚሊሻ ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ የተስተዋለ ሲሆን አሜሪካ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዘር ነበር። በርካቶችም በዋናው በር ላይ ድንጋይ በመወርወር፣ የቪዲዮ ካሜራዎችን በመስበርና ለጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ማማዎችን በማጥቃት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

በመቀጠልም ሰልፈኞቹ ከዋናው በሮቹ መካከል አንደኛውን ሰብረው መግባት ችለዋል።

የፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደዘገበው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በሩን ሰብረው አምስት ሜትር ያህል እንደተጓዙ የአሜሪካ ወታደሮች በአስለቃሽ ጭስ በመታገዝ እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል።

ሁኔታው ሲከሰት በኤምባሲው ውስጥ ምን ያህል ሠራተኞች እንደነበሩ የታወቀ ነገር የለም። ማረጋገጥ ባይቻልም አምባሳደሩ ቀደም ብለው እንዲሸሹ ተደርገዋል የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።

(BBC)

Report Page