*/

*/

Source

#መምህራችን_ሁሴን_አዳል ይህን አለ።

ለክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ለኢፌዴሪ የተወካዮች ም/ቤት ለኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት ለ10 የኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት ፕሬዚደንቶች በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአማራ ማስሚዲያ ኤጀንሲ

ለኢትዮጵያ ዜጎች በሙሉ

ከሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)
Email address: adalhusm@gmail.com Mobile Phone: +251913987705

Wollo University

ወደ “ሰው መሆን” ፖለቲካ በፍጥነት እንመለስ!!

በየዘመኑ በአገራችን የነበሩ ነገሥታት/መንግሥታት ከውስጥና ከውጭ በሚነሳ አመጽ ስለሚቸገሩ የግዛታቸው አድማስ ሰፋ ወይም ጠበብ ይበል እንጂ የንጉሠ ነገሥቱ የሕዝብ ተደራሽነት ወሰን በኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና አብሮነት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ አልነበረውም፡፡ የአገሪቱን ሁኔታ በጥልቀት የተረዱ አንዳንድ የውጭ አገር ጸሐፊዎች “አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበረችው ኢትዮጵያ ናት” የሚሉት ከዚህ የግምገማ ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያረጋገጠው የቅሪተአካላት ቅርስ ምርምር ግኝት ይህን ግምገማ ያጠናክራል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ አገር መሆኗ የሚያስገኘው ተጨማሪ የቱሪዝም ገጽታ በየትም አገር ለሚኖሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች የኩራትና ክብር ምንጭ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ “መሬት ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” እንዲሉ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ብርቅ አገር ባለቤቶች መሆናችንን በቀናዒነት በመደመም በሚመለከቱ የሰሜን አሜሪካና አውሮፓ አገሮች የሚኖሩ “የበሉበትን ወጭት ሰባሪ” ኃፍረተ ቢስ የብሔር ፖለቲከኞች ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ከብሔር ፖለቲካ ለሚገኝ ጥቅም ሲሉ ጎዳና ላይ በመውጣት ኢትዮጵያ ትውደም [Down Down Ethiopia]፤ አብይ ይውደም [Down Abiy] በሚል የክህደት ጩኸት የዓለም ሕዝብ አገራችንን በትዝብት እንዲያይ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ ተነስቼ ሰው ማለት ምን ማለት ነው? በአገራችን ከብሔር ፖለቲካ ተላቀን “ሰው መሆን” ወይም “ሰውኛ” ወይም “ሰዋዊ” ፖለቲካ ባህል መቼ እንጀምር ይሆን? እስቲ ልጠይቃችሁ!

ሕዝብና መንግሥት አንድ አይደሉም፡፡ ሕዝብ ሳይኖር ወደ መንግሥት ስልጣን የሚወጣ አካል የለም፡፡ መንግሥት ወጪ ወራጅ፤ አላፊና ጠፊ አካል ሲሆን ሕዝብ ግን በትውልድ መተካካት ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ተቋም ነው፡፡ መንግሥት በሕዝብ ላይ ግዛቱን አስፋፍቶ ሕዝብን አስገብሮ
ሕልውናውን የሚያስጠብቅ፤ በአንድ ወቅት ፈክቶ በሌላ ወቅት የሚከስም የፖለቲካ አስተዳደር ተቋም ነው፡፡ በአገረ መንግሥት፤ መንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ስናጤን የምንገነዘበው ዕውነታ ይህ ነው፡፡ የአገረ-መንግሥት አድማስ በመንግሥት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ስር ያለ ተለማጭ ስፍረት ሲሆን ሕዝብ ግን. ከመንግሥት የአገዛዝ ማዕቀፍ ውጭ ጭምር በሚፈጠር መስተጋብር ተቀራርቦ በአብሮነት የሚኖር የሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ሕዝብ ድንበር የለውም፡፡ ድንበር የሚያሰምሩት ንጉሠ ነገሥታት/መንግሥታት/ገዥ መደቦች ናቸው፡፡ በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት ለአገር ውስጥ ጸጥታና አስተዳደር ጉዳይ አገርን በንዑስ አስተዳደር ግዛቶች ወይም ክፍላተ ሐገራት ያዋቅራል፡፡ ኢትዮጵያ በረዥም ዘመን የመንግሥት ታሪኳ በየጊዜው የነበሩ ገዥ መደቦች በርካታ ንዑስ አስተዳደራዊ እርከኖችን በየሚመቻቸው መንገድ ሲያዋቅሩ ኖረዋል፡፡ በአንድ ወቅት በተወሰነ የአስተዳደር አሃድ ውስጥ የቆየ አካባቢ በሌላ ወቅት ወደ ሌላ የአስተዳደር አሃድ ወይም ከፍ ወደ አለ የአስተዳደር እርከን ሲሸጋሸግ ቆይቷል፡፡ በእገሌ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት/መንግሥት ወቅት የኢትዮጵያ ግዛት እስከዚህ ይደርስ ነበር፤ የዚህ አካባቢ ሕዝብ አስተዳደር ወደ እዚያኛው ክፍለ ሐገር/አውራጃ/ወረዳ/ቀበሌ ተካልሎ ነበር ሲባል በወቅቱ ለነበረው ንጉሥ/መንግሥት ግብር የገበረውን ሕዝብ ስርጭትና የአካባቢ አስተዳደር ፍሰት በቦታ ይገልጻል እንጂ ከንጉሠ ነገሥቱ ቁጥጥር ውጭ የቆየው ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ያልነበረ ወይም የሕዝቡ መስተጋብር ተቋርጦ በአብሮነት ያልኖረ መሆኑን አይገልጽም፡፡

በውስጥና በውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘርን ጥቃት ከመሪዎቹ ጎን በመሰለፍ እየመከተ በየጊዜው በሚሸጋሸግ የውስጥ አስተዳደር አሃድ ውስጥ በአንድነት ኖሯል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ወቅት በመሳፍንቱ መካከል የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት፤ ሕብረት ማጣት፤ ለዙፋኑ ብቻ በሚደረግ ትንቅንቅ ለባህር ጠረፍ ግዛቶች ጉዳይ ደንታ ቢስ መሆንና የዳር አገር ሕዝቦች መዘንጋት ያስከተለው ክፍተት የውጭ ኃይሎች የአገራችንን ሉዓላዊነት ደፍረው በያዙት አካባቢ በሚኖረው የጠረፍ ሕዝባችን ላይ ዘመን ተሻጋሪ የስነልቦና ጫና ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ሳይገደቡ በአገር ውስጥ ቅራኔዎችን በማነሳሳት ወይም በማባባስ ለጊዜያዊ መናኛ ጥቅም ሲሉ ለውጭ ኃይሎች አድረው አገራቸውን መቦርቦር ግድ የማይላቸው “የእናት ጡት ነካሾች” ለማሰለፍ ስለማይገዳቸው ከርቀት ሆነው በመቆጣጠር የሚያፈነዱትን ፈንጅ ዘወትር ለመቅበር መቼም ጊዜ ተቸግረው አያውቁም፡፡

አገራችን የምትገኝበት ጂዖፖለቲካዊ አቀማመጥና የብሔር ፖለቲካችን ሁኔታ ለአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አመቺ የፈንጂ መቅበሪያ መሬት ስለሆነ ከዚህ ችግር ዛሬም ቢሆን አልተላቀቅንም፡፡ ወደፊትም ቢሆን አንላቀቅም፡፡ አፍሪካን ተቀራምተው በነበሩት የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ተጽዕኖ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ በአገሮች መካከል የተሰመረው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አስተዳደር ወሰን አንድ የሆነውን ብሔረሰብ ቅኝ በተገዙ የጎረቤት አገሮችና በአገራችን ውስጥ እንዲገኝ አድርጎ በድንበር ለያይቶ በመክፈሉ የዳር ድንበሯ መሸርሸር፤ የአንዳንድ ዜጎቿ የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና መዛባትና የስብዕና መጓደል በአባቶቻችን ተጋድሎ አንድነቷንና ነጻነቷን ጠብቃ ለኖረችው አገራችን የዘላለም “የጀርባ እከክ ወይም የጉሮሮ አጥንት” ሆኖባት ቆይቷል፡፡ አንዳንድ የጎረቤት አገሮች የሚያቀርቡት “የጩኸቴን ቀሙኝ” የድንበር ጥያቄ የሚነሳው ከዚህ ችግር የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያዩዋት በየዘመኑ ግዛቶቿን የምትሰጥ ጥንታዊ አገር እንጂ የጠፉ ግዛቶቿን ማሰባሰብ የሚሳናት አገር አድርገው ነው፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የምንኮረኮመው፤ ውስጣችን ገብተው የሚያምሱን ለዚህ ነው፡፡ እነርሱ ህልማቸውን የሚያሳኩ ከሆነ እንዴት አድርጎ ነው የዛሬው ትውልድ ከመጪው ትውልድ ወቀሳ የሚድነው? የብልህና ዐዋቂ፤ ጠንካራ ባለ ራዕይ መሪ ከተገኘና እኛ በአንድ ላይ ከቆምን ኢትዮጵያ ይህን የጀርባ እከክ ወይም የጉሮሮ አጥንት በማከም ወደ ቀድሞ ገናናነቷ የምትመለስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

