ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ ችግር በማኅበረሰቡ ተቀባይነት የሌለው እንደነበርና ተጠርጣሪዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ነዋሪዎች ጠየቁ።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

ተሳታፊዎች ይህንን የጠየቁ  በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው ችግር  ዙሪያ የዞን እና የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች  ዛሬ  ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። 

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን፣ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ዲን እና የፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር አስረስ ንጉስ እና የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ወልድያ ላይ ውይይት  አድርገዋል። 

አንዳንድ ሚዲያዎች  ከአፍራሽ ድርጊታቸው ተቆጥበው ትክክለኛውን እና የሚዲያ ስነ ምግባርንና ሕግን ተከትለው እንዲሠሩ  ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።  "ወሎ እንግዳ ተቀብሎ፣  በፍቅር ተሳስቦ እና ተረዳድቶ አብሮ መኖርን እንጂ በወንድሙ ላይ   ጉዳት ማደርስ የሚችል ሕዝብ አይደለም።  ይህንን መልካም እሴት ጥላሸት ለመቀባት የተሠራው ሴራም  የውሎ ሕዝብ ባሕሪ አይደለም" ብለዋል ተሳታፊዎቹ።  አጥፊዎችንም መንግሥት ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ሊያስከብር እንደሚገባ  ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። 

ችግር ፈጣሪዎችን  አጋልጦ ለሕግ ከማቅረብ ባለፈ የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ ከዩኒቨርሲቲው እና ከአካባቢው የፀጥታ መዋቅር ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። 

በማኅበራዊ ሚዲያው የሚናፈሰውን አሉባልታ   እውነትነት እና ምንጩን በማጣራት ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሠላም መጠበቅ እንዳለበት  ከመድረኩ ተነስቷል።

መሠል ውይይት ችግሩ በተከሰተባቸው ክልሎች እየተካሄደ እንደሚገኝ ከመድረኩ  የተገለፀ ሲሆን ችግር ፈጣሪዎችንም ለሕግ ለማቅረብ የክልሎች የፀጥታ አካላት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየሠሩ እንደሆነ ተገልጧል። ማኅበረሰቡም ከደቦ ፍርድ በመውጣት ተጠርጣሪዎችን  ለሕግ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ከመድረኩ ተነስቷል።

ማኅበረሰቡ ችግሩን ለመፍታት ያደረገውን ርብርብ የሥራ ኃላፊዎች አመሥግነዋል።


  ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

Report Page