BG

BG


በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን በሎ ጅጋንፎይ ወረዳ ነሃሴ 24 እና ነሃሴ 25 በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ከ50 በላይ ሴቶች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ሪፖርት አደረገ።

የክልሉ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር ምስጋናው ኢንጂፈታ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ፤ ከ50 በላይ ሴቶችን በጅምላ የገደሉት የጉህዴን ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ ከሰዋል።

ጉድህዴን ከዚህ ቀደም በአካባቢው እንደነበር አስታውሰው የሰላም ትግላቸውን ትተው በአፈሙዝ ጥቃት እየፈፀሙ ነው ብለዋል፤ ኃይሉ ከመተከል ዞን ባለፈም ወደ ካማሺ ዞን መግባቱን ጠቁመዋል።

አካባቢው ላይ በስፋት የጉምዝ ማህበረሰብ እንዳለ በማንሳት ነሃሴ 23 እና ነሃሴ 24 ቡድኑ ከ50 በላይ ሴቶችን በጅምላ መረሸኑን ገልፀዋል፤ ማህበረሰቡ ድምፁን የሚያሰማበት፣ ሶሻል ሚዲያ የመጠቀም፣ ሚዲያ የማግኘት እድል የለውም ብለዋል።

ም/ኮሚሽነሩ ምስጋናው ፤ አጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ እና አካባቢውን ከታጠቀው ኃይል ለማስለቀቅ ተጨማሪ ኃይል እየጠየቅን ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፀጥታ ኃይሎች በካማሺ 5 ወረዳዎች ከጉህዴን ታጣቂዎች ጋር ውጊያ እያካሄዱ መሆኑንም ም/ኮሚሽነር ምስጋናው ገልፀዋል።

"እነዚህ ታጣቂዎች ጉምዝን ነፃ እናወጣለን፣ በመሰረተ ልማት ወደኃላ ቀርተናል፣ ጉምዝ እራሱን በእራሱ ያስተዳደር የሚሉ ...ሌሎች መዓት ነገር ነው የሚያነሱት ነገር ግን ጥያቄያቸውን በሰላም ከማቅረብ ይልቅ ኢ-ህገመንግስታዊ መንገድ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት" ሲሉ አክለዋል።

ከቡድኑ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የክልሉ ፖሊስ በርካታ ተጠርጣሪዎችን ማሰሩን ጠቁመዋል። 

ምክትል ኮሚሽነሩ በአካባቢው ባለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የሱዳን እጅ በጣም ረጅም መሆኑን ያነሱ ሲሆን "በሱዳን አካባቢ የነበረው የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው፤ በመሳሪያ በሃሳብ፣ እዛ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን መልምሎ ሱዳን አስቀምጦ የሚደግፉበትና ሽፋን የሚሰጡበት ሁኔታ አለ" ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚፈፀሙትን ጥቃቶች ለመመከት የክልሉ የፀጥታ ኃይል በቂ የፀጥታ ኃይል እንደሌለው ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ አሁንም የታጠቁ ኃይሎች ከበው ያሉባቸውን ቦታዎች ሰብሮ ለመግባት እና ለማጥቃት የአቅም ውስንነት በመኖሩ የመከላከያ እና ፌዴራል ድጋፍ ጠይቀናል ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ለፌዴራል መንግስት የሚጠየቁ ጥያቄዎችን (የመሳሪያ ግዢ) በቶሎ ተደራሽ ያለማድረግ ችግር አለ ያሉ ሲሆን ምንም እንኳን ፌዴራል መንግስት በሀገር ደረጃ ያለውን ችግሮች ቢታወቅም ቢያስ ክልሉ ያለበትን ችግሮች በማየት ትኩረት እንዲሰጠው ፣ የታጠቁት ኃይሎች ነገ ተደራጅተው ዋጋ እንዳያስከፍሉ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ቶሎ ምላሽ እንዲሰጥ ፤ ግብዓት በማድረስ እገዛ እንዲያደርግልን እንጠይቃለን ብለዋል።

(ቪኦኤ-ናኮር መልካ)

Compiled By : Tikvah-Ethiopia

Report Page