ALAIN

ALAIN


በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

“አካባቢው እንዲተራመስ የሚፈልጉ አካላት አሉ” ያሉት ቃል አቀባዩ” የሱዳንን ሰፊ መሬትን የያዙ አሉ፤ ግን ለሱዳን ተቆርቋሪ እየመሰሉ ይረብሻሉ” ብለዋል፡፡ “ስማቸውን መናገር አልፈልግም ፤ እናንተው ታውቋቸዋላችሁ” ሲሉ ማንነታቸውን በግልጽ ሳይጠቅሱ አልፈዋል። “እነዚህ ሰዎች በሱዳን ቢከሽፍባቸው በሌላ ቦታ ሊጀምሩ ይችላሉ” ሲሉም ነው ፣ አካባቢውን ለማተራመስ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የገለጹት። “ይህም ሆኖ እኛ የኢትዮ-ሱዳንን ግንኙነት እንንከባከባለን ፤ ቁማር የሚጫወቱትን ማጋለጥ እንፈልጋለን ፤ ለነዚህ ሰዎች ዕድል አንሰጥም” በማለትም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አንዳንድ የሱዳን መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች በጉዳዩ ላይ አልተሳተፉም ማለት አይቻልም ብለዋል ቃል አቀባዩ።

በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል የሚደረገው ድርድር በሚቀጥለው ዕሁድ ታህሣሥ 25 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚቀጥልም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ የድርድሩን ስብሰባ የተጠራው በአፍሪካ ነው፡፡ ከድርድሩ ራሷን አግልላ የነበረችው ሱዳን ወደ ድርድሩ እንደምትመለስ በቅርቡ ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፡፡

በትግራይ ክልል ሲካሔድ ከቆየው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኤርትራ በዚህ ዘመቻ አግዛናለች “ያሉት፣ “ሕግ የማስከበር ዘመቻውን ደግፋለች ማለት ነው እንጂ ወታደር ልከዋል” ማለታቸው አይደለም ሲሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻውን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ሁሉ እገዛ ማድረጋቸውን በመጥቀስ ምስጋና ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡

ስለ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከዚህ ቀደም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ያሉት ትክክል ስለመሆኑም አምባሳደር ዲና አንስተዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ “ሕወሓትን ለመታደግ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ስለመወትወታቸው” ጄነራል ብርሀኑ ገልጸው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ እንደመሆናቸው “ከእሳቸው የተለየ ነገር አትጠብቁ “ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው “እኔ ማንንም አልወገንኩም ወገንተኝነቴ ለሰላም ብቻ ነው” በማለት በወቀቅቱ ለቀረበባቸው ክስ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡

ምንጭ፦ አል ዓይን ኒውስ


Report Page