ETH

ETH


የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄ ምንድነው ?

የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽስ ምንድነው ?

በርከት ያሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በማኅበሮቻቸው በኩል መንግሥትን የደመወዝ ጭማሪና የዕርከን ዕድገት እንዲያደርግ፣ አሊያም ለሚከተለው ጣጣ ኃላፊነቱን እንደማይወስዱ ሰሞኑን ገልፀዋል።


የየዩኒቨርሲቲዎች ማኅበራትም ለየብቻ ባቀረቡት ቅሬታ መንግሥት እስከ መስከረም ወር የደመወዝና ተያያዥ የደረጃ ጥያቄዎቻቸውን እንዲመልስ አሊያም አድማ እስከ መምታት ድረስ ዕርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል።


የዩኒቨርሲቲዎች ማኅበራት በአንድ ላይ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ቋሚ ተጠሪ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ፣ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት ለሚወስዱት አሠራርን ለሚያቃውስና የትምህርት መርሐ ግብርን ሊያስተጓጉል ለሚችል ዕርምጃ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች ኃላፊነት አይወስዱም፡፡ 


ትምህርት ሚኒስትሩ ሆኑ ማንኛውም የሚመለከተው የመንግሥት አካላት ጥያቄዎቻቸውን ተቀብለው አግባብነት ያለው ምላሽ በጊዜ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡ 


የተለያዩ መምህራንም በየግላቸው እንደሚናገሩት፣ በሚያገኙት ደመወዝ ዝቅተኝነትና በደረጃ ያለማደግ ተስፋ በመቁረጣቸው መንግሥት ጥያቄዎቻቸውን በአፋጣኝ እንዲመልስላቸው እንደሚፈልጉ ነው፡፡


የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበራት በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሥር የሚታቀፉ ሲሆን ዋናው አገራዊ ማኅበሩም ይህንን ችግር ለመፍታት ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የሥራ ምዘናና ደረጃ ማስተካከያ (Job Evaluation and Grading/JEG) ላይ በጥናት ሲሳተፍ እንደነበር የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ 


በ2011 ዓ.ም. ይህ ጥናት ተጠናቆ ተግባራዊ ሲደረግ 22 የሥራ ደረጃዎችን ይዞ ወጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ማኅበሩ ከትምህርት ሚኒስቴርና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በተደጋጋሚ በመነጋገር፣ ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ያሉ የአጠቃላይ የመምህራንን ደረጃ በማስተካከል ተግባራዊ አስደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ ወጥቶ የነበረው ደረጃና የደመወዝ ዕድገት በጊዜው ፀንቶ ቆይቷል፡፡


‹‹በአጠቃላይ ትምህርት፣ የመምህራን የሥራ ደረጃና ደመወዝ ዕርከን ላይ ትኩረት አድረገን ስለነበር፣ በ2011 ዓ.ም. ላይ ይህ ጥናት ወደ ተግባር ሲወጣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደመወዝ ዕርከንና ደረጃዎች ችላ ተብለው ነበር፤›› ሲሉ ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡


እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ በዚህ ምክንያትም በዲግሪ የትምህርት ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚያስተምሩ መምህራን 12,500 ብር ሲከፈላቸው፣ በማስተርስ የትምህርት ደረጃ የሚያስተምሩ ደግሞ ከ13 ሺሕ ብር በላይ ይከፈላቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን የዩኒቨርሲቲ ዋና መምህራኖች 11,305 ብር ብቻ እየተከፈላቸው ቆይተዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄዎችን ማንሳት እንደጀመሩ ዮሐንስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡


የዩኒቨርሲቲ መምህራኖቹም በመቀጠል በእናት ማኅበራቸው፣ በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በኩልና በትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጥናቶችን በማካሄድ፣ ሰነዶች ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት ማቅረባቸውን ማኅበራቱ በጻፉት የጋራ ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ 


የደረጃ ዕድገታቸውን ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለማሻሻልም ከጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባለ ሦስት አማራጮች የዩኒቨርሲቲ መምህራን ምዘና ማሻሻያ ምክረ ሐሳብ ለትምህርት ሚኒስቴር ማስገባታቸውን በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል፡፡ 


ነገር ግን ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው አዲሱ የሥራ ደረጃ ማሻሻያ ከጥናቱና ምክረ ሐሳቡ ውጪ የነበረ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡


በዚህና መሰል የሥራ ላይ ለውጦች በመፈለግ ሲሆን፣ መምህራኖቹ ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ ያሉት እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር) አስተያየት ከሆነ ግን፣ ትንሽ መታገስና ከአድማም መቆጠብ እንዳለባቸው ነው፡፡ 


በእሳቸው ማኅበር ውስጥ አባል የሆኑ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 700,000 መምህራን ያሉ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ግን ወደ 40,000 የሚጠጉ ናቸው፡፡


የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ የመምህራኖቹ ጥያቄ እንዳለ እንደሚያውቅ፣ ነገር ግን አሁን ላይ ለውጦች ለማምጣት ጥናት እየተካሄደ እንዳለ ከመግለጽ ባለፈ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚለው ነገር እንደማይኖር፣ የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አመለወርቅ ሕዝቅኤል ገልጸዋል፡፡ ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ አይደለም የሲቪል ሰርቪስ ጉዳይም ነው፤›› በማለት ወ/ሮ ቀለምወርቅ አክለዋል፡፡


ፊርማቸውን ካኖሩት ማኅበራት ኃላፊዎች ውስጥ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አንደኛው ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተፈራ መላኩ (ዶ/ር)፣ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ከጥቂት ቀናት በፊት በስብሰባ ላይ እስኪነግሯቸው ስለጉዳዩ ሙሉ መረጃ እንዳልነበራቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታና ዕውን አንገብጋቢው ጉዳይ ምን እንደመሆነ ማየት ግን ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተፈራ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡


የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ይህ ዓይነት ጥያቄ በእሳቸው ዩኒቨርሲቲ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡  

(Credit : ሪፖርተር ጋዜጣ)


(የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄዎች ፦ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን)

Report Page