20/80

20/80


የካቲት 06 2012 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ጋር በነበረን ስብሰባ የተገኘው መልስ ሪፖርት

ሠላም የ13ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች፤ በመጀመሪያ ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ባለቤቶች ተሰባስበን ስለ ቤታችን እንድንታገል ጥሪ በተደረጋው መሠረት የተቻለንን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመን መሰባሰብ በመቻላችን የተሰማንን ደስታ መግለጥ እንወዳለን፡፡ አሁንም ቢሆን ቤታቸንን በምንፈልገው ጊዜ የማግኘትና ያለማግኘታችን መክነያት የኛ የባለቤቶቹ አንድነት፣ፅናትና ጥንካሬ ስለሆነ፡

 አሁንም መረጃው ያልደረሳቸው የቤት ባለቤቶችን መረጃውን በማድረሥ ቴልግራምና ፌስቡክ የሚጠቀሙት የቴሌግራምና(@win132080) የፌስቡክ ገፆቻችንን እንዲቀላቀሉን የማይጠቀሙት ደግሞ በሌሎች አማራጮች መረጃ በማግኘት አብረውን እንዲታገሉ እንድናደርግ፤

 ከፊት መጥታችሁ ማስተባበር የምትችሉ ወይም ችሎታው እንዳላቸው የምታውቋቸውን የቤት ባለቤቶች እንድትጠቁሙንና ቤታችንን በአጭር ጊዜ እንድናገኝ የበኩላችሁን እንድታበረክቱ በድጋሜ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ዛሬ የካቲት 06 2012 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኃላፊ ኢንጅነር ሠናይትና ሌሎች የቢሮ ሀላፊዎች ጋር የነበረንን ስብሰባና ውጤቱን በአጭሩ ለማሳወቅ ያክል፡-

በመጀመሪያ ደረጃ 32ሺ በላይ ከሆኑት የ13ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች መካከል በትንሹ 2000 የሚገመት የቤት ባለቤት እስከ 3፡00 ባለው ጊዜ ብቻ ቦታው ድረስ የተገኘ ሲሆን ዘግይቶ የመጣው ባለቤት ተጨምሮ ቁጥሩ ከዚህ በጣም የሚበልጥ ህዝብ ቦታው ድረስ ተገኝቷል፡፡

በመቀጠል ለውይይት ወደስብሰባ አዳራሽ ለመግባት በምንሞክርበት ጊዜ በዋናነት ሁለት ችግሮች አጋጥመውናል፤በመጀመሪ ደረጃ ስልክ ይዞ መግባት ስለማይቻል ከሁለት ሺህ በለይ ለሆነ የቤት ባለቤት ስልኩን የሚያስቀምጥበት ቦታና ሃላፊነት ወስዶ ስልኮችን ተቀብሎ የሚያሰቀምጥ አካል መገኘት አልቻለም፤በሁለተኛ ደረጃ የመጣውን ሰው ሊያስተናግድ የሚችል የመሠብሰቢያ አዳራሽ እንደሌላቸው ማሳወቃቸው ነበር፡፡ በርግጥ እነዚህ ችግሮች ተከስተው ስብሰባው መስተጓጎሉን ባለስልጣናቱ አይፈልጉትም ብሎ ለመገመት ቢያስቸግርም፤ባለፈው ጥር 27 በነበረን ስብሰባ እነዚህን ችግሮች ቢነግሩን መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይችል ነበር፡፡

እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው የተወሰኑ የጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት ከቢሮ ሃላፊወችና ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይትና ድርድር 110 የአዲስ አበባ መታወቂያ ያለው ሠው ወደ ስብሰባ አዳራሹ እንዲገባና ከቢሮ ሀላፊዎች ጋር ውይይት እንዲያደርግ የተቀረው የቤት ባለቤት ግን ከነዚህ 110 ሠዎች መረጃውን እንዲሠማ ስምምነት ላይ ተደርሶ የተወሰኑ የጊዜያዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ 110 አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ስብሰባ አዳራሹ በመግባት ስብሰባውን ሊሳተፉ ችለዋል፡፡

ሀላፊዋ ኢንጅነር ሰናይት ሌላ ሰው ልካ ውይይት እንዲደረግ አድርጋ የነበረ ቢሆንም ከተወሰነ ንግግር በኋላ ኢንጅነር ሰናይትና አንድ ሌላ የቢሮ ሀላፊ የቤት ባለቤቶችን ለማነጋገር ወደ ስብሰባ አዳራሹ መጡ፡፡

ሀላፊዋ ስለቤቱ አጭር መግላጫ ከሠጠች በኋላ ለውይይት ከተጋበዙ የቤት ባለቤቶች የተነሳላቸውን ሁለት ጥያቄዎች በመመለስ የነበረው እጅግ በጣም አጭር ስብስባ ተቋጭቷል፡፡