አንዳንዶች ሕዝብና ንጉሠ ነገሥት/መንግሥት፤ ፓርቲና መንግሥት አንድ ናቸው የሚል ሐተታ ያትቱ ነበር፡፡ ግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ “ትህነግና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው” ኢሕአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ አትኖርም፤ የሚል አጓጉል የትህነግ ትርክትና ሟርት ነበር፡፡ ነገር ግን ትርክቱም ሆነ ሟርቱ ውሐ አልቋጠረም፡፡ አባባሎቹ የገዥ መደቦች የሕዝብ አፍዝ አደንግዝ ከንቱ አባባሎች እንደሆኑ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የትግራይ ሕዝብ አሁንም አለ፤ ወደፊትም ይኖራል፤ ትህነግና ኢሕአዴግ ግን በታሪክ መዝገብ ላይ ለመከተብ ተራ ይዘዋል፡፡ ይህ የማንም ገዥ መደብ ዕጣ ፈንታ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በአገራችን በየዘመኑ የነበሩ ገዥ መደቦች ወደ መንግሥት ስልጣን የወጡበት ርዕዮተ ዓለም ዓይነት አንዱ ከሌላው ይለያል፡፡ መለኮታዊ ስልጣን፤ ሶሻሊዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ በቅደም ተከተል ባለፉት በርካታ ዘመናት አገራችንን የዋጁ የርዕዮተ ዓለሞች ዓይነቶች ነበሩ፡፡ የቀድሞ ነገሥታት ቅብዓ-ቅዱስ ተቀብተን በሕዝቡ ላይ ለመንገሥ በፈጣሪ የተመረጥን ነን በሚል “መለኮታዊ” ርዕዮተ ዓለም ያለ ነገድ/ጎሳ ልዩነት (አማራ፤ትግሬ፤ኦሮሞ ወዘተ) የዘር ሐረጋቸውን የአይሁድ ዘር ከሆነው ጠቢቡ ንጉሥ ሠለሞን የዘር ግንድ ጋር በማገናኘት “ሞዓ አንበሳ ዘ እምነ ነገደ ይሁዳ ስዩመ እግዚአብሔር ዘ ኢትዮጵያ” በሚል “መለኮታዊ” ሥነ ቃል ዘውድ እየደፉ ገዝተዋል፡፡ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አጼ ኃይለ ሥላሴ (1885-1967) ከዙፋናቸው እስከ ወረዱበት የካቲት 1966ዓ.ም ድረስ በአገራችን የነበረው አገዛዝ ከዘመነ መሳፍንት ውጭ ከሞላ ጎደል ዘውዳዊ ሥርዓት ነበር፡፡

ሕዝባዊ አመጽ ተቀስቅሶ ዘውዳዊው ሥርዓት በተወገደ ማግሥት የተተካው ወታደራዊ መንግሥት አገሪቱን ለመምራት የተከተለው አዲስ ርዕዮተ ዓለም ከምሥራቁ ዓለም ጎራ በትውስት የመጣው የሕብረተሰባዊነት (ሶሻሊዝም) ርዕዮተ ዓለም ነበር፡፡ ይህ ርዕዮተ ዓለም በአገራችን ዙሩን እያከረረ በሄደው የትጥቅ ትግል፤ የውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞና በዓለም ላይ የነበረው ቀዝቃዛው ጦርነት ባስከተለው የጎራ አሰላለፍ ለውጥ ተጽዕኖ ተደናቅፎ ከስልጣን ተወግዷል፡፡ ሕዝቡ ይመኝ የነበረውን የተሻለ የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ስላላስቻለ በንድፈ ሐሳብና በተግባር አንድነት መጓደል የተነሳ ይህም ርዕዮተ ዓለም ከመወገድ አልዳነም፡፡ ዳሩ ግን ከላይ የተገለጹት የሁለቱ ርዕዮተ-ዓለም አራማጆች ቢያንስ የኢትዮጵያን ሕዝብና ኢትዮጵያን ነጣጥለው ባለመመልከት አገር ማለት ለዘመናት በተገነባ የጋራ ማንነት ሕዝብ ድርና ማግ ሆኖ አንድ ላይ የሚኖርባት የጋራ ምድር ለመሆኗ ዕውቅና የሰጡ ነበሩ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ ርዕዮተ ዓለሞች አገርን የገዙ ገዥ መደቦች ለራሳቸው ልዕልና ከፍ ማለትና “እንወዳታለን ለሚሏት አገራቸው” ሉዓላዊነት መከበር ጉዳይ ትኩረት ሲሰጡ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት ተጋፍተው ነበር ከማለት በስተቀር በተፈጥሮ የተሰጠ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በግፍ በጅምላ ጥሰው እንደነበር በሙሉ አፍ መናገር አይቻልም፡፡ ዜጎች በየትኛውም የአገራቸው ክፍል በነጻነት ተንቀሳቅሰው ለመኖር ችለዋል፤ ሐብት አፍርተዋል፡፡ ወልደው ከብደው ልጅ ድረዋል፤ በየቀያቸው አርጅተው ሞተው በክብር ተቀብረዋል፡፡ ነገር ግን በሌላኛው የአገራቸው ክፍል መጤ እየተባሉ የገዛ አገራቸው ባይተዋር ተደርገው ሰለባ አልሆኑም ነበር፡፡

ግንቦት 1983ዓ.ም ወታደራዊ አስተዳደር ደርግን አስወግዶ በቦታው የተተካው ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ይባል የነበረ ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለም በማስፈን ሕዝቡን በጠላትነትና ወዳጅነት፤ በመጤነትና ነባርነት ከፋፍሎ በማናቆር የሕዝብ ግጭትንና እልቂትን የፖለቲካ ወረቱ አድርጎ ከዚህ ጥፋት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍን እየቆረጣጠመና እያከፋፈለ የሚኖር የመንግሥት ሥርዓት ነበር፡፡ የዚህ ርዕዮተ ዓለም ሐሳብ ጠንሳሽና መሐንዲስ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ቡድን በዜጎች ነጻነት፤ዕኩልነትና አብሮነት የማያምን፤ በተለይም የአማራ ብሔረሰብን የተፈጥሮ ጠላቱ አድርጎ ለማጥፋት በክፋት ታጥቆ በመነሳት በሌሎች ብሔረሰቦች ዘንድ ለማስጠላት ያልፈጸመው ተንኮል የለም፡፡ “የአማራ ብሔርን ማህበረሰባዊ ዕረፍት ማሳጣት” የሚል አንቀጽ በመቋቋሚያ ማኒፌስቶው በቋሚነት በማስፈር የአማራ ጭቁን ሕዝብ ላለፉት በርካታ ዘመናት የገዥ መደቦች ድክመት ኃላፊነት እንዲወስድ በማስገደድ በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የግፍ ግፍ ፈጽሟል፡፡ የአማራ ሕዝብ ይህ በደል የሚፈጸምበት በየትኛውም ወቅት የአማራ የቤተመንግሥት ድርሻ ከማንም ብሔረሰብ ድርሻ በልጦ በማይገኝበት ወይም ተገቢ ድርሻውን ባላገኘበት ሁኔታ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብንና በአመዛኙ የአማራ ሕዝብ ኃይማኖት ተደርጎ የሚቆጠረውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት እሴቶችን በመጠቀም ስሙንና ኃይማኖቱን እየቀየረ ገዥ መደብ ወይም የገዥ መደብ ጭፍራ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጅምላ “የአማራ ገዥ መደብ” አድርጎ በመሳል የአማራ ብሔረሰብ ጭቁን ሕዝብ በሌሎች ብሔረሰብ ሕዝብ እንዲጠላ ጥረት ተደርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ ንጹህና ለፍቶ አዳሪ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች፤ ያፈሩትን ንብረት የሚገፈፉት፤ የሚሳደዱትና በግፍ የሚታረዱት በዚሁ የተዛባ ትርክት ላይ በተመሰረተ የብሔር ፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ እንደ ሐቁ ከሆነ በስሙ የተነገደበት ጭቁን የሆነው የአማራ ሕዝብ ስሙ መነሳት ያለበት በገዥ መደብ አብራክነት ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በየጦር ሜዳው ደረቱን ለጦር፤ እግሩን ለጠጠር አርጎ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በመዝመት ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ የሁላችንም የሆነችውን አገራችንን ለአሁኑ ትውልድ በጋራ ባቆየበትና አገረ መንግሥት በተገነባበት ጉልህ የታሪክ ድርሻው ነው፡፡

በዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተሰኘ ርዕዮተ ዓለም ወደ መንግሥት ሥልጣን የመጡ ገዥ መደቦች የአገር ሉዓላዊነትና የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ዋነኛ የተግባር አጀንዳ አላደረጉም፡፡ በሌላው የአገራቸው ክፍል የሚኖሩ ዜጎች በባይተዋርነት ታይተው ለሰው ልጆች በተፈጥሮ የተሰጡ በሕይዎት የመኖርና በነጻ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ተገፈዋል፡፡ በነጻነት ለመኖርና ሐብት ለማፍራት አልቻሉም፡፡ በግፍ በተገደሉበትም ሆነ ኖረው በሞቱበት ቀየ አስከሬናቸው በክብር መቀበር አልቻለም፡፡

የትህነግ መንቀሳቀሻ መንኮራኩር የነበረው ኢሕአዴግ ለስሙ መጠሪያ ቃሉን ከመዋሱ በስተቀር “ኢትዮጵያ” የምትባል አገር መኖሯን ከልቡ የማይቀበል ድርጅት መሆኑን በግብሩ አረጋግጧል፡፡ በኢሕአዴግ የመጠሪያ ስም ላይ ያለው “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ኤች አይ ቪ “በአስመሳይ ተግባቦት” ወደ ነጭ የደም ሕዋስ አካል ዘልቆ ሕዋሱን አፈራርሶ የበሽታ መከላከል መድህን አቅሙን አዳክሞ ዘአካሉን እንደ ሚገድለው፤ ኢሕአዴግ የአገሪቱ ማፈራረሻ “የተግባቦት ቫይረስ” መጠሪያ ነው፡፡ በአጭሩ ኢሕአዴግ ለራሱ ቡድን ብቻ የኖረ የኢትዮጵያ ሕዝብና ዜጎች ጸር ነበር፡፡ ለሕዝብና ዜጎች ደንታ ቢስ የነበረው ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ “ብሔር/ብሔረሰቦች” ተቆርቋሪ ነኝ የሚል ቀረርቶ እያቅራራ “የአዞ እንባ ያለቅስ” ነበር፡፡

በራሱ ውስጥ በፈነዳው የለውጥ ፍላጎትና ከውጭ በተነሳ የሕዝባዊ አመጽ ማዕበል ግፊት ሕዝቡ ከኢሕአዴግ የተላቀቀው ገና በቅርቡ ነው፡፡ በመሆኑም በብሔረሰቦች መካከል የፈጠረው የተዛባ ግንኙነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያስከተለው ጎጂ ተጽዕኖ አሁንም የአገራችን ከባድ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አገራችን በተፈጥሮ ባገኘችው የመከላከል መድህን አቅም የደረሰባትን ተጽዕኖ ለመቋቋምና ብሎም ለማዘግየት ባትችል ኖሮ ወደ ሞት አፋፍ ተቃርባ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ተገዝግዞ ሊበጠስ ያልቻለው ይህ የመከላከል መድህን አቅም በሕዝቡ ውስጥ ለዘመናት የቆየው የህብረብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የጋራ አስተሳሰብ የፈጠረው የአብሮነትና የአንድነት ትስስር ነው፡፡ አገራችን ለሦስት አስርት ዓመታት በኢሕአዴግ ከደረሰባት ጉዳት ለማገገም ገና ረዥም ጊዜ ወይም የዜጎችን ብርቱ ጥረት መጠየቁ አይቀርም፡፡ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ከሚጠይቅ በስተቀር ኢሕአዴግ ያላላው የአብሮት መንፈስ በዜጎች የነቃ ተሳትፎ ቀድሞ ወደ ነበረበት ጥንካሬ መመለሱ አይቀርም፡፡
ኢሕአዴግ በሕዝቡ ውስጥ አሰራጭቶት ለነበረው መርዝ ማርከሻ መድኃኒት የግድ መገኘት አለበት፡፡ ለዚህ የሰረጸ “የአመለካከትና የአስተሳሰብ መዛባት” መርዝ ጊዜ መስጠት ማለት አገራችን ኢሕአዴግ ባዛባው የብሔረሰቦች የግንኙነት ቀውስ ከቆመችበት የገደል አፋፍ ተንገዳግዳ ወድቃ እስከምትሰባበር መጠበቅ ማለት ነው፡፡ የአገሩን ታሪክ በትክክል ተገንዝቦ ገንቢ ሚና እንዳይጫወት ኢሕአዴግ ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በአዕምሮው ውስጥ የውሸት ትርክት በማስረጽ ወጣቱን ትውልድ ቀፍድዶ ይዞት ነበር፡፡ በኢሕአዴግ መርዛማ የውሸት ትርክት ከተለወሱ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ታሪክ፤ የብሔር/ብሔረሰብ/ሕዝቦች ጽንሰ ሐሳብ፤ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀርና የአገሪቱ ሕገመንግሥት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢሕአዴግ ካደረሰባት ጉዳት ማገገም መጀመሯ የሚታወቀው ይህን የተዛባ አመለካከትና አስተሳሰብ ለማስተካከል በሚወሰደው የርምጃ ዓይነትና ፍጥነት ነው፡፡
በታሪክ ጠልነት የአገራችንን ታሪክ ወደ መቶ ዓመት ዝቅ ማድረግ፤ በውሸት ትርክት መበረዝና ማደብዘዝ ብሎም የታሪክ ትምህርትን ከአገሪቱ የሥርዓተ ትምህርት ዝርዝር ውስጥ መሰረዝ፤ በደፈናው የኢትዮጵያ ታሪክ የአማራ ሕዝብ ታሪክ ነው ብሎ ማሳነስ፤ ነባሩን የኢትዮጵያ ባንዲራ የነፍጠኛ ባንዲራ ነው ማለት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ኦፊሴላዊ ቋንቋን [አማርኛ] የነፍጠኛ ቋንቋ ብሎ ማንኳሰስ፤ ወጣቱን ትውልድ በተዛባ ትርክት ለመቅረጽ ኢሕአዴግ በዕኩይነት የተጠቀመበት ስልት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጸመበትን ዕኩይ ተግባር ተገንዝቦ ወደ ጎን አግልሎ የየአካባቢውን ህብረተሰብና የአገሩን ታሪክ በግል ንባብ አሟልቶ ለማወቅ ጥረት በማድረግ የኢሕአዴግን መርዘኛ ትርክት ታግሎ ሽሯል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ያካበተው የታሪክ ዕውቀት ክምችት ወደፊት በሥርዓተ ትምህርት ታግዞ ለሚሰጥ የታሪክ ትምህርት ማብላያ እርሾ ይሆናል፡፡

