Addis Maleda

Addis Maleda


የዲኬቲ ኢትዮጵያ ሠራተኞች፣ ተቋሙ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከ50 በመቶ በላይ ሠራተኞቹን በሕገወጥ መንገድ ከሥራ አፈናቅሏል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

አንዲት ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ሠራተኛ፣ በዚህ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ባስቸገረበት ሰዓት፣ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከ50 በመቶ በላይ ሠራተኞቹን ከሥራ እንዲፈናቀሉ አድርጓል ብለዋል።

አክለውም፣ ተቋሙ ዓለም ዐቀፍ ተቋም በመሆኑ፣ ከሥራ የሚያባርርበት ምክንያት ለጋሽ (donor) የለም በሚል ነው። ሆኖም ለጋሽ ቢኖርም ባይኖርም በራሱ መቆም የሚችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሥራው ጤና ላይ ያተኮሩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና ፋርማሲዎች መሸጥ መሆኑን ጠቅሰውም፣ በዚህ ወቅት በምርቶች ላይ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕገወጥ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

ከአሽከሪካሪዎች ጀምሮ እስከ አስተዳደር ሠራተኞችም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ሠራተኞች ላይ ሕገወጥ የሥራ ማፈናቀል እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ሠራተኛዋ በተጨማሪም ይህን ተግባር እየፈጸሙ ያሉት በትውልድ ፓኪስታናዊ የሆነው አሜሪካዊ የማዕከላዊ ቢሮ ኃላፊ (country director) እና የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊው (area office manager) በጋራ በመሆን ነው በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ሌላኛው ሥማቸውን ሳይጠቅሱ ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኛ በበኩላቸው፣ ከአምስት ዓመት በላይ በቋሚነት መሥራታቸውን ገልጸው፣ ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ታስሬ ስመለስ ከሥራ ታገድኩ ብለዋል።

በዚህም ፍርድ ቤት ከስሼ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ከሥራችን ውጪ በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ነበረን። አሁን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር ስለወረደ ሠራተኛ እየቀነስን፣ አዲስ መዋቅርም እየሠራን ነው የሚል ምላሽ አቅርበዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም አዲስ መዋቅር ሊሆን እንደማይችል አንስተው፣ በመላ አገሪቱ ከ100 በላይ ሠራተኞች ቢኖሩም የቀሩት 30 ገደማ ናቸው ብለዋል። በዚህም እርሳቸው ከተባረሩበት ኅዳር ወር ጀምሮ እስከ አሁን በየወሩ የሥራ ማገጃ እየሰጡ መሆኑን አመላክተዋል።

በእኛ ምትክ ሌላ ሠራተኛ የሚቀጥሩ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ይሁን እንጂ ጅማ ለሚገኝ ተዘግቶ ለቆየ አንድ መጋዘን፣ ፈቃድ ያለው ፋርማሲስት የሥራ ቅጥር ሳያወጡ መተካታቸውን ጭምጭታ ሰምቻለሁ ነው ያሉት።

እንዲሁም አንድ ሠራተኛ በርከት ያሉ ዓመታትን በተቋሙ እንደቆዩ ገልጸው፣ አሁን ላይ ተዘምቶብናል ማለት ይቻላል ብለዋል።

ተቋሙ ላለፉት 32 ዓመታት በቤተሰብ ዕቅድና በሥነ ተዋልዶ ጤና ትልቅ ሥም የነበረው ተቋም ነው ካሉ በኋላ፣ መጀመሪያ የቆዩ የአስተዳደር ሠራተኞችን እንዲወገዱ በማድረግ በቀጣይም እስከ ታች ያሉት ተባርረዋል ነው ያሉት።

አክለውም፣ በዘንድሮው ዓመት የመጣው አዲስ የተቋሙ ኃላፊ በግልጽ ተቋሙን የማፍረስ ሥራ ነው እየሠራ ያለው ብለዋል። በተጨማሪም በትክክለኛ ዋጋ እንዲያሰራጩ የሚፈለገውን ምርቶች ከመንግሥት ፖሊሲ ውጪ ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር ማኅበረሰቡ እንዲማረርና ሌላ ጫና ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከሥራ የታገዱ ሠራተኞችም ቢሮ እንዳይገቡ ጭምር እየተከለከሉ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ሕገወጥነት ነው ብለውታል።

ቅሬታ አቅራቢዎች እንዲሁም የሥራ ቦታቸውን ለቀው ሌላ ቦታ እንዲሄዱ እንደሚጠየቁ የገለጹት ሠራተኞቹ፣ ለአብነትም የሥራ ቦታው አዲስ አበባ የሆነ ሰው እንደማይሄድ እየታወቀ ወደ ክፍለ አገር ሂድ ይባላል፣ አልሄድም ካለ ሥራውን እንዲለቅ ይገደዳል ብለዋል።

አክለውም፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና አዋጅ ባለመታቀፋችን ይህ ችግር ደርሶብናል ሲሉ ገልጸው፣ ያም ሆኖ ግን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን ለሚመለከተው ተቋም እያሳወቅን ነው። በፍርድ ቤትም ጉዳያችን ተይዟል ነው ያሉት።

አዲስ ማለዳ የቀረቡ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ ወደ ዲኬቲ ኢትዮጵያ ቢሮ ደውላ የጠየቀች ሲሆን፣ ምላሽ በስልክ አንሰጥም መባሉን ተከትሎ የተቋሙን ምላሽ ማካተት አልቻለችም።

Report Page