Tarik Adugna

Tarik Adugna


ታስረው እንዲቀርቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የወጣባቸው የስራ ኃላፊ ሳይቀርቡ ቀሩ።


የፍርድ ቤት መጥሪያ ፈርመው ወስደው በቀጠሮ ቀን ሳይቀርቡ የቀሩት የአ/አ ቤቶች ኮርፖሬሽን ኃላፊ አቶ ሽመልስ ታምራት ታስረው እንዲቀርቡ ትናንት በነበረ ቀጠሮ ትዕዛዝ የወጣባቸው ቢሆንም ዛሬም ሳይቀርቡ ቀርተዋል።


በአ/አ ከተማ በሀምሌ 1ቀን 2014 ዓ/ም ከኮንዶሚኒዬም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ ዕጣው ተጭበርብሯል ተብሎ የአ/አ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን እና ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑትን አቶ አብርሀም ሰርሞሌን ጨምሮ በአጠቃላይ በ 11 ተከሳሾች ላይ በየደረጃው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።


ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውንና ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ገልጸው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዓቃቢህግ ምስክሮችን ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።


በዚህ መሰረት ዓቃቢህግ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ስርዓት ጋር ተያይዞ እንዲሁም ለምቷል የተባለው ሶፍትዌርን በሚመለከት የምስክር ጭብጥ ካስመዘገበ በኋላ በህዳር 22 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ፍርድ ቤቱ የዓቃቢህግ ምስክር ቃል መሰማት ጀምሯል።


በዚህ መልኩ ዛሬ የተሰማውን አንድ ምስክርን ጨምሮ እስካሁን አጠቃላይ ዘጠኝ የዓቃቢህግ የምስክሮችን ቃል ፍርድ ቤቱ አዳምጧል።


ሌላኛው የዓቃቢህግ 2ኛ ምስክር ሆነው የተቆጠሩት የአ/አ ቤቶች ኮርፖሬሽን ኃላፊ አቶ ሽመልስ ታምራት መጥሪያ ፈርመው ተቀብለው ባለመቅረባቸው ምክንያት ታስረው እንዲቀርቡ በትናንትናው ዕለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም የስራ ኃላፊውን በቢሯቸውም ሆነ በመኖሪያ ቤታቸው እንዳላገኛቸው ገልጾ ፖሊስ ለችሎቱ መልስ ሰጥቷል።


ዓቃቢህግ ያልቀረቡ ቀሪ ምስክሮችን በሚመለከት ተፈልገው መጥሪያ ደርሷቸው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ችሎቱን ጠይቋል።


በ1ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ሞላልኝ መለሰና የ6ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ቤተማርያም በበኩላቸው ''ከዚህ በፊት ምስክር ለማቅረብ ፖሊስ በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ስራውን በአግባቡ ባልተወጣበት እና ፖሊስ ምስክሮችን በአድራሻቸው እንዳላገኛቸው ገልጾ መልስ በሰጠበት ሁኔታ ላይ ለምስክር ተብሎ ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጥበት የህግ አግባብ የለም በማለት ተከራክረዋል።


ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ አክለውም'' 2ኛ የዓቃቢህግ ምስክር ሆነው የተቆጠሩት የአ/አ ቤቶች ኮርፖሬሽን ኃላፊ አቶ ሽመልስ ታምራት ታስረው እንዲቀርቡ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ኃላፊውን አስሮ ማቅረብ እየተቻለ ምስክሩ በቢሯቸውም ሆነ በቤታቸው የሉም ብሎ መልስ መሰጠቱ በራሱ በዓቃቢህግም ሆነ ፖሊስ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ማሳያ ነው'' ሲሉ የተጠቀሱ ምስክሮችን ቃል የመስማት መብታቸው እንዲታለፍ ጠይቀዋል።


በተጨማሪም ጠበቃ ሞላልኝ ለተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸው ታሳቢ እንዲደረግ ለችሎቱ አስተያየት ሰጥተዋል።


 ክርክሩን የተከታተለው ችሎቱ አጠቃላይ የምስክር አቀራረብን እና የተጨማሪ ማስረጃ አቀራረብን በሚመለከት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


ይህ በእንዲህ እያለ በአ/አ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ለምቷል የተባለውን ሶፍትዌር በሚመለከት በስራ ኃላፊነት ቁጥጥርና ክትትል አላደረጉም ተብለው የተከሰሱት የአ/አ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ የባለቤታቸውና የራሳቸው የባንክ ሒሳባቸው መታገዱን ተከትሎ የህጻናት የልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሊቋረጥባቸው እንደሆነና ህጻናቱ ምሳ መቋጠር የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ችግር ላይ መሆናቸውን የዕንባ እየተናነቃቸው ለችሎቱ ገልጸዋል።


በተጨማሪም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ በነበሩበት ወቅት ወላጅ አባታቸው መታሰራቸውንና ወላጅ እናታቸው በአሁን ወቅት ህመምተኛ መሆናቸውን እና ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸው የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።


መዝገቡን የሚመለከቱ የችሎቱ ዳኞች በተቻለ መጠን ተከሳሶቹ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል። 

(ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ)

14/4/2015

Report Page