“ብሔር፤ብሔረሰብ፤ሕዝቦች” [Nation/Nationalities/People] የሚባለው የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የሚኖረን ተግባቦት ወደፊት የአገራችንን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነት ስኬት ይወስናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በ“ ” ውስጥ የተቀመጠው ይህ የተደረተ ቃል ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል በሰፊው የተጠቀመበት “መተት” ነው ይሉታል፡፡ አንዳንዶች በመዝገበ ቃላት ላይ የማይገኝ ተጣብቆ የተፈጠረ ኢሕአዴግ የፈጠረው የማይረባ ቃል ነው ይላሉ፡፡ ነጠላ ቃላቱ ከቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ጥያቄ ወቅት ጀምሮ ቢታወቁም ድርቱ “ብሔር፤ብሔረሰብ ፤ሕዝቦች” ኢሕአዴግ የፈጠረው የዕኩይ ዓላማ ማሳኪያ ጭራቅ ቃል ነው በማለት በሁለቱም ወቅት የኖሩ አንጋፋ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ድርት ቃል የሚገለጽ ምንም የሚታወቅ ነገር በዓለም ላይ የለም፡፡ ቃሉ ገላጭነት የሚኖረው እየተቆራረጠ ሲታይ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔር ምንድነው? ብሔረሰብ ምንድነው? “ሕዝቦች” ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው በማለት እንጠይቅ፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገመንግሥት አንቀጽ 39 (5) “ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ሕዝብ “ሠፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፤ ሊግባቡበት የሚችሉት የጋራ ቋንቋ ያሏቸው፤ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፤ የስነልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” የሚል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በአንቀጹ ላይ የሰፈረው ሐሳብ ለሦስቱም ማለትም “ብሔር፤ብሔረሰብ፤ሕዝብ” ተመሳሳይ ትርጉም መስጠቱ በግልጽ ስለሚታይ እንደ ሕገመንግሥቱ አገላለጽ ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ሕዝብ በትርጉም አይለያይም፡፡ ፖለቲከኞች በደፈናው ብሔር፤ብሔረሰብ፤ሕዝብ በማለት እንዳሻቸው የሚናገሩት ሕገመንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ሳይረዱ ቀርተው ይመስላል፡፡ በአገራችን ለዘመናት የተካሄደ የሕዝብ መስተጋብር ብሔረሰቦችን በማቀላቀል በሕብረብሔራዊ አገር ጥላ ስር እንዲኖሩ ስላደረገ ብሔሰቦች የሚጋሩት የማንነት ገላጭ ባህርያት በዝቶ በመካከላቸው ልዩነት የመፈጠሩ ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡

አንድ መስፈርት (ለምሳሌ ቋንቋ) በመውሰድ ወይም ጥቂት መስፈርቶችን በመውሰድ አንዱ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ይለያል ለማለት ያዳግታል፡፡ በአገራችን በአንድ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ የቅድመ አያቶቹን ቋንቋ ይዞ የቀጠለ ወይም የጣለ ወይም የሌላውን ቋንቋ የተቀበለ ወይም ቋንቋ ያቀላቀለ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁ ከመሬት አኳያ ሲታይ መሬቱ ሌላ ቋንቋ ይናገር የነበረ ቀደምት ነዋሪ ሕዝብ ወይም በዘመን ብዛት ከበርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብሔረሰቦች ጋር በአብሮ መኖር የተወሃደ ሕዝብ የኖረበት ሊሆን ይችላል፡፡ በሰው ደረጃም ቢሆን አንዱን ሰው የእኛ ማለት እንዳይቻል የአያት ቅድመ አያቶቹ የዘር ምንጭ የተለያዩ ብሔረሰቦች ሊሆኑ ይችላል፡፡ በገዥ መደብ አባላት ደም የተንቆረቆረውም የተቀላቀሉ ብሔረሰቦች ትውልድ ደም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህብረብሔራዊ ማንነት ያላቸው ውሕድ ዜጎች ቁጥር ነጠላ ብሔራዊ ማንነት አለን ከሚሉ ዜጎች ቁጥር ይበልጣል፡፡ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ አፋር፤ ወዘተ በማለት ማንነትን ለመስጠት ወይም ማንነትን ለመንፈግ የዘረመል [DNA] ምርመራን ጨምሮ በርካታ መረጃዎችን ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ነገር “የእኛ” ከምንል “የሁላችን” ብንል ወደ ዕውነቱ እንጠጋለን፡፡ የአንድ አካባቢ ሕዝብ ማንነት ቋንቋ፤ ባህል፤ ታሪክ፤ ቀደምት ሁኔታ ወዘተ ሊታወቅ የሚችለው በሰፊ ሳይንሳዊ ጥናት ላይ ተመስርቶ በሚገኙ አስረጂዎች እንጂ በፖለቲካ ልሂቅ ፍረጃ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት የሚገኘው በአንድ አካባቢ በመወለድ ወይም በማህበራዊ መስተጋብር በሚፈጠር አጋጣሚ ወይም በምርጫ የሌላውን ማንነት በመያዝ ነው፡፡ ለአገር በቀል ዕውቀት ልዕልና ተገዥ ከሆንን “ብሔር” ማለት አገር ወይም ሕዝብ፤ ብሔረሰብ ደግሞ “የዚያ አገር ሰው” ወይም “ከዚያ ሕዝብ የወጣ ሰው” ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ዘብሔረ ሸዋ፤ ዘብሔረ ወለጋ፤ ዘብሔረ ወሎ፤ ዘብሔረ ትግሬ፤ ዘብሔረ መንዝ፤ ዘብሔረ ቡልጋ፤ ዘብሔረ አድዋ፤ ወዘተ፤ ይባል የነበረው የብሔራዊ ማንነት ምንጭ በኢትዮጵያ በአንድ ክ/ሐገር ወይም አውራጃ በመወለድ ወይም ማህበራዊ መስተጋብር በመፍጠር እንጂ በዘር ማለትም ነገድ/ጎሳ በመጥቀስ አለመሆኑን ያስገነዝባል፡፡ እያወራን ያለነው “ስለብሔር ጉዳይ” ስለሆነ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ብሔራዊ ማንነት በዘር ፈጽሞ አይገኝም፡፡

በመሰረቱ ብሔር ወይም ብሔረሰብ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ “ሰዎች” በመባል የሚታወቁትን ማህበራዊ እንስሳት ለመግለጽ የሚውል ሐሳብ ነው፡፡ “ሕዝብ” የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም አገር/ክፍለ ሐገር/አውራጃ/ወረዳ/ቀበሌ ሰዎችን የሚገልጽ ልክ እንደ አገር ተለማጭ የሆነ የወል ስም ነው፡፡ “ሕዝቦች” የሚል የወል ስም ሊገኝ የሚችለው በትህነግ/ኢሕአዴግ ወይም በደቀመዝሙሮቹ መዝገበ ቃላት ውስጥ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መዝገበ ቃላት ከተዘጋጀ በጣም ቆይቷል፡፡ በአማርኛ መዝገበ ቃላት ወይም ሰዋሰው “ሕዝቦች” የሚል የሕዝብ ብዜት ቃል አልተለመደም፡፡

በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ሰነድ ላይ እንዲሁ በእንግሊዝኛ ሰዋሰው ያልተለመደ “Peoples” የሚል የእንግሊዝኛ ቃል በአቻነት ጎን ለጎን ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ኢሕአዴግና ደቀመዝሙሮቹ “ሕዝቦች” የሚለውን “የመተት ቃል” ከእነ እንግሊዝኛ አቻው ኢትዮጵያውያንን በድፍረት በማስተማር ለማስለመድ ብዙ ደክመዋል፡፡ በዚህ “የመተት ቃል” ላይ የሙጥኝ ያሉበት ምክንያት የተለያየ ሕዝብ አስመስሎ በማቅረብ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ለመከፋፈልና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በዜጎች ላይ ቋሚ የሥነ ልቦና ተጽዕኖ ለመፍጠር ነው፡፡ ይህን ሕዝብን የማናቆር ድብቅ ሴራ በየዓመቱ ሕዳር 29 ቀን በሚያዘጋጁት “ብሔር፤ብሔረሰብ፤ ሕዝቦች” ፌስቲቫል ለመሸፈን ብዙ የአገር ሐብት በከንቱ አባክነዋል፡፡ ሕዝብ የማናቆር “መተት” የሚሠራው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው ስለሚባል ከእንግዲህ ይህን ቃልና ትህነግ/ኢሕአዴግን ከአዕምሯችን አውጥተን እንጣል፡፡

