#A

#A


1ኛ. ለአማራ ሕዝብ በሙሉ

የአማራ ህዝብ ቀደም ሲል ጀምሮ ለዘመናት የገጠሙንን በርካታ ፈተናዎች በጥበብና በማስተዋል አልፈናል፡፡ በዚህ ወቅት እየገጠሙን የሚገኙ ችግሮችንም ሆነ ውዥንብሮች እንደ ቀድሞው ሁሉ ጥበብን፣ ማስተዋልንና አርቆ አሳቢነትን በመላበስ የምንሻገራቸው ናቸው፡፡ የዚህ አይነት አሳዛኝ ክስተቶች ለጊዜው ቅስም ሰባሪ ቢሆኑም አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክሩታል እንጂ እንደማይፈታተኑት በጽኑ እናምናለን፡፡ አንድነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር የተሻለ ነገን መፍጠር እንደምንችልም ጥርጥር የለንም፡፡ ለዚህም መሳካት ሁላችንም የበኩላችንን ሚና ለመጫወት ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀላፊነት እንድንወጣ ጥሪ ስናቀርብ የምሁራን መማከክርት ጉባዔው የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ መከናወን ይገባቸዋል የሚላቸውን ጉዳዮች ነቅሶ አውጥቶ ከክልሉ መንግሰትና መሪ ፓርቲ እንዲሁም ከሌሎች የአማራ ህዝብን ጥቅምና መብት ለማሰከበር ከተደራጁ ፓረቲዎች ጋር በመተባበር ለመተግበር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ለህዝባችን እናስታውቃልን፡፡

2ኛ. ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ

እኛ ኢትዮጵያውያን በረጅሙ ታሪካችን በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚና በአጠቃላይ በቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብት አንዱ ካንዱ በማይለይበት ደረጃ ተሳስረንና ተጋምደን የኖርን፣ ለወደፊቱም የምንኖር ህዝብ ነን፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ካለው ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት፥ የመከባበርና የአንድነት እሴት ከሚንድ ከፋፋይ እና አፍራሽ ተግባር ሁላችንም በመታቀብ ልዩነቶቻችንን በአመክንዮአዊ ውይይትና በድርድር በመፍታት ለጋራ ሀገራችን በአንድነት እንድንሰራ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

3ኛ. ለአማራ ምሁራን

የአማራ ክልል በርካታ አቅሞች ያሏቸው ምሁራን ያሉት ቢሆንም ምሁራን ያለንን ዕውቀትና ክህሎት ለህዝባችን ዘላቂ ዕድገትና ብልጽግና እንድናውል የሚያስችል አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ አውድ ስላልነበረ የሚጠበቅብንን ድርሻ በተገቢው መንገድ ሳንወጣ ቆይተናል። የሰኔ 15ቱ ክስተትም የአማራ ምሁራን ዳር ይዞ ከመቆም ይልቅ ለሕዝባችን ያለብንን ኃላፊነት እንድናጤን የማንቂያ ደወል በመሆኑ አሁንም አልረፈደምና የተፈጠረውን መጥፎ አጋጣሚ ወደ መልካም እድል እንድንቀይረውና ህዝባችን አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድ ለማድረግ የማንንም ጥሪ ሳንጠብቅ፣ በማንምና በምንም ምክንያት ክፍተት ሳንፈጥር እንድንተባበርና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለህዝባችን እንድናድርግ ጥሪ እናስተላልፋለን። ለዚህም ምሁራን አንድነታችንን በማጠናከር ለማሕበረሰባችን አርዓያ ከመሆን ባሻገር ለችግሮች ሳይንሳዊ መፍትሄ አፈላላጊና አመንጪ በመሆን በክልላችንና በሀገራችን ማሕበራዊና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግተን ለመሥራት ቃል እንገባለን።

4ኛ. ለወጣቶች

የክልላችንና የሀገራችን ወጣቶች አሁን ለተገኘው አንጻራዊ የመናገርና የመወያየት ነፃነት ክቡር የሆነውን ህይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ ስለዚህ የተከፈለው ክቡር የሰው ህይወት በከንቱ እንዳይቀር የታየው የለወጥ ተስፋ ወደ እውነተኛ እና ዘላቂ ነፃነትና ልማት ለማሸጋገር የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ክልሉ ብሎም ሀገራችን እንዲረጋጋ የወጣቱ ስክነት፥ አስተዋይነት፥ መርህ ጠባቂነትና አመክንዮአዊነት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በተለይም ይህ ዘመን የወጣቱ ነው፤ የተሻለ ነገ የናንተ የወጣቶቹና የምታልሟቸው ውድ ልጆቻችሁ ነው። አያቶቻችሁና ቅድመአያቶቻችሁ በዓለም ስመ ጥርና ክቡር ሀገር ያወረሷችሁ ዛሬ እንደምናየው በማህበራዊ ሚዲያ የወሬ ጋጋታና ውዥንብር ሳይሆን በታላቅ ጥበብ፥ ሲያስፈልግም ምክንያታዊ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈላቸው ጭምር ነው።

