A.A

A.A

ታማኝ ዜና


የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ356 ሰዎች በላይ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ሲያልፍ ከ1,200 ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ 

በመረጃ መሠረት ከአደጋዎቹ መንስኤዎች መካከል የከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም ለመንገድ ደህንነት ፣ለትራፊክ አደጋ እና ለትራንስፖርት ፍሰቱ ማነቆ የሆኑትን ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በከተማዋ የትራፊክ አደጋን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል የተባለው የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር የሚገኙ የአንበሳ ከተማ አውቶብስ እና የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያው ገጥመው ያጠናቀቁ ሲሆን ሌሎች መንግስታዊ ተቋማትም በማስገጠም ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ 

በቀጣይም የአሰራር ሥርዓት መመሪያን በማዘጋጀትና የአፈጻጸም ሲስተሞችን በመዘርጋት የንግድ ትራንስፖርት እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ተግባራዊ የሚደረገው የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያውም የተቀናጀ የተሽከርካሪ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ጋር የተጣመረ ሆኖ እንደተሽከርካሪው ሁኔታ ወደ ሞተሩ የሚገባውን ነዳጅ ወይም አየር በመቀነስ የተሽከርካሪው ፍጥነት በሕግ ከተደነገገው በላይ እንዳይፈጥን የሚቆጣጠር ነው፡፡

መሣሪያው ከኔትዎርክ ውጪ (offline) ሆኖ የሚሰራና ኔትዎርክ ሲያገኝ መረጃዎቹን ወዲያውኑ የሚያስተላልፍና ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ሲታከልበት ከመረጃ ቋት (data base) ከያዘው ኮምፒውተር ጋር በመረጃ መረብ ተገናኝቶ የሚናበብና መረጃ የሚያስተላልፍ ቴክኖሎጂ ይኖረዋል፡፡ 

እንዲሁም አሽከርካሪው ከተቀመጠለት ፍጥነት በላይ ወይም በታች በሚያሽከረክርበት ጊዜ መሣሪያው ለአሽከርካሪው በምልክት ያስጠነቅቃል፤ መረጃውንም ወደ ኤጀንሲው መረጃ ማዕከል ያስተላልፋል፡፡

አሁን እየተዘጋጀ ያለው መመሪያ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠመው የፍጥነት መቆጣሪያ የመንገድ ፍጥነት ወሰን መመሪያ ቁጥር 1/2010 መነሻ በማድረግ በከተማ በሰዓት ከ15 እስከ 70 ኪ.ሜ አማካኝ ፍጥነት ወሰን ውስጥ የሚሽከረከር ሲሆን ከከተማ ውጪ ሲሽከረከር መሣሪያው ከሳተላይት በሚመጣለት መረጃ በሚፈቀድለት የፍጥነት ወሰን ራሱን ያስተካክላል ተብሏል፡፡

መመሪያው ሲጠናቀቅ ኤጀንሲው የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ አቅርበው የሚገጥሙና የራሳቸው የመቆጣጠሪያ ማዕከል ያላቸውን ድርጅቶች የሚያወዳደር ሲሆን በሚወጣው መስፈርት መሰረት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይሰጣል፣ ያድሳል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ይሰርዛል ተብሏል፡፡

ካሁን ቀደም የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያውን የመግጠም ፈቃድ ይሰጥ የነበረው የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ብቻ የነበረ ቢሆንም በቀጣይ ዓመት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በከተማ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ መሣሪያውን ለሚገጥሙ ድርጅቶች ፈቃድ ይሰጣል፡፡

በአጠቃላይ በ9 ወራት በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ጥፋት የተከሰሱና የተቀጡ አሽከርካሪዎች ብዛት 905,811 ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ያሽከረከሩ ናቸው፡፡

Report Page