በጧቱ የተለከፍንበትን የምዕራቡ ዓለም ፍቺውን ስናይ በማህበራዊ ቁስአካልነት ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካና ምጣኔ ሐብት ሐሳብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የማርክሲስት/ሌኒኒስት ፍልስፍና አራማጆች “ብሔር/ብሔረሰብ” የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከህብረተሰብ የዕድገት ታሪክ ወቅት ጋር በማነጻጸር ይተነትናሉ፡፡ እንደ ማርክስስት/ሌኒኒስት ፍልስፍና አስተሳሰብ “ብሔረሰብ” ዝቅተኛ በሆነ የኢኮኖሚ ሕይዎት የሚኖር በዕድገት ኋላቀር የሆነ ህብረተሰብ (ፊውዳሊዝም) ፤ “ብሔር” ደግሞ የዳበረ የኢኮኖሚ ሕይዎት ባለቤት የሆነ ህብረተሰብ (ካፒታሊዝም) ለመግለጽ የተጠቀሙበት የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ቃል ነው፡፡ ካፒታሊዝም ሲዳብር ህብረተሰቡን በሥራና በሥፍራ በማሰባሰብ፤ የህብረተሰቡን ቋንቋ መዳበርና በሳይንስና ቴክኖሎጅ ማደግን በማስከተል በዚያው “ብሔረሰብ” ወደ “ብሔር” የዕድገት ታሪክ ወቅት ይሸጋገራል ብለው ያስባሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብን በተለያየ ብሔር ለመክፈል አስቻይ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ሥነ ምህዳር ሳይኖር ለተነሳችበት ዕኩይ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲያመቻት ትህነግ/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መስፈርት ላይ ተመስርታ በብሔር/ብሔረሰብ ግድግድ አጥር ከፋፈለች፡፡ በቋንቋ መስፈርት ብቻ ሕዝብን አማራ፤ኦሮሞ፤ትግሬ፤ሐረሪ ወዘተ ብሎ በክልል ለማካተት መሞከር ልኬታቸው አንድ የሆኑ ጠባብ ሱሪዎችን አሰፍቶ ሁሉም ሰው እንዲለብስ እንደ ማስገደድ ይቆጠራል፡፡ እንደ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግራይ፤ ደቡብ ኢትዮጵያ ወዘተ ያሉ ክልሎች ውስጥ በቋንቋ የማይመሳሰሉ ወይም አንድ ዓይነት ቋንቋ ቢጋሩም እንኳ ሰፊ የባህል ብዝህነት እና ከሌላው ሕዝብ ይበልጥ ቀረብ ያለ የባህልና የታሪክ ትስስር ያላቸው ስለሆነ በአንድ ክልል ውስጥ አስገድዶ በማስገባት አጭቆ ማስጨነቅ ያስቸግራል፡፡ በሌላ በኩል ለዘመናት አብረው ከኖሩበት ዘውግ ያለፈቃዳቸው አፈናቅሎ በክልል መለያየት ወይም በሌላ ክልል ውስጥ ማካተት በመሬት ይገባኛል፤ የውሐና የግጦሽ ሳር መሬት መቆጣጠር ፍላጎት፤ በተወራራሽ ባህልና ታሪክ ሽሚያ በሚፈጠር ስግብግብነትና “የእኛ” ነው ባይነት ጎራ ለይቶ ዘላለም በማናቆር ያስተላልቃል፡፡ አስገድዶ ማጨቅ ወይም የሕዝብን የአብሮነት ስሜት ሳይገመግሙ በፖለቲካ ልሂቅ እሳቤ ሕዝብን እንደ ፈለጉ ማካለል በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ያለውን ችግር በማስከተል ለአጭር ጊዜ ታይቶ ጠፊ ብሔራዊ ክልል በመፍጠር ከባድ ኪሳራና ቀውስ ያስከትላል፡፡ በዚህ የፖለቲካና ምጣኔ ሐብት ትንታኔ መሰረት በ1960ዎቹም ሆነ ዛሬ በታሪክ ዕድገት ወቅት አንጻር አንዱ ከሌላው የሚለይ የህብረተሰብ ክፍል በኢትዮጵያ የለም፡፡ የሚያርስበትን ሞፈርና ቀንበር ወይም የሚያስጎትትበትን የቤት እንስሳት ዓይነት ከሌላው ብሔረሰብ ቀድሞ የለወጠ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ እስከ አሁን የለም፡፡ በአርብቶ አደሩም አኗኗር ረገድ እንዲሁ ነው፡፡ በአገራችን በአራቱም አቅጣጫ ያለው አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር የሚተዳደረው ያው ተፈጥሮ የቸረችውን ሐብት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ በሆነ ኋላ ቀር የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ስልት ለፍቶ በማምረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንዱ ብሔረሰብ በፊውዳሊዝም ስልተምርት ላይ ተቸንክሮ ሲቀር ወደ ከፒታሊዝም ስልተምርት ተስፈንጥሮ የገባ ብሔረሰብ እስካሁን መኖሩ አይታወቅም፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያን ወይም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ “ብሔር”፤ በአገሪቱ ውስጥ በተወለደበትና ባደገበት ቦታ የሚኖር የተቀራረበ የባህል ገጽታና የተለየ ቋንቋ ያለውን ሕዝብ “ብሔረሰብ” በማለት ብንገልጽ ከአገር በቀሉ ትርጉም ጋር የሚቀራረብ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ አንድ ብሔርና የብዙ ብሔረሰቦች አገር ናት ማለት የተሻለ አመክንዮት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ የሁሉም ብሔረሰቦች መብት ተከብሮ አብረው በዕኩልነት መኖር እንዲችሉ ቋንቋቸውን ማበልጸግ፤ ባህላቸውን ማጎልበት፤ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ነው፡፡ እኔንም ጨምሮ የቀድሞ ተማሪዎች በሕብረት የታገሉት ከዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ነበር፡፡
ተማሪ-መሩ የብሔር ፖለቲካ የመምህራኑ አሻራ ያልታከለበት በእንጩጭ ደረጃ ላይ የሚገኝ ግርድፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ስለነበር ተማሪዎቹ በወቅቱ ያስተጋቡት መሆን በሚገባው ልክ ሳይሆን በተረዱት መጠን ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢሕአዴግ የመንግሥት ስልጣን እንደያዘ ገና ከመነሻው ጉድለት የነበረበትን “የብሔር ትግል ፖለቲካ” ጽንሰ ሐሳብ በመጠቀም ሕዝብን ያለ ጥናት ብሔር/ብሔረሰብ ብሎ በመከፋፈል የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት ከመጣሱም በተጨማሪ ልዩነቶችን በማጦዝ አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለመለያየት ሞክሯል፡፡ የብሔር ፖለቲከኞቹ ተጨባጭነት የሌለውን የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ ጨምድደው ይዘው የቡድን መተዳደሪያ ገቢ ምንጭ በማድረግ “በሌላው ቁስል እንጨት እየሰደዱ” “ሁልጊዜ አበባየ” ለቅሶ አልቅሰውበታል፡፡ በዚህ ያልጠራ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ የተገነባው የብሔር ፖለቲከኞች የሞቀ የጫጉላ ቤት ብቻ ነው፡፡ በዚህ የኪራይ መሰብሰቢያ ፖለቲካ ስንቱ ኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ተንደላቆ ሲሞሸር፤ አገራችን ምን ያህል በዕድገት ወደ ኋላ እንደቀረች፤ የስንቱ ድሃ ቤት እንደቀዘቀዘ/እንደፈራረሰ፤ የስንት አምራች ወጣት ትውልድ ሕይዎት እንደ ተቀጠፈ፤ ስንት አረጋዊያን ያለ ጧሪና ቀባሪ እንደ ቀሩ ቤቱ ይቁጠረው፡፡