ኢንጅነር ሠናይት ንግግራቸውን የጀመሩት ‘የ13ኛ ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪቤት እድለኞች እንኳን ደስ አላችሁ’ በሚል በጣም የዘገየ ንግግር ሲሆን ቤቶችን ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሰሩ እንደሆነ፣ እጣ ሲዎጣባቸው 80 ፐርሰንት የነበሩት የ13ኛ ዙር 20/80 ቤቶች በአሁኑ ጊዜ በአማካይ 98 ፐርሰንት አካባቢ መጠናቀቃቸውንና አብዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን ፤አሁን ያለው የከተማ አስተዳደር ከሚገባው በላይ በጀት መድቦ ቤቶቹ የሚጠናቀቁበትንና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች(መንገድ፣መብራት ውሃና መሠል መሠረተ ልማቶችን) የሚኖርባቸውን ብዛት ያለው የቤት ባለቤት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመሰራትና በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አጠር ያለ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የ13ኛ ዙር የ20/80 የቤት አድለኞች በተነፃፃሪነት ብዙ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ይህን በሚመጥን መልኩ ቤቶችን ለማስተላለፍ የዝግጅት ስራቸውን እየጨረሱ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን በተቻለ መጠን በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቶችን ለባለቤቶቹ እንደሚያስተላልፉ ቃል ገብተዋል፡፡

የቢሮ ሃላፊዋ ማብራሪቸውን ከጨረሡ በኋላ ሁለት ጥያቄዎችን ከተሳታፊዎች የተቀበሉ ሲሆን ጥያቄዎቹም፡

1. መሥሪያ ቤቱ ለ7 እና ለ15 ዓመታትያህል ቆጥበን የሠራነውን ቤታችንን ወደ እድለኞቹ የሚተላለፍበትን ቁርጥ ያለ ቀን አስቀምጦ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ወደ ተጠቃሚዎች እንዲያስተላልፍ እንጠይቃለን፡፡

2. ኮየ ፈጬ ያሉ ቤቶችን በተመለከተ አንዳንድ ብሎኮች ላይ የተወሰኑ የቤት ቁጥራቸው ተለጥፎ ሌሎች የቤት ቁጥራቸው ተዘሏል ምክነያቱ ምንድን ነው?

የሚሉ ነበሩ፡፡

ሀላፊዋ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሞከሩ ሲሆን ቤቶቹ የሚተላለፉበትን ቁርጥ ያለ ቀን በተመለከተ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከሩት ሁሉንም ቅድመ ዝግጅቶች እየጨረሱ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ የማስተላለፍ ስራውን እንደሚጀምሩ ነገር ግን ቁርጥ ያለ ቀን ለመግለፅ ከብዙ ነገሮች አንፃር እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነሯ አያይዘውም ባለቤቶች ቤቶችን ለመረከብ ማሟላት የሚገባቸውን ሰነዶች ማለትም የታደሰ መታወቂ፣የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣የፍች የምስክር ወረቀት፣የውርስ ማስረጃና መሠል ሰነዶችን በማዘጋጀት እነዲጠባበቁ፤ቤት ማስተላለፍ መጀመራቸውን የሚገልፁትና የማስተላለፍ ስራው የሚሰራው ቦሌ ክፍለ ከተማ ስለሆነ እዛ ማስታወቂያ እንዲከታተሉ መረጃ ሰጥተዋል፡፡

ቁጥር ያልተለጠፈባቸውን ቤቶች በተመለከተ ሲመልሱ ይህ በተለያየ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያስቀመጡ ሲሆን የነበሩበት ደረጃ ገና ስለነበር እጣ ውስጥ ስላልገቡ፣የተለጠፈባቸው ቁጥር በተለያየ ምክነያት ተገንጥሎ፣ የተሻለ ጥራት ያላቸው ቁጥሮች ለመለጠፍ እየተሠራ ስለሆነ ሊቀየሩ ተነስተውና መሰል ችግሮች ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

በዛሬው እለት ከኃላፊዋ ጋር የነበረው ስብስባ ይህን የሚመስል ሲሆን በዋናነት እጣ የወጣባቸውን ቤቶች ለማስተላለፍ ያላቸውን ፍላጎት የገለፁ ሲሆን ቁርጥ ያለ የማስተላለፊያ ቀን ግን ሳይናገሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚል ለትርጉም በጣም ክፍት የሆነ ጥቅል ንግግር ሊያልፉት ችለዋል፡፡ አጭር ጊዜ የሚለውን እንደ መልስ ለመቀበል በጣም አስቸጋሪ ሲሆን ለምሳሌ 1 ወር በአንፃራዊነት ለአንዱ አጭር ጊዜ ለሌላው ደግሞ ረጅም ጊዜ ሊሆን ይችላል፤በተመሳሳይ አንድ አመትም እንዲሁ በአንፃራዊነት ለአንዱ አጭር ጊዜ ለሌላው ደግሞ ረጅም ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡አንድ እቅድ በጊዜ የተገደበ፣የሚለካ፣ተደራሽና ግልፅነት ያለው ካልሆነ እቅድ ለማለት ያስቸግራል፣በአጭር ጊዜ ለማሰተላለፍ አስበናል የሚለውም እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚሀ አጭር ጊዜ በራሱ መለኪያ የሌለው ጥቅል ንግግር ስለሆነ የዛሬው ስበሰባ ተስፋችንን ከማለምለም የተረፈ ተጨባጭ ውጤት ሳይገኝበት ቀርቷል፡፡

Report Page