*/

*/

Source

=>+"+ እንኩዋን ለቅዱስ "እንድርያስ ሐዋርያ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::

+ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::

+ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::

+በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት:- "ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ::

(ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ)" ብሏል:: (መልክዐ ስዕል)

+ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:9, 12:22) ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኩዋል::

+ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ::
ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጉዋል::

+ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር (እንዲሁ ሰው) መስሎት <ለጌታችን ስለ ጌታችን> ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::

¤"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ:: ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::

ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል::

+እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር: ብርቱ) ማለት ነው:: ድፍረት ሥጋዊ: ድፍረት መንፈሳዊ አለና:: "ድፍረት ሥጋዊ" በራስ ተመክቶ ሌሎችን ማጥቃት: ለጥቃትም ምላሽ መስጠት ነው::

+"ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ: ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን: ራስን አሳልፎ መስጠት: መከራንም አለመሰቀቅ ነው:: ይሕንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል::

+ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እሥራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧልና "ተባዕ (ደፋር)" ይለዋል:: "ዘኢያፍርሃከ ምንተ መልአከ ዓመጻ ጽኑዕ::

አንተኑ እንድርያረስ ተባዕ" እንዲል:: (መልክዐ ዓቢየ እግዚእ)

+የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት:: ይህቺን ሃገር: አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ዼጥሮስ አስተምሮባታል:: ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል::

+በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም:: ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ: ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ:: በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ::

+ነገር ግን ከብረው: ገነው: ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር:: አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው: ጦርና ጋሻን አስታጥቀው: ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ::

+ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ-ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር 27 ቀን ያከበርነውን ማለት ነው) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ ምዕራፍ (113:12) ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ" አለው::

+ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር:: "አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር:: ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ:: እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ:: አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ . . . የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው:: ዓይን አላቸው: ግን አያዩም:: ጀሮ አላቸው: ግን አይሰሙም::

አፍንጫ አላቸው: ግን አያሸቱም . . ." አለ::

+በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ / የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ" ብሎ ጸጥ አለ:: ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ:: በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ::

+እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማሕበር ቀላቀላቸው:: አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ:: በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ::

+የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ" አለው:: ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምሕሬ ለእንድርያስ እስክነግር ድረስ ታገሠኝ" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው::

+በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው:: ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው:: "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አደይለም" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው::

+ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ:: ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕጻን ነበርና:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ: ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት:: ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት::

+ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው:: ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት:: በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ::

+በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው:: መጀመሪያ የሞተውን ሕጻን ደግሞ ፊልሞና አስነሳው:: በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ: ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ::

+ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ:: ስሟ ባልተጠቀ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው::

+ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት: ደበደቡት አሰቃዩት:: በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው:: ታሕሳስ 4 ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው: ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል::

¤እኛም እንደ አባቶቻችን:-

"እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ:: አንቅሃኒ እምሐኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ::

ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ::" እያል ቅዱሱን እንጠራዋለን:: (አርኬ ዘታሕሳስ 4)

=>አምላከ ቅዱስ እንድርያስ ከሞተ ልቡና አንቅቶ ለክብሩ ያድርሰን:: ከበረከቱም ያድለን::

=>ታሕሳስ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ 2.አባ ጻዕ 3.አባ ያዕቆብ

4.ቅድስ ታኦድራ

=>ወርኀዊ በዓላት 1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ 2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

=>+"+ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት:: ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ: ሲከተሉትም አይቶ:- "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው:: እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት:: ትርጉዋሜው "መምሕር ሆይ!"ማለት ነው:: "መጥታችሁ እዩ" አላቸው:: መጥተው የሚኖርበትን አዩ:: በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ:: አሥር ሰዓት ያህል ነበረ:: ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ዼጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ:: +"+ (ዮሐ. 1:47)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Report Page