ነባር የብሔር ፖለቲከኞች አንድ ቀን ልብ ገዝተው ወደ ልባቸው በመመለስ ለሕዝቡ ያዝኑለታል ተብሎ ሲጠበቅ አዳዲስ የብሔር ፖለቲከኞች ለየብሔረሰባቸው መድህን ለመሆን በማሰብ ቀስ በቀስ እንደ አሸን እየፈሉ በመምጣታቸው ዛሬ ላይ በአገራችን የብሔር ፖለቲካው ገበያ ደርቷል፡፡ ነገር ግን እኝህ መጤ የብሔር ፖለቲከኞች ስህተት ፈጽመዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም የብሔር ፖለቲካ ፓርቲ የተቋቋመለት ብሔረሰብ ቢያንስ በሕይዎት የመኖር ዕድል ካገኘ ሌላው ብሔረሰብ ለምን የትም ወድቆ ይቀራል፡፡ ይልቁንም በአንዳንዱ ብሔረሰብ ስም በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማቋቋም ፉክክሩ ተጧጡፏል፡፡ በኢትዮጵያ ለጊዜው 86 ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ለስንቶቹና በአንድ ብሔረሰብ ስም እስከ ስንት የብሔር ፖለቲካ ፓርቲ ማንቀሳቀሻ ፈቃድ መስጠት እንደሚቻል የምርጫ ቦርድ ገና የመወሰኛ ሕግ አላወጣም፡፡ ፖለቲካ አማራጭ ቢዝነስ ተደርጎ በሚቆጠርባት አገራችን ማንም ሰው የነገዱን/ጎሳውን ስም ጠርቶ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም አማራጭ የሥራ ዕድል ቢፈጥር ሊጎዳ የሚችለው አገሪቷና ሕዝቡ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የብሔር ፖለቲከኛው ችግር አይደለም፡፡

