BBC

BBC


#SUDAN

ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች በነበሩባቸው የሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ #የግዳጅ የውትድርና ምልመላ ይካሄድ እንደነበረ መረጃ እንዳለው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አሳወቀ።

ተቋሙ ከወራት በፊት ከስደተኞቹ መካከል አንዳንድ ጊዜ በኃይል ጭምር ተዋጊዎችን ለመመልመል የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ “ተአማኒ ሪፖርቶች” ደርሶኛልብሏል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ 2013 ዓ.ም. ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ድንበር ተሻግረው ወደ ምሥራቅ ሱዳን መግባታቸው ይታወሳል።

ተመድ ወታደራዊ ምልመላ መኖሩን እንደተገነዘበ ጉዳዩን በተመለከተ ለሱዳን ማዕከላዊ መንግሥትና ለአካባቢ ባለሥልጣናት ስጋቱን መግለጹን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ሁኔታዎች የተሻሻሉ ይመስሉ እንደነበር ገልጿል። ተቋሙ " ወታደራዊ ምልመላውን ለማካሄድ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች እንደነበሩ " ከስደተኞች መረዳቱን የገለጸ ቢሆንም፤ የትኛው ወገን ምልመላውን እንዳካሄድ ግን " ማረጋገጥ አልቻልኩም " ብሏል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ሰደተኛ ነን ብለው ወደ ሱዳን የገቡ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ከህወሓት ጋር በመሆን ሲዋጉ ነበር እንደነበር መግለፁ ይታወሳል።

የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፤ በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ የሚደረጉ ምልመላን ጨምሮ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የስደተኞችንና የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ ከዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችና የስደተኞች መርሆዎች ጋር የሚቃረን ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል።

ስደተኞችን በመመልመል ላይ የተሰማሩ አካላትም ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ እና ሰብዓዊ ሕግጋቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ብሉምበርግ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ከትግራይ ኃይሎች ጎን ተሰልፈዋል የሚል ዘገባ አወጥቶ ነበር።

ብሉምበርግ በዘገባው ለደኅንነታችን እንሰጋለን በሚል በሱዳን ቀርተው ጥገኝነት ጠይቀው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት፣ ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች ጋር በመሆን በሁመራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መቃረባቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውኛል ብሏል።

የብሉምበርግ ዘገባን ተከትሎ ተመድ ለቀድሞ የሰላም አስከባሪ አባላት የስደተኝነት እውቅና ከሰጠ በኋላ ወደ ጦርነት ተሰማርተዋል የሚሉ ክሶች ሲሰሙ በተደጋጋሚ ሲሰሙ ቆይተዋል።

የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ግን የስደተኝነት እውቅናን የሚሰጠው የሱዳን መንግሥት መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ላይ የደርጅቱ ተሳትፎ የቴክኒክ ምክር እና ድጋፍ ማድረግ ብቻ መሆኑን አመልክቷል።

“ቁጥራቸው ወደ 650 የሚጠጋ የቀድሞ ሰላም አስከባሪ አባላት በሱዳን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው 247ቱ” የስደተኝነት እውቅና ማግኘታቸውን ከፍተኛ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ነገር ግን የስደተኝነት እውቅና የማግኘት ሂደቱን ሳያጠናቅቁ ከሚኖሩበት አካባቢ ጥለው ስለሄዱት ግለሰቦች የሚያውቀው መረጃ እንደሌላው ድርጅቲ ለቢቢሲ በኢሜይለ በሰጠው ምላሽ ገልጿል።

“ዓለም አቀፍ ሕጎች የስደተኝነት እውቅና ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እንደማይሄድ እና አንድ ወታደር ጥገኝነት ለመጠየቅ ከፈለገ ወታደርነቱን መተው እንዳለበት ይደነግጋሉ” ሲል ከፍተኛ ኮሚሽኑ አክሏል።

(BBC AMHARIC)


Report Page