02

02

የግንኙነት እና ሚዲያ ክፍል ሰብሳቢ፡ ◦•●◉✿dersolgne @ dGb.ms✿◉●•◦

ዝክረ ቅዱሳን ዘኅዳር 2

November 7, 2022

✝✞✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ


✝✞✝ ኅዳር 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+" አባ ዼጥሮስ ሣልስ "+


✝✞✝ 'ዻዻስ' ማለት 'አባት-መሪ-እረኛ' ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው::

+ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር 'ሸክም: ዕዳ' ሲሆን በሰማይ ግን 'ክብር' ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም::


+ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ-ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ 'ሹሙኝ' ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው::

+አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ-መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት / ዽዽስና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::

+አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች 4ቱ የበላይ ናቸው:: እነዚህም የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::


+እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::


+የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::


+በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ ዼጥሮስ ሣልሳዊ ነው::


+ሣልሳዊ መባሉ ከእርሱ በፊት በዚህ ስም ተጠርተው በመንበረ ማርቆስ ላይ የተቀመጡ 2 ፓትርያርኮች ስለ ነበሩ ነው:: ቅዱስ ዼጥሮስ ቀዳማዊ 'ተፍጻሜተ ሰማዕት' (የሰማዕታት ፍጻሜ) የተባለው ሲሆን 17ኛ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

+ቅዱስ ዼጥሮስ ካልዕ ደግሞ በ370ዎቹ አካባቢ 21ኛ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ የተሾመና የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ደቀ መዝሙር የነበረ አባት ነው:: ዛሬ የምናስበው አባ ዼጥሮስ ደግሞ በ470ዎቹ አካባቢ ሊቀ ዽዽስናን በግብጽ ተሹሞ ያገለገለውን ነው::


+ወቅቱ መለካውያን (የኬልቄዶን ጉባኤ አማኞች) የሰለጠኑበት በመሆኑ ሁኔታዎች ትንሽ አስቸጋሪ ነበሩ:: አንደኛ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2 የተከፈለችበት ጊዜ በመሆኑ ፈተናው ለእረኞች ቀላል እንዳይሆን አድርጐታል:: ሌላውና ዋናው ፈተና ግን በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት ለመለካውያን (ለመናፍቃን) ወግነው ምዕመናንን ማሳደዳቸው ነው::


+አባ ዼጥሮስ ከተመረጠ በኋላ አስቀድሞ ያደረገው አጋዥ መፈለግ ነበር:: እግዚአብሔር ሲረዳው የታላቂቱ ሃገር የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የሆነው ቅዱስ አካክዮስን አገኘ:: ከእርሱ ጋርም ደብዳቤ ይጻጻፉ ያዙ::


+ደብዳቤ ሲባል ግን እንዲህ እኛ በዘመኑ እንደምንጽፈው ያለ አይደለም::ይልቁን 5ቱ አዕማደ ምሥጢራትን የተሞሉ ጦማሮች ነበሩ እንጂ:: 2ቱ አበው በየሃገራቸው እየዞሩ እየሰበኩ: አልደርሱበት ባሉበት ቦታ ደግሞ ክታቦችን እየጻፉ በአንድነት ስለ ቀናች ሃይማኖት ደከሙ::


+በእግዚአብሔር ቸርነትም ተሳካላቸው:: አባ ዼጥሮስ በዚህች ቀን ሲያርፍ መሰሉ 'ካልእ አትናቴዎስ' ተክቶታል:: ከፈጣሪውም እሴተ ኖሎትን (የእረኝነት ዋጋውን) ተቀብሏል::


+አምላከ አበው ዻዻሳት መንጋውን በርሕራሔ የሚጠብቁ እረኞችን ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::


+ኅዳር 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ሣልስ

2.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት

3.ቅድስት ሴቴንዋ ነቢይት

4.ቅድስት አንስጣስያ


>+"+ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና:: ወንጌልን ብሰብክ እንኩዋ የምመካበት የለኝም:: ግድ ደርሶብኝ ነውና:: ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ:: ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና:: ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል:: እንግዲህ ደመወዜ ምንድን ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው:: +"+ (1ቆሮ. 9:15)


<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Report Page