1200

1200

Selam_et

በደቡብ አፍሪካ የንግድ መዲና ጆሀንስበርግ ልዩ ስሙ ጂፒ አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት "1200 መታሰራቸውን" ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።


በጂፒ አካባቢ የሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አቶ ተከስተ ሹምዬ ለቢቢሲ እንደተናገረው በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 1/2011 ዓ.ም ጠዋት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ከተለያየ መስመር በመሆን ቦታውን በመዝጋት ወደ አካባቢው መጥተው ህገወጥና ሐሰተኛ ምርቶችን እንቆጣጠራለን በማለት የጅምላ እስር መፈጸማቸውን ገልጿል።


አቶ ተከስተ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ምክንያት አፈሳ ይኖራል በሚል የንግድ ቦታቸውን ዘግተው እንደነበርም ያስረዳል።

በአካባቢው የተገኙ ግለሰቦች ያለምንም ማጣራት መታፈሳቸውንና ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውን ገልጾ፤ ያላቸው ሕጋዊ ወረቀት እንዲሁም ከሳምንት በፊት በተከሰተ ግጭት በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ያልተሳተፉ መሆናቸው ተጣርቶ እንደሚፈቱ መገለፁንም ይናገራል።

"በትናንትናው ዕለት ፖሊሶች ቀኑን ሙሉ ሰዎችን ሲያፍሱ ነበር" የሚለው ተከስተ የእሱም ምግብ ቤት ተዘግቶ ፖሊሶች በአካባቢው ሰዎች እንዳይዘዋወሩ በመከልከላቸው ሰራተኞቹ ከውስጥ ተቆልፎባቸው ማምሸታቸውን ገልጿል።

አቶ ተከስተ ወደ ሥራ አካባቢው በደረሰበት ወቅት ስፍራው ከፍተኛ ቅጥር ባለው የፖሊስ ኃይል ተከቦ የነበረ ሲሆን፤ እሱም ክስተቱን በርቀት መከታተሉንና በኋላም ወደ ሬስቶራንቱ ማምራቱን ይናገራል።


"ምንም እንኳን የፖሊሶቹ ምክንያት ህገወጥ (ሐሰተኛ ምርቶችን) ለመቆጣጠር የሚል ቢሆንም በህጋዊ መንገድ ከቻይና እቃ ከሚያስመጡ ሰዎች ላይ በርካታ እቃዎች ተወስደዋል፤ ከህገወጡ በበለጠ የተጎዱትም እነዚህ ናቸው። ህገወጥ ህገወጥ ነው ማንም ቢሆን የሚከላከላቸውም ሆነ ተዉ የሚላቸው አካል የለም። ግን በህጋዊ መንገድ የሚሰራውን ነጋዴ በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ አድርሶበታል" ይላል።

ፖሊሶች ከሄዱ በኋላ ወደ አመሻሽ ላይ በቅርብ ርቀት የሚኖሩ ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ለዘረፋ መጥተው የነበሩ ሲሆን መጠነኛ ግጭትም ተፈጥሮ ሳይባባስና ችግር ሳይፈጠር በሰላም እንደተፈታም ይናገራል።

ተከስተ እንደሚናገረው ይህ ጉዳይ አሁን የተፈጠረ ሳይሆን ከባለፉት ስምንት ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ነገር መሆኑን ያስረዳል።

ለብዙ ስመጥር የስፖርት አልባሳት ኩባንያዎች ተወካይ የሆነ አንድ ግለሰብ በፖሊስ ታጅቦ ኢትዮጵያዊያን በሚነግዱባቸው ቦታ በመምጣት ሐሰተኛ ብራንድና ህገወጥ ናቸው በሚል በተደጋሚ እቃዎችን እንደሚያስወስድ አቶ ተከስተ ይናገራል።


አክሎም እቃዎቹ በህጉ መሰረት መቃጠል ወይም ለመንግሥት መግባት የነበረባቸው ቢሆንም በተለያዩ ግንኙነቶች የተወሰዱት እቃዎች ተመልሰው እዚው ቦታ ገበያ ላይ መዋላቸው በንግዱ ላይ በተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ምሬት መፍጠሩንም ያስዳል።

"ህገወጥ ነው ተብሎ ከተወሰደ ወይ መቃጠል ነው ያለበት ወይም ለመንግሥት ነው መግባት ያለበት ነገር ግን ተመልሶ ገበያ ላይ የሚገኝ ከሆነ ዘረፋ ነው የያዙት ማለት ነው" ይላል።

