US HFAC

US HFAC


#Ethiopia : የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉዳይ ውሳኔ አሳልፏል።

ኮሚቴው ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ሁከት እና የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን ያወገዘ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች ግጭት እንዲያቆሙ ፣ ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እና ተዓማኒነት ያላቸው የግፍ እና ጭካኔ ድርጊቶች ክሶችን በተመለከተ ለገለልተኛ ምርመራዎች እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።

የውሳኔ ሃሳቡ ከተላለፈ በኋላ ካረን ባስ ባወጡት መግለጫ ፥ " እኔ ይህንን ውሳኔ የመራሁት በብሔር ፣ በፖለቲካ እና በታሪክ የተወሳሰበ ለዚህ ሁለገብ ግጭት ሰላማዊ ፣ የድርድር መፍትሄ ማየት ስለምፈልግ ነው" ብለዋል።

ባስ እኤአ በጥቅምት 2020 የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (TPLF) በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ግጭቱ መጀመሩን እና ግጭቱ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች መስፋቱን ገልፀዋል።

በድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይኖር ግጭቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት ፍራቻ አለኝ ብለዋል ባስ።

" H. Res 445 " የተሰኘው ይህ የውሳኔ ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁከት እንዲቆም ፤ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (TPLF) በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ ይጠይቃል።

ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ፣ ጾታዊ እና ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ፣ እጅግ የበዙ የመብት ጥሰቶችን እና ጭካኔዎችን የሚፈጽሙ ወታደሮችን ፣ አማፅያኖችን እና ሌሎች ተዋንያንን ያወግዛል። የኢትዮጵያ መንግስት ተአማኒነት ላላቸው የግፍ እና ጭካኔ ክሶች ነፃና ግልፅ ምርመራዎች እንዲተባበር ጥሪ አቅርቧል።

ከውሳኔ ሀሳቡ በተጨማሪ TPLF ህፃናትን ለውትድርና መጠቀም እንዲያቆም ፤ ከአማራ ክልልም በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ፤ ከOLA-ሸኔ ጋር ያለውን ጥምረትም እንዲያቆም ተጠይቋል።

ባስ ፥ የውሳኔ ሀሳቡ ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲኖር እንደሚጠይቅ በቀን ቢያንስ 100 የጭነት መኪናዎችን ወደ ትግራይ መላክ እንዳለበት የሚገልፅ ነው ብለዋል።

TPLF መራሾቹ ኃይሎች ጦርነት ለመቀጠል ሲሉ የጭነት መኪናዎችን ወይም የእርዳታ ዕቃዎችን ከመዝረፍ እንዲቆጠቡ እንደሚያሳስብም ተናግረዋል።

ባስ ፤ እሳቸው ባሉበት በካሊፎርኒያ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ እንዳሉ እና በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ሁሉንም ወገኖች ሀሳብ ለመስማት እንደሞከሩና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለግጭቱ አስተዋፅኦ በማድረግ ድርሻ እንዳላቸው እንደሚያውቁ ገልፀዋል፤ ባለድርሻ አካላቱ ለተኩስ አቁም እና ለድርድር ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ባስ ፤ ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ የለውም ያሉ ሲሆን ያለብሄራዊ መግባባት እና ውይይት የኢትዮጵያ ሁኔታ እየባሰ እንዳይሄድ ስጋታቸውን አጋርተዋል።

በተጨማሪም በአሜሪካ አስተዳደር ማዕቀብ የመጣል አደጋ ውስጥ መሆኗና ግጭቱ ከቀጠለ በአጎዋ ውስጥ የመሳተፍ እድሏ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።

ያንብቡ : https://bass.house.gov/media-center/press-releases/house-foreign-affairs-committee-passes-resolution-ethiopia

@tikvahethiopia

Report Page