የዛሬ ወጣቶች ከአያቶችና ቅድመአያቶች ጥበብ የሚያልቃቸውና ኃላፊነታቸውን እጥፍ ድርብ የሚያደርገው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ያስገኘዉን እዉቀትና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ትውልድ መሆናቸው ነው። የዓለምን የፖለቲካ ሂደት በጨለማ ዳስሰው ከሩቅ በመመርመር ታላቅ ሀገራዊ አቅምና አንድነት ከገነቡ የትናንት ጀግኖች ልጆች የምንማረውና ለወደፊቱም እርግጠኞች የምንሆነዉ በዚህ ክፍለ ዘመን ላይ የሚገኘዉ የዛሬ ወጣት በሰፈር የማሰብን እንቆቅልሽ እንደሚፈታ እና ዛሬን ተሻግሮ በተሻለ ክብር ነገን እንደሚያይ ነው፡፡ የሰከነ ውይይትና አመክንዮአዊነት እንዲሁም ከጎጠኝነትና ከሰፈርተኛነት የላቀ የሞራል ልዕልናና ሰብዓዊነት ብቸኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች በመሆናቸው የክልላችንና የሀገራችን ወጣቶች ይህንኑ ጠንቅቀዉ በመረዳት እንዲተገብሩ ጥሪ እናስተላልፋለን።

የምሁራን መማክርት ጉባዔዉ በክልላችንም ሆነ በሀገራችን በማንኛዉም ጊዜ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅና በርካታ ወደስራ ሊሰማራ የሚችል የወጣት ሀይል እንዳለ፥ ይህንም ሀይል ደግሞ ሰፋፊ የስራ መስኮች በመፍጠር ወደስራ በማስገባት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ስለዚህ የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴን ለመደገፍና ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት አዉንታዊ አስተዋጽዎ ለማበርከት ቃል እንገባለን።

5ኛ. ለፖለቲካ ፓርቲዎች

የህዝብን ጥቅም እና መሰረታዊ ጥያቄ ማዕከል አድርገው የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ፖለቲከኞች ከአካሄዳቸው/ከስልታቸው በሚመነጭ ልዩነት ምክንያት ህዝቡን በየጎራው ከፋፍለው በማሰለፍ እርስ በርስ እንዲጋጭ ከማድረግ እና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት ሊቆጠቡ ይገባል። በተለይም በአማራ ክልል ህዝብ ዙሪያ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እና አባላት የክልሉን ህዝብ በአካባቢና በጎጥ ከሚከፋፍል አደረጃጀትና ስነ ልቦና ግንባታ እንዲቆጠቡ እና ይልቁንም በአመክንዮ እና በሃሳብ ልእልና የሚያምን እና እንደ አያቶቹና ቅድም አያቶቹ ከራሱ ይልቅ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ትዉልድ ለመፍጠር የበኩለቸዉን እንዲሰሩ በጥብቅ እናሳስባለን። ከዚህም አልፈው የአማራን ህዝብ ጥቅምና መብት ለማስከበር ሲባል ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድ ላይ እንዲቆሙና የተፈጠረውን ሁለንተናዊ ችግር ለማስወገድ በጋራ እንዲሰሩም እንጠይቃለን፡፡ የምሁራን መማክርት ጉባዔዉ እንዲህ ዓይነት መድረኮችን ለማመቻቸት እና በሂደቱ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆኑን እየገለፅን ለተግባራዊነቱ ሁሉም ዓካላት ትብብር እንደምታደርጉ ሙሉ ተስፋ አለን።

6ኛ. ለሁሉም ማህበራዊ አንቂዎች (አክቲቪስቶች)

በክልላችንና በሀገራችን ነፃነትንና እኩልነትን ለማረጋገጥ በተደረገው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የፖለቲካና ማህበራዊ አንቂዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አሁንም በመጫወት ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ከዚህ በተጻራሪ የቆሙ በለውጥ እንቅስቃሴ ላይ አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ ጥቂት የማይባሉ አንቂዎች አሁን ለምንገኝበት ችግር አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ይገኛሉ። ስለዚህ ሁሉም አንቂዎች አፍራሽ ከሆነ ሚናቸው ተቆጥበው ሕዝብን በማረጋጋትና የሀገራችንን አንድነት በማስጠበቅ ላይ አተኩረው በመስራት ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።

7ኛ. ለሁሉም ብዙኀን መገናኛ፡

የዘመናዊ ብዙኀን መገናኛ ዓይነተኛ ባሕርይና ኃላፊነት ተራ አሉባልታን ከማሰራጨትና ሕዝብን ከሕዝብ ከሚያጋጩ ድርጊቶች በመቆጠብ መልካም ማሕበራዊ ትስስር፤ አብሮነትንና መተሳሰብን መገንባት በመሆኑ ብዙኀን መገናኛ በዕውነት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን በፍጹም የኃላፊነት መንፈስ ለህዝብ እንዲያደርሱ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ይህንን ኃላፊነታቸውን ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ እንዲወጡ እንጠይቃለን።

