2020

2020

https://t.me/feleginfo https://www.nature.com/immersive/d41586-020-03435-6/index.html

በዓመቱ በቀዳሚነት ሳይንስን ያነፁት ሰዎች

እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆቹ 2020 በሳይንስ ላይ ብዙ ተፅእኖ ያሳደሩ ታላለቅ ሰዎችን አሳይቶናል፡፡ ለዛሬ የኔቸር ጆርናል በአመቱ ውስጥ ሳይንስን አንፀዋል ብሎ የመረጣቸውን አስር ሰዎች ከነስራቸው ይዘንላችሁ መጥተናል፡፡

ቴዎድሮስ አድሀኑም፤

ቴዎድሮስ አድሀኑም

የኢቦላ ወረርሺኝን ተከትሎ የነበረውን ስኬታማ ያልሆነ ምላሽ ተከትለው ነበር በዓለም ጤና ድርጅት ታሪክ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ዋና ፀሀፊ ሆነው እ.አ.አ በ2017 የተመረጡት፡፡ በቀጣዩ ዓመት 2018 ላይ ግጭት ቀጠና ውስጥ በነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሺኝ ሲቀሰቀስ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት እና 300 ሺህ ያህል ሰዎች ክትባቱን እንዲያገኙ በማስቻላቸው ሙገሳን አግኝተዋል፡፡ ቴዎድሮስ በሚያሳዩት የሌሎችን ችግር እንደራስ የማየት፣ ጠንካራ ስራ እና ቅርበት የብዙዎቹን የጤናው ዘርፍ ተመራማሪዎች እና አጥኚዎችን ልብ ገዝተዋል፡፡ ሆኖም እርሳቸውንም ሆነ የሚመሩትን ተቋም በ2020 ዓለምን ሲያምስ የቆየው ኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከሰትን ተከትሎ ወሳኝ ሚናን እንዲጫወቱ ሆኗል፡፡ እርግጥ በአንድ በኩል ወረርሺኙ በቻይና በተነሳባቸው የመጀመሪዎቹ ሰዓታት ወቅት ምላሻቸው የዘገየ ነበር የሚል ትችት ቢነሳባቸውም (ተቋሙ ባይቀበለውም) በሌላ በኩል ግን በስራቸው ሙገሳን ተችረዋል፡፡

ቨሪና ሞሀፕት፤

ቨሪና ሞሀፕት

Multidisciplinary drifting Observatory for the Study of Arctic Climate (MOSAiC) በተባለው አርክቲክ ላይ በተካሄደው የአንድ ዓመት ተልዕኮ ውስጥ የሎጅስቲክ አስተባባሪ የነበረችው ቨሪና ሞሀፕት አደገኛ እንስሳትን እና አስቸጋሪ ቅዝቃዜን በመቋቋም የአየር ንብረት ለውጥ መረጃዎችን የሚሰበስቡ ተመራማሪዎችን ስትጠብቅ አሳልፋለች፡፡ ተልዕኮው እሳካሁን አርክቲክ ላይ ከተደረጉት አሰሳዎች ሁሉ ትልቁ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን አየር ንብረት አካባቢውን ብሎም ዓለምን እንዴት እንደሚለውጥ የሚያሳዩ መረጃዎችን ይዞ የመጣም ነበር፡፡ ቨሪና የ300 ያህል ተራማሪዎችን ደህንት ሀላፊነትን ወስዳ ከዱሩ ጋር በመጋፋት ለተልዕኮው ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክታለች፡፡

