*/

*/

Source

“ጠይቄ አስጠየቄ እስኪ ልቋጠራት፣
የእነ ብረት አስጥል የእነ ንቦ ዘር ናት”

ማኅጸነ ለምለም፣ ዙፋን ላይ ሆና የምትፈርድ፣ ሲርብ በእናት አንጄት የምታጎርስ፣ ሲከፋ የምትዳስስ፣ ሲታረዙ የምታለብስ፣ ሀገር ሲጠቃ የምትተኩስ ሴት ከወዴት አለች? ቢባል ከኢትዮጵያ ነው።

እንደ እናት ታዝናለች፣ ትፀልያለች፣ አሳምራ ታሳድጋለች፣ እንደ አባት ታስታጥቃለች፣ ለራሷም ትታጠቃለች፣ እንደ አርበኛ ትተኩሳለች፣ መቀነት ታጥቃ እንዳይፈታ አጥብቃ ጠላትን በመመለስ ለሀገር ጠበቃ ትሆናለች። የሌላው ዓለም እናት ጀግና ልትወልድ ትችላለች፣ የኢትዮጵያ እናት ግን ጀግና ወላድ ብቻ ሳትሆን ጀግናም ናት።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት በተደረጉ ጦርነቶች ሴቶች ደጀን ሆነው በመተኮስ፣ ወገን ሲጎዳ ደም በማበስ፣ ሲሞት አፈር በማልበስ፣ ሲራብ በማጉረስ፣ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ስልት በመቀየስ ለተመዘገቡት ድሎች ሁሉ የሴቷ እጅ አለበት። ኢትዮጵያዊት እናት ፈሪ ልጅ አትወልድም፣ ፈሪ ሰው አትወድም። “ተኳሽ እወዳለሁ ገዳይም አልጣላ፣ ሲደክመኝ አርፋለሁ ከጎፈሬው ጥላ” እያለች እልፍ ጀግኖችን ታፈልቃለች።

ኢትዮጵያዊ መሆን ያኮራል፣ ስሙ ብቻ ያስከብራል። ለምድር የተሰጠው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ። ኢትዮጵያ ለዓለም መኖርና ለስልጣኔ መፈጠር ቀዳሚዋ ናት። ቀዳሚዋ ከሌለች ተከታዮቹ መኖር አይቻላቸውምና፣ ዳሩ ኢትዮጵያ የፈጣሪውን ቁጣ በፀሎት፣ የጠላትን በትር በጥይት የምትመልስ ሀገር ናትና ምንም አትሆንም።

“ሀገራችን ኢትዮጵያን ባርካት ቀድሳት፣ ሰላም ስጣት ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት፣ ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት አድርግላት” የሚለው የካህኑ ልመና “ሰላም ይሁን የሚለው የሼሁ ዱዓ” የማይታዩ ነገር ግን የማይሸነፉ አሳልፈው የማይሰጡ የኢትዮጵያ ሚስጥራዊ ወታደሮች ናቸው። ለሚስጥር እና ለምስክር የተፈጠረች ሀገር ፍፃሜ ዓለም እስኪደርስ ድረስ ትቆያለች እንጂ አትሰጋም።

የማይፈሩና የማይደፈሩ ምድራዊ ወታደሮች፣ ረቂቅ ሰማያዊ ጠባቂዎች ያሏት ሀገር ናት። ሰውና ፈጣሪ፣ ሰውና መላዕክት በስስት የሚመለከቷት አብዝተው የሚወዷት፣ በደስታ የሚጠብቋት ሀገር ናት ኢትዮጵያ። የዓለም ዓይኖች ሁሉ ሊያይዋት ይመኟታል። በክፉ ያዩዋት ይጠፉባታል። በመልካም ያዩዋት ደግሞ ይከብሩባታል። ኢትዮጵያ ለደጎች እንጂ ለክፉዎች ቦታ የላትም። መሰረቷም ደግነት፣ አንድነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ብልህነት፣ ጠበብትነት፣ አይደፈሬነት፣ ጀግንነት እና አሸናፊነት ነው።