8ኛ. ለሃይማኖት አባቶች

በሀገራችን በተለይም የክልላችን የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች የሰከነና ስነምግባር የተላበሰ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ ላለፉት በርካታ ዘመናት ጉልህ ሚና ሲጫወቱ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የእምነት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች መልካም እሴቶችን በማጎልበት በዚህ ወቅት የገጠሙንን የስነምግባር መዛነፎችንና ይህን ተከትለው እየተስተዋሉ ያሉ ክልላዊና ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የበኩላችሁን ሚና እንትጫወቱ በትህትና እንጠይቃለን።

9ኛ. ለባለሀብቶች

ባለሀብቶች ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እና ለሀገራቸዉ ሀብት ፈጣሪ በመሆን በስራ ፈጠራና በሀገር ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ላይ የማይተካ አውንታዊ ሚና እንዳላቸዉ ይታመናል። በጥረት ሃብት ማፍራት፤ ያፈሩትን ሃብት ለትውልድ ጥቅም ማዋልና ማውረስ የሚቻለውም ሀገርና ህዝብ ሰላም ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ባለሀብቶች የህዝብን ጥበቃና ከለላ የሚያገኙት ደግሞ ስራ በመፍጠርና እሴት በመጨመር ለህዝብ ኑሮ መሻሻልና ለኢኮኖሚው እድገት ጉልህ ሚና ሲያበረክቱ ነው፡፡ በተጨማሪም ባለሀብቱ ስራ ፈጠራን እንደ ዋና ተግባሩ አይቶ ወጣቱ ከኢኮኖሚ መገለል ስሜት እንዲወጣና ትኩስ ጉልበቱን፣ ዕውቀቱንና ክህሎቱን ለልማት እንዲያውል በስፋትና ከምንጊዜዉም በተሻለ በኢንቨስትመንት እና ንግድ ተግባር ላይ እንዲሰማሩና ህዝባቸዉን እና ሀገራቸዉን እነዲያግዙ ጥሪ እናቀርባለን። በመንግስትም በኩል ሆነ በሌሎች የባለድርሻ አካላት የኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታዉ ከምንጊዜዉም በላይ የተሻለና ምቹ እንዲሆን እየጠየቅን፤ ለዚህም መሳካት የምታደርጉትን ጥረት የምሁራን መማክርት ጉባዔዉ እንደሚደግፍ እና አብሮዋችሁ እንደሚሰራ ቃል እንገባለን።

10ኛ. ለፀጥታ ሀይሎችና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፡-

የፀጥታና የመከላከያ ሃይላችን ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ቅድመ መከላከል ማድረግ፣ ከተፈጠረም በኋላ ቀውሱን ማብረድና ድጋሜ እንዳይፈጠር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም ክቡር የሆነው የሰው ልጅ አንድም ጥቃት እንዳይደርስበት ጥረት ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው የጸጥታና የመከላከያ ኃይል የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በክልሉ መንግሰት አመራር የተሰማራሃው የጸጥታ ሀይል ውስጣዊ አንድነትህን በማጠናከር የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በህዝብና መንግስት የተጣለብህን አደራ እንድትወጣ እንጠይቃለን፡፡ እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ የክልሉ ህዝብና መንግስት በሚጠይቁት ጊዜና ቦታ በመገኘት ሀገራዊ ሀላፊነታችሁን በአግባቡ እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡ የምሁራን መማክርት ጉባዔዉም ይህ ሰላም አስከባሪ ሀይል ለሀገሩ ሲል የሚከፍለዉን ከፍተኛ መስዋዕትነትና ዋጋ ከግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት ተገቢ የሆነና ከምንጊዜዉም የተሻለ ህዝባዊና አገራዊ ከበሬታ እና አድናቆት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን አዎንታዊ ስራ ለመስራት ቃል እንገባለን።

11ኛ. ለክልልና ፌደራል መንግሰታት

በክልላችንም ሆነ በሀገራችን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ መንግስት የሚጫወተው ሚና አይተኬ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና የዕለት ከዕለት ስራቸውን በነጻነት ተዘዋውረው እንዲያከናውኑ ማድረግ ይቻል ዘንድ ከሁሉም በላይ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ እና በክልሉ ውስጥ ላለዉ አለመረጋጋት ምክንያት የሆኑ የተጓደሉ የመስረተ ልማቶችን በማሙዋላት ፈጥኖ ወደ ልማት እንዲገባ እንጠይቃለን፡፡ እንዲሁም የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የሚወሰዱ የህግ የበላይነት ማሰከበር ስራወችም በምንም መልኩ ለተለየ የፖለቲካ ግብ ሳይውሉና የአማራ ህዝብና ግለሰቦችን የመደራጀት መብትን ሳይሸራርፉ እየተተገበሩ መሆናቸውን ለማረጋጋጥ መንግሰት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሀዝቧን ይባርክ፡፡

ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም

ባህርዳር

Report Page