ጎንዛሎ ሞራቶሪዮ፤

ጎንዛሎ ሞራቶሪዮ

የስነ-ቫይረስ ባለሙያ የሆነው ጎንዛሎ ኡራጋይ በኮሮና ቫይረስ ላይ ባሳየችው ስኬት ውስጥ ትልቁን ሚና ከሚጫወቱት ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ጎንዛሎ እና የቤተ ሙከራ አጋሮቹ ቫይረሱን መለየት የሚያስችል የራሳቸው የሆነ መመርመሪያ በማዘጋጀትና ኋላም ይህን መመርመሪያ ወደ ቀላል እነ ወጪ ቆጣቢ ኪት በመቀየር ብሎም የሀገሪቱን የኮቪድ-19 ህክምና ትስስር በመወጠን ትልቅ አውንታዊ ሚናን ተጫውተዋል፡፡ ብዙዎች የኡራጋይ ዜጎች ቀድሞ ምርመራ የተካሄደላቸው ሲሆን አሁን ላይ በሀገሪቱ ነገሮቸ ወደ ቀድሞው አኳሀን ተመልሰዋል፡፡

አዲ ዉታሪኒ፤

አዲ ዉታሪኒ

የህብረተሰብ ጤና ተመራማሪ የሆኑት አዲ ዉታሪኒ በየዓመቱ በዓለም ዙርያ 400 ሚሊዮን ሰዎችን የሚያጠቃው ዳንጊ ትኩሳት በሽታን ሊያጠፋ የሚችለውን ቴክኖሎጂ ሙከራን መርተዋል፡፡ አዲ እና ቡድናቸው ቫይረሱን ማሰራጨት እንዳይችሉ የተደሩ ትንኞችን በመልቀቅ በአንዳንድ የኢንዶኔዢያ ክፍሎች ውስጥ ይህ አደገኛ ወረርሺኝ ስርጭት በ77 በመቶ እንዲቀንስ ያስቻሉ ሲሆን ለዓመታት የቆየው ተልዕኳቸው በዚህ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ወቅትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ለብዙዎች መድህን ሆነዋል፡፡

ካትሪን ጃንሰን፤

ካትሪን ጃንሰን

በአሜሪካኑ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ፋይዘር ውስጥ የክትባት ጥናት ኃላፊ የሆኑት ካትሪን ጃንሰን አሁን ላይ ለሰዎች መሰጠት የተጀመረውን የፋይዘር ኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ደህንነቱን ጠብቆ በዚህ ፍጥነት እውን እንዲሆን አስችለዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም እንደ ፈንጣጣ እና ሂውማን ፓፒሎሞ ቫይረስ (HPV) ላሉት ክትባት እንዲመጣ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረጉት ካተሪን በኮቪድ-19 ክትባት ፍለጋ ውስጥ የመሪነቱን ድርሻ በመውሰድ ለስኬት ማብቃት ችለዋል፡፡

ዣንግ ዮንዠን፤

ዣንግ ዮንዠን

እኚህ ተመራማሪ ኮቪድ-19ኝን የሚያመጣው የሳርስ-ኮቭ-2 ቫይረስን አር.ኤን.ኤ ስንስል ከማንም ቀድመው ለዓለም በበይነ-መረብ ላይ ይፋ በማድረግ የተለያዩ ሀገራት ከቫይረሱ ጋር ለሚያደርጉት ግብግብ ትልቁን ድርሻ የተወጡና ክትባቶችን የመፈለጉ ሂደትንም የመጀመሪያውን እርምጃ ተራምደዋል፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረው የሳርስ ቫይረስ ወረርሺኝን ለመለየት ተመራማሪዎች ረጅም ወራትን የፈጀባቸው ቢሆንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር ዣንግ ቫይረሱን ምንነት በአስደናቂ ቅልጥፍና ሊያሳዩን ችለዋል፡፡

ቻንዳ ፕሬስኮድ ዋይንስቲን፤

ቻንዳ ፕሬስኮድ ዋይንስቲን

ቻንዳ ፕሬስኮድ ዋይንስቲን ዳርክ ማተርን በመመርመር ላይ ያለች እውቅ ኮዝሞሎጂስት ስትሆን በታዋቂው ዘ ኒው ሳይንቲስት መፅሔት ላይም በየወሩ ፅሁፎችን ታሰፍራለች፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፤ ቻንዳ በሳይንስ ውስጥ ዘረኝነትን በመታገል ረገድ ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይም ናት፡፡ ከባለፈው ሰኔ አንስቶ ከሌሎች ዝነኛ ተመራማሪዎች ጋራ በመሆን ተቋማት ማህበረሰባዊ ዘረኝነትን እንዲከላከሉ ያለመ እንቅስቃሴን በበይነ-መረብ አማካኝነት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ ይህ ጥረቷ ከፍተኛ ውጤትን እያሳየ ሲሆን የተለያዩ የትምህርት ተቋማት እንቅስቃሴውን ተረድተው በሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ያለውን አግላይነት ለመቅረፍ መስራት እንዳለባቸው ተቀብለዋል፡፡

