East Gojjam
የቀጠለው ቅሬታ ...
የምስረቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ከ2013 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር በተያያዘ የተነሳው ቅሬታ ነፃና ገለልተኛ በሆኑ አካላት ተጣርቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጠው ጠየቀ።
መምሪያው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ዉጤት በማስመልከት ለትምህርት ሚኒስቴር ቅሬታ ማቅረቡን እና ተገቢ ምላሽ ሊሰጠዉ እንደሚገባም ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
በዞኑ በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በ40 ት/ቤቶች በሶሻል ሳይንስ 15,222 ተማሪዎች ተፈትነው 1765 ተማሪዎች 11.6% ማለፋቸው በናቹራል/ተፈጥሮ/ሳይንስ ደግሞ 7,075 ተፈትነው 1,619 (22.8%) ተማሪዎች ብቻ ማለፋቸውን ተመላክቷል።
ትምህርት መምሪያው ለትምህርት ሚኒስቴር የፈተና አስተራረምና የውጤት አሞላል ችግር ያለበት መሆኑን በተደጋጋሚ ብንገልጽም የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ገልጿል።
የምስራቅ ጎጃ ዞን ትምህርት መምሪያ ባወጣው መግለጫ ፥ ለቀረበው ቅሬታ ምክንያት ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል አንደኛው የአብርሃ አፅብሃ 2ኛ ድረጃ ት/ቤት አንድ ተማሪ (አማኑኤል ፀሐይ) በመጀመሪያ የተለቀቀው ውጤት 162 ሆኖ በኦንላይ ቅሬታ ቢያቀብርም ሳይፈታለት ቀርቶ በአካል በሀገር አቀፍ ፈተና አገልግሎት ቀርቦ ሲያስፈትሽ 647 ሆኖ ተገኝቷል ብሏል።
ሌላው ተማሪዎች ፈተና ሲወስዱ በክልሉ ጦርነት የነበረበት ወቅት በመሆኑና ወላጆችም ግንባር የዘመቱ በመሆናቸው ተማሪዎች በስነልቦና ጫና ውስጥ ሆነው ፣ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እየሰሙ መፈተናቸውን ይህ እየታወቀ እንደ ሰላማዊ ጊዜ ከሌሎች ክልሎች እኩል የመግቢያ ውጤት መወሰኑ ችግር ያለበት እና ኢፍትሃዊ እንደሆነ ገልጿል።
ትምህርት መምሪያው ት/ሚኒስቴር በተማሪዎች የቀረበለትን ቅሬታ በአግባቡ ምላሽ ባለመስጠቱና የቅሬታ ጊዜውን በቸልተኛነት ያሳለፈ በመሆኑ የዞኑ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራንና መላው ማህበረሰቡን ያሳዘነ ተግባር ነው ብሎታል ሚኒስቴሩ ጉዳዩን እንደገና ተገንዝቦት ነፃና ገለልተኛ በሆኑ አካላት ተጣርቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።