RE

RE


የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ ወጥቶላቸው የቤት ቁልፍ የተረከቡ የ40/60 ሁለተኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ቤቶቹን አጠናቆ ሊያስረክባቸው አለመቻሉን ገለጹ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹን አጠናቆ ማስረከብ ባለመቻሉ ቅሬታ የቀረበባቸው ቤቶች አያት ሁለት በተሰኘው ሳይት የሚገኙ 13 ብሎኮች ሲሆኑ፣ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ዕድለኞች ቁጥር 1,390 ነው፡፡

በሳይቱ ከአጠቃላይ ቤቶቹ ውስጥ የ11 ብሎክ ባለቤቶች ቁልፍ የተረከቡ መሆናቸውን፣ ሁለት ብሎኮች ደግሞ ከጅምሩ ቁልፍ አለመረከባቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ቤቶቹን በተመለከተ ቅሬታ ያቀረቡት ዕድለኞች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተደጋጋሚ በሚያሰሙት አቤቱታና በቀጠለው ስሞታቸው ስማቸው ቢገለጽ፣ በቀጣይ በሚኖረው ሒደት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጠርባቸው በመሥጋታቸው ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል፡፡

የቀረበው ቅሬታ እንደሚያሳየው ቤቶቹ ተጠናቀዋል፡፡ ቀሪው ሥራ በአጭር ጊዜ ይጠናቃቀል ተብለው ቁልፍ ቢረከቡም፣ ዕጣው ከወጣበት ቀን ጀምሮ ቤታቸው ገብተው ለመኖር የሚያስችሉ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃና የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የወለል ሴራሚክና የመታጠቢያ ቤት፣ የአሳንሰር፣ እንዲሁም የፓርኪንግና የግንባታ ተረፈ ምርቶች ማንሳት እስካሁን እንዳልተጀመሩ ለማየት ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ የቤቶቹ የአልሙኒየምና የመስታወት ሥራ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ መስመርና የበረንዳ ሥራዎች ተጀምረው አልተጠናቀቁም፡፡

ቤቶቹ ግንባታቸው ከተጀመረ ስምንት ዓመታት እንደሆናቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከጅምሩ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውል ሲገቡ በ18 ወራት ተጠናቀው እንደሚረከቡ ቢገለጽም፣ አሁን የቤቶቹን ቁልፍ ቢቀበሉም ቤቶቹ ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ ላይ ስላልሆኑ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹን ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ዕድለኞቹ የተለያዩ ኮሚቴዎችን አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኮሚቴ አባላት መካከል ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ አንድ ዕድለኛ እንደገለጹት፣ ቁልፍ ከተረከቡ አራት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት በቀረው ጊዜ ውስጥ ቤቱን ባለመረከባቸው፣ አንዱ ቤት ተጠናቆ በአማካይ በወር 10‚000 ብር ቢከራይ በአጠቃላይ ለሁሉም ቤቶች እካሁን 600 ሚሊዮን ብር ያህል ያስገኙ ነበር፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ለቤቶች አስተዳደር ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንና ለአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በዋቢነት አቅርበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምልልስ በበዛበት ሒደት ውስጥ መልስ አጣን የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ቤቶቹ ባለመጠናቀቃቸውና ሰው የማይኖርባቸው በመሆናቸው፣ ንብረት እንዳይዘረፍና በጋራ ጥበቃ ለማድረግ የቦሌ አያት ብሎክ ሁለት የጋራ ሕንፃ የቤት ባለንብረቶች ማኅበር በሚል ስያሜ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ተደራጅተው የከፈቱት የባንክ አካውንት አንዳይንቀሳቀስ ዕግድ የተጣለበትን ደብዳቤ ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡

የባንክ አካውንቱ መዘጋቱ ይመለከተዋል የተባለው የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊ ቤዛ ደመቀ፣ ስለተባለው ጉዳይ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለመጠናቀቃቸው ቅሬታ እየቀረበባቸው ባሉ ቤቶች ውስጥ በተወሰኑት ብሎኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣ ያወጣላቸው ዕድለኞች፣ ያለባቸውን ዕዳ ከእነ ወለዱ እንዲከፍሉ የሚል ማስጠንቀቂያ ለጥፎባቸዋል፡፡ ንግድ ባንክ ማስጠንቀቂያ የለጠፈባቸውን ቤቶች በተመለከተ፣ ‹‹ቤቱ ደርሷችኋል ተብለን በኪራይ ቤት እየኖርን ባለንበት ጊዜ ንግድ ባንክ የውዝፍ ክፍያ ክፈሉ ሊለን አይገባም፤›› ሲሉ አንድ ቅሬታ አቅራቢ ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡ አንድ የቤት ባለቤት ደግሞ፣ ‹‹ቤቱ ውስጥ መኖር ካልቻልን ዕጣ ደርሷችኋል ተብሎ በጋዜጣ መለጠፉ ምንም ትርጉም የሌለው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖረተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ለሪፖርተር የተባለው ቅሬታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ቤቶቹን ለማጠናቀቅ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ የነበረችበት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ፣ ሠርቶ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ወራት ቤቶችንና መሠረተ ልማቱን ለማጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ ገንዘብ መፍቀዱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ያጋጠመው ችግር አገራዊ በመሆኑ ሁሉም ሰው ሊረዳን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

(ሪፖርተር ጋዜጣ)

Report Page