#15

#15


ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በአማራ ክልል በተፈጠረው የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያና ተያያዥ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች የተጠረጠሩ 57 ተከሳሾች ከእስር ተፈቱ::

ከተጠረጣሪዎች መካከል በነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 57 ጉዳያቸው ተጣርቶ ሐምሌ 19 ቀን 2011ዓ.ም ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል።

እነ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮለኔል አለበል አማረና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን በተመለከተ ደግሞ ችሎቱ ተጨማሪ የ10 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ትናንት በባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት 13ኛ ወንጀል ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ ቀርበው ጉዳያቸው የታዬ ሲሆን ተጠርጣዎች መካከልም ከወንጀሉ ነፃ የተባሉ 57 ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ ተደርጓል፡፡

በዚህ መዝገብ 218 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ቢሆንም ቀደም ሲል 103ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቃቀቸው ተገልጿል፡፡

ቀሪዎቹ ችሎት ከቀረቡት መካከልም ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮለኔል አለበል አማረና ኮለኔል ባምላኩ ዓባይን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ይገኙበታል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች እንዳሉት ፖሊስ ጉዳዩን በአግባቡ እያየና የማጣራት ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ነገር ግን በወቅቱ ጥቃት ሊሰነዘርባቸውና ታግተው የነበሩ ከችግሩ በተአምር የተረፉ ኮለኔል አለበል አማረና ኮለኔል ባምላኩ ዓባይ እስካሁን ተጨባጭ ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው በምርመራ ቡድኑ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ የተፈጠረውን ችግር ለመመከት ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውን እየተካሄደ ባለው ምርመራ መረጋገጡንና እስካሁን ማስረጃ አለመገኘቱን ጠበቆቹ አቅርበዋል።

በመሆኑም በስም ተጠቃሾቹ በጉዳዩ የተሳተፉ አለመሆናቸው በተካሄደው ምርመራ እየታዬ በመሆኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጣቸው መዝገቡ ተዘግቶ እንዲለቀቁ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

ከተጠርጣሪ እስረኞች መካከል የመቁሰል አደጋ ያለባቸው ተጠርጣሪዎች ስማቸው ተዘርዝሮ ሕክምና እንዲያገኙ ችሎቱ እንዲያዝዝም ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

ኮለኔል አለበል አማረ በበኩላቸው “ከታሰርን ጀምሮ አመላካች ውጤት ባለመገኘቱ ቤተሰቦቻችን እየተጎዱ በመሆኑና የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናችን ፍርድ ቤቱ ጉዳያችንን በአግባቡ መዝኖ ሊለቀን ይገባል” ብለዋል፡፡

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ደግሞ “ችግሩ እንዳይሰፋና ወደ ከፋ ጫፍ ሁኔታ እንዳይሄድ ያስቆምኩት እኔ ነኝ” ብለዋል፡፡

“እስካሁንም በምርመራው መዝገቡም ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም፤ ምንም በሌለ ጉዳይ መታሰሬ አግባብ ባለመሆኑ ልለቀቅ ይገባል” ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪዎች ጉዳይ በጥንቃቄና በፍጥነት እየታዬ ነፃነታቸው የተረጋገጡ እየተፈቱ መሆኑን አስረድቷል።

ይሁን እንጂ አሁንም ከታሰሩት መካከል ቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፉ እንዲሁም ከችግሩ ነፃ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ጉዳዩን በሰውና በቴክኒክ ማስረጃ ማጣራት ተደርጎ ከወንጀሉ ንጹህ የሆኑ ሰዎች እንደሚፈቱም አስታውቋል።

“ከጉዳዩ ነፃ የሆኑ ሰዎችን በምንም መንገድ ቢሆን አላግባብ የሚወነጅል የለም፤ መጣራቱ ለተጠርጣሪዎችም ቢሆን ጠቀሚ ነው” ብሏል።

በመሆኑም እስካሁን ያልተጣሩና መጣራት ያለባቸውን ጉዳዮች በሰውና በቴክኒክ ማስረጃ ለማጣራት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲያዙና መታከም ያለባቸው ቁስለኞች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ቀደም ሲል ማዘዙን አስታውሶ በድጋሜ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፖሊስ ያልጨረስኩትና ማጣራት ያለብኝ ጉዳይ አለ ብሎ ከጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውስጥም 10 ቀን ችሎቱ በመፍቀድ ሐምሌ 29/2011 ዓ.ም እንዲቀርቡና እስከዚያው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Via AMMA

Report Page