የራያን ምድር አይቼ፣ በባሕላቸው ተደስቼ፣ በፍቅራቸው ተረትቼ፣ የግራ ካሶን ዳገት ወጥቼ፣ ኮረምን ተመልክቼ በወፍላ ተራራዎች ተገኝቼ ነበር። ብርዱ ልብ ያንሰፈስፋል። እጅ ያደነዝዛል። ተራራዎቹ ፈታኞች ናቸው። በወፍላ ተራራዎች ከቆቦ ተነስቶ፣ በግራ ካሶ ታላቅ ጀብዱ ፈፅሞ፣ ኮረምን አረጋግቶ፣ ጠላቱን አፅድቶ የትህነግን ታጣቂ እየደመሰሰ የሄደው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ይገኙበል። በማይሸሸው ልባቸው፣ በሚያነጣጥረው ዓይናቸው አካባቢውን እየጠበቁት ነው።

አጥንት በሚሰረስው ብርዳማ ተራራ በፅናት እና በኩራት ለወገንና ለሀገር የቆመውን ሠራዊት ሳይ ደነቀኝ። ለእኛ ሙቀት የሚሰጡት እነርሱ እየበረዳቸው ነው። ለእኛ መኖር እነርሱ ሞተው ነው። ለእኛ ሰላም ማደር እነርሱ እንቅልፍ አጥተው ነው። ለወገን መልካም ሕይወት ሲሉ የእነርሱ ሕይወት በዱር በገደል፣ በተራራ በጉድብ ሆኗል። መታደል ነውና ይሁን ብዬ አለፍኩ።

ትጥቅና ስንቅ አንግተው፣ በእግራቸው እየተጓዙ፣ በግራ ካሶ ተራራ እየተኮሱ ድል እየነሱ የሄዱና በወፍላ ተራራዎች ለወገን ዘብ የቆሙ ሴቶችን አየሁ። “ገና ሲወለድ እራሱን ሲላጭ፣ ይቅለበለባል እጁ ከምላጭ” እንዳለ እጃቸው ከመሳሪያቸው ምላጭ አጠገብ አይታጣም። ዓይናቸው እንደ ንስር ነው። አካባቢውን በንቃት ይመለከታሉ። የሴትነት ውበት አላሳሰባቸውም አፈር ምሰው ድንጋይ ተንተርሰው ያድራሉ እንጂ። የእነርሱ ውበት የወገናቸው ሰላምና ደስታ ነው። ስለ

ወኔያቸውን በአንደበታቸው መስማት ፈለኩ። አናገርኳቸው። ጀግኖች ብቻ ሳይሆኑ ትሁትም ናቸው። በዚያ ውጊያ መሪና ተመሪ አልነበረም። መሪው ቀድሞ ይገባል። ስልት እየቀየሰ ራሱም እየተኮሰ ነበር የሚገባው። ይህ ደግሞ ለልዩ ኀይሉ መነሳሳት የፈጠረ ነበር። ሴት የልዩ ኀይል አባላት ከወንድ የልዩ ኃይል አባላት እኩል ግዳጅ ሲፈፅሙ እንደነበር ጓደኞቻቸው መስክረውላቸዋል። ከነብስ ወከፍ መሳሪያ ጀምሮ እንደ ወንዶች እኩል በመተኮስ፣ ለተራበ በማጉረስ፣ ለተጠማ በማጠጣት ተጋድሎ ሲያደርጉ እንደነበርም ተናግረውላቸዋል።

ሴት የልዩ ኀይል አባላት የሚያሳዩት ጀብዱ ሠራዊቱ ለተጨማሪ ድል እንዲነሳሳ እንዳደረጋቸው ጓደኞቻቸው ነግረውኛል። የትኛውንም ጀብዱ ይፈፅማሉ ነው ያሏቸው።