ወደ ቀድሞ ተማሪዎች ግርድፍ የብሔር ትግል ፖለቲካ ጉዳይ ስንመለስ የተማሪው የትግል ቋያ የተቀረውን የህብረተሰብ ትግል አቀጣጥሎ የዘውዳዊውን ሥርዓት ለመገርሰስ ያስችል እንጂ የመንግሥት ሥልጣን ለመረከብ የሚችል የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ በወቅቱ ባለመኖሩ ምክንያት የተተካው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነበር፡፡ ደርግ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ አይመቺም ያሉ ጥቂት የቀድሞ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያንኑ ግርድፍ “ብሔር/ብሔረሰብ” ጽንሰ ሐሳብ በጥርሳቸው ነክሰው ለሜዳ ትግል በየጎጣቸው ወደ ሚገኝ ጫካ ፈረጠጡ፡፡ ከ17 እስከ 30 ዓመታት የፈጀ ደም አፋሳሽ የትጥቅ ትግል በኋላ ደርግን በትብብር በማስወገድ ያንኑ ግርድፍ ጽንሰ ሐሳብ ይዘው ወደ ቤተመንግሥቱ በመግባት ጽንሰ ሐሳቡን የሁሉም ነገሮች በር መክፈቻ ቁልፍ አደረጉት፡፡ ኤርትራም ከእናት አገሯ ተገነጠለች፡፡ በዚህ ግርድፍ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመስርተው በሁሉ አዋቂነት አባዜ ሕዝቡን አሁን ለደረሰበት ግፍና መከራ ዳረጉት፡፡ አፋጂው ጽንሰ ሐሳብ በመነጨበት አገር ሲከስም ይኸው በእኛ አገር የፖለቲካ ሳልቫጅ ቡትቶ ለብሰን መንገታገት ዕጣ ፈንታችን ሆኗል፡፡ ከዚህ የተነሳ ፖለቲካችን ብልሹና ቆሞ-ቀር ወይም የኋልዮሽ ተጓዥ ሆነ፡፡ የብሔር ፖለቲካን በሕግ ያገዱ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች መኖራቸው ቢታወቅም የሌሎች አገሮችን ልምድ መንግሥታችን ለምን እንደሚፈራው እየነጋ ሲሄድ ስለሚገለጥ ሐቁ ነገ ጧት የሚታይ ይሆናል፡፡ ነባሮቹ የብሔር ፖለቲከኞች ዱላውን ላሳደጓቸው ግልገል ደቀመዝሙሮች በማቀበል ዛሬ እነርሱ ደንገጡር ሆነው ሲቀመጡ ወይም በተለያየ መንገድ ዱካቸው ሲጠፋ በአምሳላቸው የቀረጹት ግልገሉ “የብሔር ፖለቲካ ትውልድ” በውርስ የተረከበውን የብሔር ፖለቲካ በቅብብሎሽ ዘመን ለማሻገር ለዘመናት ረግቶ የኖረውን ህብረተሰብ በግፍ ከኖረበት ቀየ በማፈናቀል ሚጢቻ በማሰር፤ ነባርና መጤ በሚል የአውሬ ብሂል በማግለልና በመጨፍጨፍ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ነው፡፡ እነሆ ዘመኑን ባልዋጀ የብሔር ፖለቲካ ሕዝቡ ከመታመስ የሚላቀቅበትን ወቅት ለመገመት ከባድ ነገር ሆኗል፡፡ ትህነግ/ኢሕአዴግ ትሞታለች እንጂ እርሷ የሞተችለት ያረጀ ሐሳብ ፈጽሞ አይሞትም የሚሉ ትንቢት ተናጋሪዎችን በሐሳብ ለመገዳደር ቀላል ጉዳይ አልሆነም፡፡ ይህ አውዳሚ የብሔር ፖለቲካ ተጨማሪ የፍጅት ዘመን ሊዋጅ የትግል ስልቱን አድሶ በተጨማሪ ጉልበት ራሱን ያሟሙቃል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎችን የብሔር ትግል መዳረሻ ግብ በመቀልበስ ኢትዮጵያን የመበታተን ትልም ትህነግ መትለሟ የታወቀው ለትጥቅ ትግል ወደ ጫካ ገብታ ደደቢት ላይ ባወጣችው የትግል ማኒፌስቶው ነበር፡፡ በደም አፋሳሹ የትጥቅ ትግል ደርግ ተወግዶ አገር መምራት እንደ ጀመረ ቀድሞ የተዘጋጀችበትን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ቻለች፡፡ በዚህም መሰረት በቋንቋ ፌዴራሊዝም የእያንዳንዱን ብሔረሰብ ሕዝብ ነጣጥሎ በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ በማስገባት በአንድ አሃዳዊ መንግሥት ፈንታ የሌሎች ብሔረሰቦች መብት የማይከበርበት በርካታ ትንንሽ አሃዳዊያን መንግሥታትን አደራጀች፡፡ መላው የቀ.ኃ. ሥ. ዩ. ተማሪ በህብረት የተነሱለት የብሔር ትግል ዓላማ በጊዜው በነበሩት ጠቅላይ ግዛቶች በኋላ ክፍለ ሐገራት አስተዳደር መዋቅር ውስጥ የዳበረ የጋራ ማንነት ለዘመናት የገነቡ ብሔረሰቦች ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ዕኩል ተከብሮ በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ የስልጣን ባለቤት እንዲሆኑ፤ ራሳቸው በሚመርጧቸው ሰዎች እንዲተዳደሩ፤ መሪዎቻቸውን ራሳቸው እንዲሾሙ/እንዲያወረዱ፤ ባህላቸውን እያዳበሩ፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እየተማሩ/እየተዳኙ፤ በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ ተመጣጣኝ ውክልና አግኝተው እንደ ዱሯቸው እንዲኖሩ ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ የአስተዳደር ለውጥ እንዲያደርጉ በተጽዕኖ ለማስገደድ ነበር፡፡ ልክ አሁን እንደ ሚታየው ብሔረሰቦች ለየብቻ በነገድ ቋንቋ ግድግድ አጥር ተከልለው፤ ዜጎች ነባርና “ደማዊ ያልሆነ ዜጋ” ወይም መጤ/ድቃላ ተባብለው በመፈራረጅ አሳዳጅና ተሳዳጅ ባይተዋር እንዲሆኑ የሚያደርግ፤ በጠላትነት የሚተያዩ ጎረቤታሞች አድርጎ የሚያጨራርስ ኢፍትሃዊ ሥርዓት ለመገንባት አልነበረም፡፡ የብሔር ትግል ፖለቲካው የኢትዮጵያ ሕዝብን በተለይም የአማራ ሕዝብንና ከአብራኩ የወጣውን ዋለልኝ መኮንንን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ዋለልኝ መኮንን መንታ ጫፍ ባለው ጦር ተወግቷል፤ ከሞተ በኋላ ከባድ ነቀፌታ ደርሶበታል፡፡ በአንዱ ጫፍ የኢትዮጵያ መነካት ልቡን በሚያቃጥለው አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ዛሬ አገሪቱ ያጋጠማት ችግር የእርሱ ጦስ ነው በማለት በደፈናው በፊት ለፊት ይወገዛል፡፡ በሌላው ጫፍ የአማራ ጭቁን ሕዝብን በገዥ መደብ ፈርጆ በሌላው ብሔረሰብ እንዲጠላ፤ በተራ የጓደኝነት ግንኙነት የኤርትራን የነጻነት ትግል የደገፈ ከአማራ ሕዝብ አብራክ የወጣው ዋለልኝ መኮንን ነው የሚል የረቀቀ መሰሪ ተንኮል ተፈጽሞበት ስሙ በአማራ ሕዝብ ጭምር እንዲተፋ ከጀርባ ተመትቷል፡፡ “ብልጥ በልቶ አፉን በሞኝ ይጠርጋል” ፤ እንደ ቫይረስ ጠምዝዘው ፈሩን ላሳቱት የብሔር ትግል ዓላማ ሕብረብሔራዊ ቅቡልነት ለመስጠት የዋለልኝ መኮንን ስም የመስዋዕት በግ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ምንም እንኳ ሁሉም ሰው አንድ ቀንደኛ ተማሪ ብቻ የብሔር ትግሉን እንዲህ አድርጎ ቀወጠው ይላል ባይባልም ኤርትራም የተገነጠለችው፤ አሰብም የተወሰደው፤ ሕዝቡ በቋንቋ ግድግድ አጥር ገብቶ የታጠረው ዋለልኝ መኮንን በ1965ዓ.ም ከተገደለ በርካታ ዓመታት በኋላ መሆኑ የሚጠፋው ሰው አለ አልልም፡፡ የብሔር ፖለቲካ ስኳር እየቃመ ዋለልኝ መኮንንን እያብጠለጠለ ቢውል ብዙ ስኳር ይጨመርለት ይሆናል እንጂ አገራችን ያጋጠማት ነቀርሳ ችግር አይቃለልም፡፡ የተሻለው መንገድ ከእነ ዋለልኝ መኮንን ሞት በኋላ ተዛብቶ ለጠባብ ቡድን ዓላማ ማሳኪያ የዋለውን የቀድሞው ተማሪ በሕብረት የጮኸለትን የመጀመሪያውን [Original] “የብሔር ትግል ጥያቄ” ወደ ትክክለኛ መስመሩ ማስገባት ሆኖ እያለ “የሞተ ጅብ ወጋሪ” እንዲሉ ዛሬ ላይ ቢደርስ አቋሙ ምን ሊሆን እንደሚችል የማይታወቅ በውስን ዕውቀትና መረጃ የታገለ የቀድሞ ተማሪ ላይ መረባረቡ ፈሪነትና ግዴለሽነት ነው፡፡ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ባይሆን ኖሮ ውጉዝ ከምአርዮስ መባል ያለባቸው ዘመኑን ያልዋጀ የብሔር ትግል አጀንዳ ላይ አሁንም ተቸንክረው የቀሩ ኪራይ ሰብሳቢ የብሔር ፖለቲካ አደሮች ነበሩ፡፡ ዕውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን አልታሰበበትም፤ ብዙም ሲነገርለት አይሰማም፡፡ የብሔር ፖለቲካው ሴራ ዋለልኝ መኮንንን በማስጠላት ብቻ አላቆመም፡፡ ሌሎች የአማራ ብሔረሰብ አንጋፋ ባለታሪክ ሰዎች ሁሉ ሰለባ ከመሆን አላመለጡም፡፡ የአማራ ወጣት ትውልድ በታሪኩ እንዳይኮራ፤ ከታሪክ የሚጠቀስ ሞዴል የሚሆን ሰው አጥቶ በተስፋ ቆራጭነት ሞራሉ እንዲነካ ለማድረግ የአማራ ሕዝብ ስመ ጥር አንጋፋዎችን ታሪክ በማጠልሸት የሌሎች ብሔረሰቦች ሕዝብ ጠላት አድርጎ በጭራቅነት ስሏል፡፡ እኔ በምኖርበት ወሎ፤ ደሴ ከተማ ላይ ተጀምሮ የነበረ የአገራችን ኢትዮጵያ አንዱ መሥራች የሆኑት የንጉሥ ሚካኤል ሐውልት ማቆሚያ ግንብ ሥራ በተንኮል እንዲቋረጥ ሲደረግ የተንታ ቀበሌ ነዋሪዎች ምስሉን በድብቅ ወስደው በትንሿ የገጠር ከተማቸው አደባባይ ላይ በግርማ ሞገስ ባይተክሉት ኖሮ ንጉሡ በመሰረቱት የራሳቸው ከተማ ላይ ምስላቸው ሙጃ ውጦት ቀርቶ ነበር፡፡ የዋለልኝ መኮንንን ሐውልት ደሴ ከተማ ለማቆም ቀደም ብሎ የመሰረት ድንጋይ እንዲቀመጥ ቢደረግም ሥራው ባለመጀመሩ በሐውልቱ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፡፡ በአንጻሩ በሌሎች ክልል ከተሞች በእነማን ስም አደባባይ ተሰየመ፤ ስታዲየም ተሠራ፤ ለእነማን ሐውልት ቆመላቸው ብለን ስንጠይቅ በአማራ ክልልም እንዲሁ እንጠይቅ፡፡ ባህርዳር ላይ የቆመው የሰማዕታት ሐውልት ተምሳሌት ምን ነበር?፤ የአማራነት ትምክህትን ይወክላሉ እየተባለ የእነማን ሐውልት ተነቀለ?