a

a


የእፀገነት ሽሙጥ ቀመስ የመድረክ ወጎች

May 30, 2021

መምህርትና የጥበብ ሰው እፀገነት ከበደ በተለያዩ መድረኮች በምታቀርባቸው ሽሙጥ ቀመስ ወጎቿ ትታወቃለች። በሰራዎቿ ከታዳሚው ዘንድ የምታገኘው አድናቆት ከፍተኛ ቢሆንም የሚተቿት እንዳሉም ትናገራለች። እንደ እፀገነት የፅሁፎቿ ዓላማ ሁሉም ወደራሱ እንዲመለከት ቢሆንም፤ የራሱን ትርጉም ሰጥቶ መልዕክቱን ለአንድ ለተወሰነ አካል የሚገፋ ታዳሚ ብዙ ነው።

AC3DDD1C_2.mp3

ሥነ-ፅሁፍን የጀመረችው በልጅነት ዕድሜዋ ቢሆንም፤ ወደ መድረክ ብቅ ማለት የጀመረችው ግን የኮሌጅ ተማሪ እያለች ነው።ደራሲ መምህርት የወግ ፀሀፊና ገጣሚም ነች።በተለይም በተለያዩ መድረኮች በምታቀርባቸው የሚያዝናኑ ግን በማህበራዊና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሰላ ትችት ባላቸው እና የማህበረሰቡን ህፀፅ በሚነቅሱ  ወጎቿ ትታወቃለች። የዛሬዋ የመዝናኛ ዝግጅት እንግዳችን እፀገነት ከበደ። 

መምህርትና የጥበብ ሰው እፀገነት ከበደ «እንጎቻ» በሚል ርዕስ አጫጭር ታሪኮችን የያዘ የህፃናት መፅሀፍና ሲዲዎችን ከዚህ ቀደም ያሳተመች ሲሆን « ማለዳን መናፈቅ»በሚል ርዕስ ሁለተኛ መጽሀፏን ለአንባቢያን ለማድረስ በዝግጅት ላይ ነች።

Äthiopien Etsegenet Kebede Buchcover

በተለያዩ መድረኮች ከምታቀርባቸው ወጎች በተጨማሪ ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ ከተማም «ቃልና ዜማ» በሚል መድረክ የሥነ-ፅሁፍ ዝግጅቶችን ታዘጋጃለች። መድረክ ላይ በምታቀርባቸው ሽሙጥ ቀመስ ወጎቿ ከታዳሚው ዘንድ የምታገኘው አድናቆት ከፍተኛ ቢሆንም የሚተቿት እንዳሉም ትናገራለች። ነገር ግን ትላለች እፀገነት« በዚህ ዘመን እንደተከሰተ  እንደ አንድ ሰው የሚሰማኝን ስሜት በሚሰማኝ መንገድ ማውጣት ካልቻልኩ ምንድነው ፋይዳዉ?»ስትል ትጠይቃለች።

« እያንዳንዱ ሰው በዚያ ዘመን ሲፈጠር ዋጋ አለው።ዝም ብሎ ኖሮ ለመሞት አይደለም።»የምትለው ዕፀገነት፤ በዕለት ተዕለት ኑሮዋ የምትታዘባቸውን ነገሮች በወጎቿ በመዳሰስ ወደ መድረክ ይዞ መውጣት ያስደስታታል። «እያንዳንዱ ነገር ዋጋ ያስከፍላል። በነፃ የሚገኝ ነገር የለም። የምፈልገውን ለውጥ በሀገሬ  ማየት ከፈለኩኝ የሚከፈለውን ትንሽ ዋጋ መክፈል አለብኝ» በማለትም  በሙያዋ እንደ አንድ ዜጋ ለሀገሯ የበኩሏን ለማበርከት ወደ ኃላ እንደማትል ገልጻለች።

በሌላ በኩል የፅሁፎቿ ዓላማ  እንደማኅበረሰብ መታረም ያለበትን ፣እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን ነገር ለመጠቆም እና ግለሰቦችም ወደራሳቸው  እንዲመለከቱ ቢሆንም፤ለምታቀርባቸው ወጎች የራሱን ትርጉም በመስጠት መልዕክቱን ለአንድ ለተወሰነ አካል የሚገፋ ታዳሚ ብዙ መሆኑንም አጫውታናለች። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

Report Page