*/

*/

Source

ህገ-መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን በኃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል እና በሀገር ክህደት እንዲሁም ከህወሓት ጸረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተልዕኮ በመፈጸም የተጠረጠሩ ብርጋደር ጄነራር ክዱ አለሙ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በኬኒያ ሀገር ወታደራዊ አታሼ ሆነው እንዲሰሩ ተመድበው እያሉ በመንግስትና በህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከሌሎች ሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመከላከያ አመራሮች ጋር በመሆን የሀገሪቱን ወታደራዊ ሚስጥር ለሌሎች ሀገራት አሳልፈው ሲሰጡ የነበሩ መሆናቸውን የሚገልጽ መረጃ ማግኘቱን መርማሪ ፖሊስ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቅርቧል፡፡

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ኬኒያ ላይ ሆነው የሳተላይት ስልኮችን በመጠቀም ወታደራዊ ድጋፍ ሲሰጡና ሲመሩ እንደነበር መረጃ ማግኘቱንም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤርፖርት ድርጅት በህወሓት ህገ-ወጥ ቡድን በተከፈተው ጦርነት የደረሰበትን የጉዳት መጠን፣በትግራይ ክልል በነበሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላትና በተቋማቱ ላይ የደረሰው የንብረት ውድመት፣የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ህይወታቸው ያለፉ አባላትን በተመለከተ መርማሪ ፖሊስ ማስረጃ ማስመጣቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ከተለያዩ ባንኮች፣ከብሔራዊና መረጃ ደህንነት የተጠየቁ ማስረጃዎችና ከተጠርጣሪው መኖርያ ቤት የተገኙ ለምርመራ የተላኩ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የምርመራ ውጤት ያለበትን ሁኔታ የመከታተል ስራ ከዚህ ቀደም በተፈቀደለት የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ አከናውኛለሁ ያለውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ሆኖም ግን ከምርመራው ስፋትና ውስብስብነት አንጻር የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጣርቶ ለማጠናቀቅ፣ከተለያዩ ባንኮች የተጠየቁ ማስረጃዎችን ለማስመጣትና በውጤቱ የምርመራ ስራ ለማከናወን፣የምስክሮችን ቃል የመቀበል ስራ ለመስራት፣በትግራይ ክልልና በአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች በህገ-ወጥ የህወሓት ቡድን በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችና የወደመ ንብረትን በተመለከተ የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን ለማስመጣት፣ለምርመራ ከተላኩ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የምርመራ ውጤት ለማስመጣትና ሌሎች ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ የሚቀረው መሆኑን በመግለጽ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ በማሰባሰብ ላይ ያሉ የተለያዩ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን ሊያጠፉና ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመቀላቀል ተጨማሪ ወንጀል ሊፈጽሙ ስለሚችሉ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት መርማሪ ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል ተጠርጣሪው በጠበቃቸው አማካኝነት የአስም በሽታ ታማሚ መሆናቸውን ለችሎቱ በማስረዳት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከደመጠ በኃላ መርማሪ ፖሊስ ቀረኝ ያለውን ሌሎች የሰውና የቴክኒክ ማስረጃዎችን እንዲያሰባስብ ተጨማሪ 11 የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡(ፌዴራል ፖሊስ)

Report Page