ሊ ላንዋን፤

ሊ ላንዋን

ሊ ላንዋን የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መነሻ የነበረቸው ዉሀን ከተማ ዝግ እንድትሆን በማድረግ ቫይረሱን ለመነቆጣጠር እንዲቻል ጥረት ያደረጉ ኤፒዲሞሎጂስት ናቸው፡፡ በሾንግ ናንሼን ዩኒቨርሲቲ የአተነፋፈስ ስርዓተ ምሁር የሆኑት እንስቷ ወረርሺኑን እንዲቆጣጠሩ በቻይና መንግስት አማካኝነት ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ወደ ከተማው በተላኩበት ጊዜ ነበር ይህን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡት፡፡ በዚህ ምክረ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የቻይና መንግስት ሁሉም የከተማው ነዋሪ በቤቱ እንዲቆይ ያዘዘ ሲሆን ለ76 ቀናት የቆየው ይህ እገዳ በወቅቱ በብዙዎች እንደ አላስፈላጊ ነገር ታይቶ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ይህ ጠንካራ ውሳኔ መልካም ውጤትን ይዞ የመጣ ሆኗል፡፡

ጃሲንድራ አርደን፤

ጃሲንድራ አርደን

የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚንስትር ሀገራቸው የኮቪድ-19 ወረርሺኝን በብቃት እንድትመክት በማድረግ አለም ዓቀፍ ሙገሳን አግኝተዋል፡፡ 6 ሰዎች ብቻ በኮቪድ 19 ተይዘው ባሉበት ሰዓት ጠቅላይ ሚንስተሯ ወደ ሀገራቸው የሚገቡ ሰዎች እራሳቸውን ለሁለት ሳምንታት ለይተው እንዲያቆዩ፣ የጉዞ እገዳዎች እንዲተላለፉ፣ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ በሽታው ቁጥጥር እንዲዞር እና ሌሎችም መሰል ወሳኝ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ እነዚህን የጠቅላይ ሚንስትሯ እርምጃዎች ተከትሎ ሀገሪቱ እስካሁን ከአምስት ሚሊዮን ህዝቧ ውስጥ 2 ሺሁ ብቻ በወረርሺኙ ሲያዝ ሟቾችም 25 ብቻ ሆነዋል፡፡

አንቶኒ ፋውቺ፤

አንቶኒ ፋውቺ

ከአርባ ዓመታት በላይ በዘለቀ ግልጋሎታቸው አንቶኒ ፋውቺ ስድስት የአሜሪካን ፕሬዘዳቶችን በባዮሎጂያዊ መሳርያዎች፣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ ኢቦላ እና ዚካ ቫይረሶች ዙርያ ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ቆይታቸው ውስጥ የተለያዩ ትችቶችን እና ሙገሳዎችን አፈራርቀው ያገኙት አንቶኒ ፋውቺ በዚህ ዓመት ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ መነሳትን ተከትሎ ሀገራቸውን በከፍተኛ ትጋት እያገለገሉ ናቸው፡፡ በወረርሺኙ ለዜጎች ብስለት በተሞላበት መልኩ ሳይንሳዊ መልዕክትን እያስተላለፉ ያሉት አንቶኒ ከመጪው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ጋራም የኮቪድ-19ን ስርጭት መግታት ላይ እንደሚሱ የተነገረ ሲሆን ሌሎች የህብረተሰብ ጤና ተግዳሮቶችን ለማቆም በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ከፊት ሆነው ሚናቸውን እንደሚጫወቱ ይጠበቃል፡፡

(Techin.gov.et)

Report Page