በተለይም በተወሰነ ጊዜ ይመጣ የነበረው ግለሰብ በተደጋጋሚ በወር እስከ አራት ጊዜ ድረስ መምጣቱ ኢትዮጵያዊያኖችን እንዳሰላቸ ገልጿል። ግለሰቡ ሲመጣም ለአንድ ህንፃ የሚሆን የፍርድ ቤት መፈተሻ ወረቀት ይዞ ቢመጣም ያልተፈቀደለትን ሁሉንም ሱቆች እንደሚፈትሽ ይገልፃል።


አብዛኛውን ጊዜም በፖሊስ ታጅቦ ከመምጣቱ አንፃር ብዙው ኢትዮጵያዊያን እሱን የመጋፈጥ አቅም እንደሌላቸው ተከስተ ያስረዳል።

ግለሰቡ እየገፋ መጥቶ የሰዎችን ንብረት መንጠቅና ማጉላላት፣ አካላዊ ጥቃት፣ መገፍተርና ማመናጨቅ በመደጋገሙ የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ክስ አቅርበው ጉዳዩም በፍርድ ሂደት ላይ እንደሆነ ኢትዮጵያዊያኑ ይናገራሉ።

በፍርድ ሂደቱም ምክንያት አካባቢው ላይ እንዳይደርስ በመከልከሉ ያልመጣው ይህ ግለሰብ ከጥቂት ቀናት በፊት በብረት ለበስ መኪና ተጭኖ ከፖሊሶች ጋር የመጣ ሲሆን በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ድንጋይ መወርወር እንደጀመሩ ተነግሯል።

"ባልተጠበቀ ሰዓት እየመጣ ነገር በመቆስቆሱ፤ ሰዉ ደግሞ ብዙ ንብረት ስለተወሰደበት፤ የፍርድ ሂደቱን ጥሶ በመምጣቱ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጠረ፤ ድንጋይም መወርወር ተጀመረ" በማለት ኢትዮጵያዊያኑ ይናገራሉ።


ይህ ሁኔታም በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የሃገሪቱ መገናና ብዙሃን "እንዴት ግለሰቦች ፖሊስ ላይ ድንጋይ ይወረውራሉ" በሚል ጉዳዩ እንደተካረረ የሚናገረው በጂፒ አካባቢ በግል ሥራ የሚተዳደረው ሔኖክ ለማ ነው። እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ቁጣን እንደቀሰቀም ይናገራል።

ተከስተ እንደሚለው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በከፍተኛ ሁኔታ ከመሰራጨቱ ጋር ተያይዞ ይህ አፈሳ መካሄዱን ይገልፃል።


ይህም ሁኔታ እስከ ላይኛው የመንግሥት አካል በመድረሱ ትላንት ለተፈጠረው የጅምላ እስር ምክንያት መሆኑንም ያስረዳል። በእስር ላይ ስላሉ ግለሰቦች ዘርዘር ያለ መረጃ እንደሌለው የገለፀው ተከስተ እንደ ቀድሞው ከሆነ በሰባት ቀን ውስጥ ሊለቀቁ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።

ሔኖክ በበኩሉ ብዙ ኢትዮጵዊያን እስርን በመፍራት ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ጓደኞቻቸውን ሊጠይቁ አልቻሉም ብሏል። አሁንም ጂፒ አካባቢ የሚገኙ ሱቆች ዝግ ሲሆኑ በአካባቢው ውር ውር የሚሉ ግለሰቦች እንዳሉ ተከስተ ይናገራል።

የትናንቱን ክስተት ተከትሎ ሰባት የፖሊስ መኮንኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አሳውቋል። ከሰባቱ ፖሊሶች መካከል አምስቱ በህገወጥነት የተወረሱ ሸቀጦችን መልሰው ለሱቆቹ ባለቤቶች በመሸጥ እንደሚከሰሱ የተነገረ ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ ፖሊስ ሊያካሂድ ስላቀዳቸው አሰሳዎች ቀድመው መረጃ በመስጠት ተከሰዋል።

በርካቶች ለእስር በተዳረጉበት የትናንቱ አሰሳ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ህገወጥና ሐሰተኛ ሸቀጦች መያዛቸውን እንዲሁም በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ተጠርጣሪ ህገወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አሳውቋል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ኢትዮጵያዊያን በፖሊስ የተያዙት ወገኖቻቸው አንድ ሺህ ሁለት መቶ እንደሚደርሱ ይናገሩ እንጂ ፖሊስ እስካሁን ስለተያዙት ሰዎች ዜግነትና አሃዝ በይፋ ያወጣው መረጃ የለም።

Report Page