#AMMA

#AMMA


የኦሮሚያ እና የአፋር ክልል መንግስታት ለአማራ ክልል መንግስት አጋርነታቸውን ገለጹ፡፡ የክልል መንግስታት ርዕሰ መስተዳድሮች ትላንት ባህር ዳር በነበረው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት ላይ ታድመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የአጋርነት መልዕክት ‹‹ኢትዮጵያውያን የሚያዋጣን ለጋራ አንድነታችንና ለልማታችን በጋራ መትጋት ነው፤ ፈተናወች የጋራ ቤትን የሚያፈርሱ ከሆነ ማንም አይጠቀምበትም፤ የጋራ ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በአንድነት ልማቷን እና ሰላሟን አስጠብቆ ለማሻገር መትጋት ይገባል›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና ቀጣይነት የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ተገቢ መሆኑንም አቶ ሽመልስ አሳስበዋል፡፡

የጥፋት መንገድ እንዳይደገም፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት በአዙሪት ውስጥ ያኖራት በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንግድ ችግሮችን የመፍታት ችግር እንዲያበቃ ሁሉም በጋራ መታገል እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ እና መንግስትም ከአማራ ክልል መንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት መንግስታቸው እንደሚሰራ ያረጋገጡት ደግሞ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር አቶ ኡስማን ሙሃመድ ናቸው፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተው ድርጊት የአማራን ሕዝብ ስም እና ታሪክ የማይመጥን እኩይ ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባውም ነው የገለጹት፡፡ ድርጊቱን የማይረሳ ነገር ግን ሊደገም የማይገባ መሆኑ ታውቆ የቆየ አንድነትን አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የአፋር ክልል አጎራባች ከሆኑት ክልሎች መካከል ሰፊ የሆነ ቆዳ ስፋት የሚያዋስነው የአማራ ክልል ነው ያሉት አቶ ኡስማን ግንኙነቱም የተጠናከረ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በአፋር ክልል አስካሁን በማንነቱ ማንም አለመፈናቀሉንና ወደፊትም ማንም ሊፈናቀልበት እንደማይችል አረጋግጠዋል፡፡

ግንኙነቱም የበለጠ እንዲጠናከር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ የቆየ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ ሊጠናክር እንደሚገባም ጠይቀዋል፤ የአዴፓ አዲሱ አመራር የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት የተሰው አመራሮችን አደራ ከዳር ለማድረስ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ እና መንግስት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች እና ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንደ ቀድሞው ሁሉ ከጎኑ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል፡፡

Via #AMMA

Report Page