ምክትል ሳጅን ሕይወት አደመ፣ ኮንስታብል ማስተዋል አወቀና ኮንስታብል ሳዳ ሁሴን በወፍላ ተራራዎች ያገኜኋቸው ጀግኖች ናቸው። በዚያ ብርዳማ ስፍራ በወኔ ቆመዋል። ስለ አየር ንብረቱ ሲጠየቁ ለሀገር ዘብ ሲቆም ሁሉም ነገር ቀላል ነው ይላሉ። በነበረው ዘመቻ በግራ ካሶ ላይ ከጠላት በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ነበር፣ በያዝነው መሳሪያ መልስ እየሰጠን የጠላትን ምሽግ አፍርሰናል፣ ድል አድርገንም እዚህ ተገኝተናል ነው ያሉት።

ሴት ወንድ ሳንል ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ጠላት የሆነውን አስወግደናል ወደፊትም እናስወግዳለን ነው ያሉኝ። ሀሳባቸው በክልል የተወሰነ አለመሆኑን እና ትግላቸው እንደ ኢትዮጵያ መሆኑንም ነግረውኛል። እኛ የአማራነት ጀግንነታችንን ተጠቅመን ለኢትዮጵያ እንቆማለንም ብለውኛል። በውትድርና ሕይወት በተለይም በውጊያ ወቅት ረሃብና ጥም አለ፤ ይህ ግን ለእነዚያ ሴት የልዩ ኃይል አባላት ካላማቸው አላስቀራቸውም።

ለአማራና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲባል ድካም አይደለም ሌላ ነገር ቢመጣ አይቆጨንም፣ ሁሉም በያለበት በወኔና በቁርጠኝነት መሥራት አለበት ነው ያሉት። “ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያውያን እስከ መቼ ነው የሚጨቆኑት የሚለው ለትግል አስነስቶናል፣ በቀጣይም ለሚኖር ግዳጅ ወደኋላ አንልም፣ ለኢትዮጵያ አለንላት፣ ጀግንነታችንና ወኔያችን የተሟላ ነው፣ አይዞሽ እናታለም፣ ኩራትሽ ነን” ሲሉ ነበር በወፍላ ተራራዎች ካገኘኋቸው ጀግና ሴት የልዩ ኃይል አባላት የሰማሁት።

“ጥንካሬ፣ ቆራጥነት፣ ፍቅርና አይበገሬነት አለባቸው። ኢትዮጵያን ሰላም እናደርጋታለን፣ ጀግንነታችን እና ወኔያችን ስንቅ አድርገን እንቀጥላለን፣ ኢትዮጵያም በእኛ ትኮራለች” ነበር ያሉኝ።

ሴት የልዩ ኃይል አባላት የቀደሙት ጀግና ኢትዮጵያዊ እናቶችን ታሪክ ለመድገም ዝግጁ እንደሆኑም ነግረውኛል።

ኢትዮጵያ ጉድብ ውስጥ አድራ አይዞሽ እናታለም አለሁልሽ የምትል ጀግና ሴት እና ከሞቀ ቤት እያደረ ሀብቷን የሚዘርፍ በጉያዋ ይዛለች። በአንደኛዋ ትኮራለች በአንደኛው ታዝናለች። መኩሪያ መሆን ቢያቅት ማፈሪያ ላለመሆን መሥራት መልካም ነው።

“ጠይቄ አስጠየቄ እስኪ ልቋጠራት፣
የእነ ብረት አስጥል የእነ ንቦ ዘር ናት” አዎ ጠይቄ ዘሯን አውቂያለሁ። ኩሩ ኢትዮጵያዊት ናት። ኩሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እንዲህ አይነት ሴት ድሮስ ከዬት ሊገኝና፣ ብንችል ኢትዮጵያ ትኩራብን፣ ሰንደቁ ከፍ ይበልልን፣ ባንችል ግን ኢትዮጵያ አትፈርብን፣ ክብር ሁሉ ኢትዮጵያን ላከበሯት።

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ
ዩቱዩብ
በዌብሳይት
በቴሌግራም
ትዊተር

Report Page