፤ አማራን ከየትኛው ብሔረሰብ ጋር ለማጋጨት የቱ ክፉ ሐውልት ቆመ? እያልን እንጠይቅ፡፡ ትህነግ/ኢሕአዴግ ለወጣቱ ትውልድ ሞዴል የሚሆኑ ሰዎችን ከሕዝብ አዕምሮ እንዲፋቁ በማድረግ አልተወሰነችም፡፡ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፤ ቅርስና ቱባ ባህል ማክሰም አንዱ የትህነግ አጀንዳ ነበር፡፡ ከፍተኛ ዝና አትርፈው የነበሩትን ወሎ ላሊበላ፤ ግሼ አባይና ፋሲለደስ የኪነት ቡድኖች ወይም የባህል ማዕከላት የደርግ የጦርነት ማስፈጸሚያ ተቋማት ነበሩ በማለት ባለሞያዎቹን ከሥራ በማሰናበት ማዕከላቱን በመዝጋት የሕዝቡን ባህል ለማዳከም ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ቀረርቶና ሽለላ የአማራ ነፍጠኛ ባህል ነው በማለት ዘፈኖቹ የተቀረጹባቸው የቴፕ ካሴቶችና ማጫወቻ ሸክላዎች ከሙዚቃ ቤቶች መደርደሪያ ላይ እንዲጠፉ በማስገደድ ተወግዷል፡፡ የድፍን ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝብ ቱባ ባህል የሆነውን አሸንድየ የልጃገረዶች ጨዋታ በመሻማት የትግራይ ሕዝብ አንጡራ ቱባ ባህል ነው በማለት በስግብግብነት ለመቆጣጠር ተሞክሯል፡፡ የራስ ዳሽን ብሔራዊ ፓርክና የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል ቤተክርስቲያናት መገኛ ቦታ ትግራይ እንደሆነ የሚያሳይ ካርታ ተዘጋጅቶ በሥርዓተ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍትና በቱሪስት መስብ ማስታወቂያዎች ተሰራጭቷል፡፡ የክልሉን አስተዳደር በበላይነት በመቆጣጠር፤ ለትህነግ ተላላኪ የሆኑ ኃላፊዎችን በየደረጃው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሰግሰግ ተቆርቋሪነት፤ በቂ ልምድ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው የክልሉ ተወላጆችን በማግለል የክልሉ መስተዳድር የመንግሥት ሥራ እንዲስተጓጎልና በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሳ በከተሞች የሚገኙ የታሪክ ቅርሶችን እንደ ልጅ እያሱ ቤተመንግሥት፤ አይጠየፍ አዳራሽ፤ መርሆ ቤተመንግሥትና ወሎ ቤተመዘክር እንዲሁም በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መስብ የሆኑ የታሪክ ቅርሶች ለረዥም ጊዜ ታዛቢ አጥተው በዕድሳትና ጥገና እጦት እንዲጎዱና እንዲፈራርሱ ሆኗል፡፡ በክልሉ በሞግዚትነት በተመደቡ የአማራ ለምድ በለበሱ ቁልፍ የፖለቲካ መሪዎች በኩል በሚነገር “ብአዴን/ኢሕአዴግ የትህነግ እህት ድርጅት ነው” የሚል የማጭበርበሪያ ማሟከሻ የክልሉን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሁነኛ ባለቤት በማሳጣት ከፊል ወሎና ጎንደርን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ትግራይ ክልል በማካተት በተጠመደችበት የግዛት ማስፋፋት አባዜ ነዋሪዎቹ ለዘመናት ከገነቡት ጎንደሬነትና ወሎየነት ዘውግ ተነጥለው በትግሬነት ዘውግ ስር ያለፍላጎታቸው እንዲካተቱ በማድረግ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ተጥሷል፡፡ ወሎና ጎንደር እያንዳንዳቸው ለስድስት ትንንሽ አካባቢዎች መከፈላቸው ሳይበቃ ጎንደርን በአማራ-ቅማንት፤ ወሎን ደግሞ በኃይማኖት ሽብልቅ በመሰነጣጠቅ በጎንደሬነትና ወሎየነት የጋራ ማንነትና ሥነልቦና መክሰም ላይ የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ ምሥረታ የመሰረት ድንጋይ በተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡ በወሎየነት፤ ጎንደሬነት ወዘተ ገመድ ተሳስራ ለዘመናት የቆየች የጋራ የሆነች ኢትዮጵያ ተመስርታ እንደማታውቅ አስመስሎ ወጣቱን ትውልድ በክህደት በማታለል፤ ለጎንደሬነታቸው፤ ወሎየነታቸው ወዘተ የጋራ ማንነት ማበብ የሚቆረቆሩ በዕድሜ የገፉ ዜጎችን ደግሞ “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች” የሚል “ታግ” በመለጠፍ አሸማቆ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ ምሥረታ ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ በመሰሪነት ሰሜን ሸዋንና መተከልን ወደ አጎራባች ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በማጠቃለል የአማራ ክልልን ከአድስ አበባ በማራቅ “አድስ አበባ ኬኛ” ፤ “የኦሮሚያ ልዩ መብት” የሚል ፖለቲካ አቆጥቁጦ በአድስ አባባ ከተማ የይገባኛል ጥያቄ የኦሮሞ ልሂቃንን ከአማራና የተቀረው ብሔረሰብ ልሂቃን ጋር አፍ ሞልቶ ሊናገሩት ወደ ሚያሳፍር እሰጥ አገባ ውስጥ በማስገባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ የጥፋት ድግስ ተደገሰ፡፡ እንዲሁም ከነመሬቱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲቆይ የተደረገው የአማራ ሕዝብ መጤ ተብሎ ለክልሉ ባይተዋር ተደረገ፡፡ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ዜጎች እንደ ሌላ አገር ዜጎች ተቆጥረው በገዛ አገራቸው በሕይዎት የመኖርና ንብረት የማፍራት ዋስትና አጥተው አኬል ዳማ የሆኑት በዚሁ “አማራ ብሔርን ማህበረሰባዊ ዕረፍት ማሳጣት” በሚለው የትህነግ የብሔር ፖለቲካ መሳሪያ ነው፡፡ ከላይ በስፋት የተጠቀሰው ትህነግ/ኢሕዴግ በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው በደል የብሔር ፖለቲካ ምን ያህል አስከፊና የአገር ጠንቅ መሆኑን በአስረጂ ለማሳየት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አያት ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም መድረክ ቀና ብለን መሄድ የቻልን፤ ከቋንቋ ግድግድ አጥር የወጣን ነጻ ዜጎች የነበርን ብንሆንም ቆሞ-ቀር ጽንፈኛ ኪራይ ሰብሳቢ የነገድ ፖለቲከኞች ሕዝቡን በየግድግድ አጥር አስገብተው እንዲጨልምበት ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በማለት “ዐይናቸውን በጨው ታጥበው” ያንኑ የተቸነከረ የብሔር ፖለቲካ ከሩቅ እስከ ቅርብ ባለ ሰፊ ገበያ እየሸቀጡ ዘወትር ኪራይ ለመሰብሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር ይሻረካሉ፡፡ በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የብሔር ፖለቲካ ከዱር እንስሳት በሕይዎት የመኖር ስትራቴጂ አይሻልም፡፡ የአብዛኞቹ እንስሳት ሕይዎታዊ እንቅስቃሴ ግትር [Rigidly fixed] በሆነ ደመነፍሳዊ ባህርይ [Stereotype] የሚመራ በመሆኑ ከቆሞ-ቀሩ የብሔር ፖለቲከኞች የፖለቲካ ስትራቴጂ ጋር ምስለት አለው፡፡ የብሔር ፖለቲካ የቡድኑን “ደማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ ሕዝብ” በግብታዊነት በቀላሉ አነሳስቶ ለጠባብ ቡድን ዓላማ ማሳኪያ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ አድርጎ ማሠለፍ ያስችላል፡፡ ማን ደማዊ፤ ማን ደማዊ ያልሆነ ብሎ በማይታወቅበት አገር ኪራይ ሰብሳቢ የብሔር ፖለቲከኞች ሕዝቡን ርስበርስ አባልተው ጉዳት ሲያደርሱ ተዉ ባይ የላቸውም፡፡ በሰፊ የሐሳብ ልዕልና በነፃ ተወዳድረው በማሸነፍ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል አቅም ለሌላቸው የብሔር ፖለቲከኞች በፖለቲከኞች ጉልት ገበያ ተቀምጠው ዕድላቸውን ለመሞከር ያላቸው አማራጭ ይኸው ከዱሮ ጊዜ ጀምሮ የታዘሉበት የብሔረሰብ ቋንቋ ልዕልና አንቀልባ ነው፡፡ የሚያውቁት ይህንኑ ያህል ብቻ ነው፡፡ ቀን በጎደለ ጊዜም አንቀልባው «የቋንቋ ተናጋሪነት የፖለቲካ ጋሻ ወይም የመደበቂያ ዋሻ» ሆኖ ያገለግላቸዋል፡፡ አበው የብሔር ፖለቲከኞች ሌላ የፖለቲካ አማራጭ ሐሳብ ይዘው ወደ ፖለቲካ መድረክ ብቅ ከሚሉ ያንኑ የሚያውቁትን አሮጌ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ በጥርሳቸው ነክሰው በለስ ከቀናቸው ምኒልክ ቤተመንግሥት ጥልቅ ማለት ካልቀናቸውም ደግሞ በአንቀልባው ተጠቅልለው ወደ እንጦርጦስ መጣል ይቀልላቸዋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ የሚያገለግለው የጠባብ ቡድኑን ፍላጎት እንጂ እወክለዋለሁ የሚለውን ብሔረሰብ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ ጠባብ ቡድን በብሔረሰብ ጉያ ተወሽቆ ሕዝብን እያታለለና እያማለለ ዓለሙን እየቀጨ ቆይቶ የልቡ ሳይደርስ ሲቀር ወይም ሲጨላልምበት የራሴ ነው የሚለውን ብሔረሰብ ሕዝብ ጭምር በልቶ የሚሞት “ልዩ የውስጥ ጥገኛ ዘአካል” ነው፡፡ ከትህነግ ተግባር የታዘብነው ዕውነታ ይኸው ነው፡፡ ስለዚህ የብሔር ፖለቲካን እስካሁን ብዙ የተማርንበት ስለሆነ “ሰው መሆን” ፖለቲካ ማለትም የዜግነት ፖለቲካ አገራችንና ሕዝቧን የብልጽግና ጉዞ ያስጀምር እንደሆነ ብንሞክረው ይሻላል፡፡

ለማጠቃለል በሕዝብ ላይ የደረሰውን �

Report Page