ENA

ENA


የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ሶስቱ አገሮች በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት መሆኑን የግድቡ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ገለጹ።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እኤአ በ2015 በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን ካርቱም የህዳሴ ግድቡን ድርድር አስመልክቶ የመርሆች ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

የመርህ ስምምነቱ አስር አንቀጾችን ያካተተ ሲሆን የሶስቱንም አገሮች ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በተስማሙት የመርህ ስምምነት መሰረት ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ለኢዜአ ገልጸዋል።

በህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ የሶስቱም አገሮች ባለሙያዎች የተስማሙባቸው ነጥቦች የተቀመጡ መሆኑን አስታውሰው አገሮቹ በዚሁ መሰረት መስማማታቸውን አስረድተዋል።

ግብጽና ሱዳን በመርሆች ስምምነት ውስጥ ሁለት ጥናቶች እንዲካሄዱ የሚያስቀምጥ ቢሆንም ግብጽና ሱዳን ጥናቱ እንዳይካሄድ ሲያስተጓጉሉ ነበር ብለዋል።

አገሮቹ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በ15 ወር ውስጥ ሁለት ጥናቶችን ማከናወን እንዳለባቸው ቢያስቀምጥም ጥናቶቹ እንዳይካሄዱ ግብጽና ሱዳን በያዙት ግትር አቋም ሳይሳካ ቀርቷል ነው ያሉት።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ ግብጽና ሱዳን የግድቡን ውሃ ሙሌት በተመለከተ የሚሰጡትን የተዛባ መረጃ ሊመረምር እንደሚገባም ገልጸዋል።

በመርሆ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ውሃ ሙሌት የተመለከቱ አንቀጾች በግብፅና ሱዳን የውሃ ባለሙያዎች የሚታወቁና ስምምነት የተደረሰባቸው መሆኑንም አንስተዋል። 

በመርህ ስምምነቱ አንቀጽ 9 ላይ እንደተመለከተው ድርድሩ የእያንዳንዱን አገር ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ መካሄድ አለበት።

ግብጽና ሱዳን ግን ይህን በመጣስ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ወቀሳና ትችት እየሰነዘሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የተዛባ መረጃ በመስጠት አለም አቀፉን ህብረተሰብ ከማሳሳት ባለፈ ለድርድር ውጤት አያመጣም ብለዋል።

የመርሆች ስምምነቱ አለም አቀፍ የውሃ ህጎችን ያካተተና የሶስቱንም አገሮች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ኢንጂነር ጌዲዮን፤ኢትዮጵያ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ የግድቡን የግንባታ ደረጃ ተከትላ የውሃ ሙሌቱን ማከናወኗን ትቀጥላለች ብለዋል።

በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም የ18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ሙሌት ተጀምሯል እንጂ አልተጠናቀቀም ብለዋል።

የሁለተኛው ዓመት የውሃ ሙሌት ነሃሴ መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጰያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ላይ የሚደርሱት በሶስትዮሽ ድርድሩ ማዕቀፍ ብቻ መሆኑንም ነው ኢንጅነር ጌዲዮን ያስታወቁት።

ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዙ ይታወሳል፤ በዘንድሮው ክረምት ደግሞ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ይሆናል።

(ኢዜአ)

Report Page