#BBC

#BBC


የአሜሪካ ብሔራዊ የስለላ ቢሮ ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት የኮሮናቫይረስ ከቻይና ቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነው ወይስ በተፈጥሮ የተከሰተ ነው በሚለው ላይ ለሁለት መከፈሉ ተነገረ።

ነገር ግን ይህ የአገሪቱን 18 የስለላ ኤጀንሲዎች የሚቆጣጠረው ተቋም ኮሮናቫይረስ ባዮሎጂካል የጦር መሣሪያ እንዳልሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሷል።

የኮሮናቫይረስን መነሻ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ብሎም ማስረጃዎችን ለማሰብሰብ ጊዜው እጅግ እየራቀ መሆኑን ባለሙያዎች በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሲአይኤ ሪፖርት ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ሪፖርቱን "ፀረ ሳይንስ" በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ይህ ከዳይሬክተሩ ጽሕፈት ቤት የወጣው ሪፖርት የደኅንነቱ ማኅበረሰብ በኮሮናቫይረስ መነሻ ላይ አሁንም የተከፋፈለ አቋም መያዙን ገልጿል።

"ሁሉም ኤጀንሲዎች በቫይረሱ ከተበከለ እንስሳ ጋር በተፈጠረ ተፈጥሯዊ ንክኪ ወይም ከቤተ ሙከራ ጋር በተያያዘ ክስተት አምልጦ ይሆናል በሚሉት በሁለቱም ግምቶች ይስማማሉ" ሲል ሪፖርቱ አስነብቧል።

በሪፖርቱ ላይ ስማቸው ያልተጠቀሰ የስለላ ተቋማት፤ ኮሮናቫይረስን ከሚሸከም እንስሳ ወይም ከቫይረሱ ጋር ቅርበት ካለው ሌላ ቫይረስ ካለበት እንስሳ ጋር በተፈጠረ ንክኪ ቫይረሱ ወደ ሰዎች ተላልፎ ይሆናል ብለው ያምናሉ። ነገር ግን በዚህ መደምደሚያ ላይ ዝቅተኛ እምነት እንዳለቸው ተጠቅሷል።

አንድ የስለላ ድርጅት ከአስር ዓመታት በላይ የኮሮናቫይረስን በተለይም በለሊት ወፎች ላይ ሲያጠና በቆየው የዉሃን የቫይረሶች የምርምር ተቋም ውስጥ የመጀመሪያው የሰዎች ንክኪ ተፈጥሯል የሚል የተሻለ እምነት ማሳደሩ ተጠቅሷል።

ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ቻይና ለምርመራው ተባባሪ አይደለችም ሲሉ ወቅሰዋል።

"የዚህን ወረርሽኝ አመጣጥ በተመለከተ ወሳኝ የሚባሉ መረጃዎች በቻይና ይገኛሉ። በቻይና ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዓለም አቀፍ መርማሪዎችን እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሕብረተሰብ ጤና ማኅበረሰብ ክሰተቱን ለመዳሰስ የሚያደርጉትን ጥረት ለማስቀረት ጥረት ሲያደርጉ ነበር" ሲሉም ፕሬዘዳንቱ ተችተዋል።

ባይደን አክለውም "መላው የዓለም ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ማግኘት ይገባዋል። እናም ይህንን መልስ እስከምናገኝ ድረስ እኔም አላርፍም" ብለዋል።

በመላው ዓለም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ወረርሽኝ በቻይናዋ በዉሃን ከተማ እአአ ታኅሣሥ 2019 ነበር የተቀሰቀሰው።

ዉሃንን የጎበኘው የዓለም ጤና ድርጅት ቡድን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሽታው በገበያ ከተሸጠ እንስሳ ተነስቷል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ይህ መደምደሚያ በአንዳንድ ሳይንቲስቶች ውድቅ ተደርጓል።

በግንቦት ወር ባይደን የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች መረጃውን እንዲገመግሙ እና በቫይረሱ አመጣጥ ላይ "ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ ሊያቀርብ" የሚችል ሪፖርት እንዲያዘጋጁ ትዕዛዛ ሰጥተው ነበር።

(BBC - አማርኛው አገልግሎት)


Report Page