*/

*/

Source

ከሌላው ዓለም ፍጡራን የተላከ ሊሆን ይችላል የተባለለት አዲስ የራዲዮ ሞገድ
========================= የሌላ ዓለም ፍጡራንን ፍለጋ ውስጥ በቀዳሚነት በሚቀመጠው ፕሮጀክት ስር የሚሰሩት ተመራማሪዎች ለፀሐይ በቅርብ ርቀት ከምትገኘውና ከምድር የ4.2 ብርሃን ዓመት ርቀት ካላት ፕሮክሲማ ሴንታዎሪ ኮከብ አቅጣጫ የመጡ የሚመስሉ አጠራጣሪ የሬዲዮ ሞገዶችን እየመረመሩ ናቸው፡፡ የሬዲዮ ሞገዶቹ አውስትራሊያ ውስጥ ባለው የፓርከስ ቴሌስኮፕ አማካኝነት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሲግናሉ ከተላከበት ጊዜ አንስቶ በተመራማሪዎቹ ትንተና እየተደረገበት ሲሆን ዝርዝሩ እስካሁን ለህዝብ ይፋ አልተደረገም፡፡ ተመራማሪዎቹ ምዕራብ ቨርጂኒያ ውስጥ ባለው ቴሌስኮፕ አማካኝነት መሰል የራዲዮ ዌቮችን መስማታቸው የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሞገዶች የሰው ልጆች ተፅዕንዖን ተከትለው የተገኙ ሲሆን ይህን ግን ለየት የሚያደርገው 980 ሜጋ ኸርዝ በሆነው የሬዲዮ ሞገዱ ባንዶች ውስጥ ሰው ሰራሽ የሆኑ ሳተላይትም ሆነ ቁስ ሲግናል አልተገኘበትም፡፡ ሲግናሉ በአውሮፓውያኑ 1977 ከተገኘውና “ዋው ሲግናል” ተብሎ ከሚታወቀው በኋላ በሌላው ዓለም ፍጡራን ፍለጋ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ሲግናል እንደሆነም በባለሙያዎች ዘንድ ተነግሮለታል፡፡ ሲግናሉን የመተንተኑን ስራ ስትመራ የቆየችው ሶፊያ ሼክ በፕሮጀክታቸው ውስጥ እስከዛሬ ከተሰሙት ሁሉ አጓጊው ሲግናል መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሲግናሉንም ብሬክስሩ ሊስን ካንዲዴት 1 (BLC1) ብለውታል፡፡ በሌላው ዓለም ፍጡራን ፍለጋ ውስጥ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ከእነዚህ ፍጡራን ጋራ የመገናኛው/መግባብያው መንገድ አለመታወቁ ነው፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርስ ውስጥ የሚፈጠሩ የሬዲዮ ሞገዶች ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉት ተፈጥሮአዊ መነሻዎችም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አይታወቁም፡፡ ስለዚህም ብዙውን እንደዚህ አይነት ሲግናሎች ሲገኙ ቴክኖሎጂ አፈራሽ እንደሆኑ ግምት የሚወሰድና ከተፈጥሮአዊ ምንጭ መሆናቸውን የሚያስረዳ ማብራርያንም በቀላሉ የማይገኝባቸው ሲሆን ነገሩን ወደ ሌላኛው ዓለም ፍጡራን መውሰዱ ግን ትኩረት ሳቢ ነው፡፡ ስለ ሲግናሉ የሚገልፅ መረጃ ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ወደፊት ይፋ ቢሆን እንኳን ልክ እንደ ዋው ሲግናል ሁሉ በማስረጃ የዋጀ ድምዳሜ ላይ የሚደረስበት አይመስልም፡፡ ከማንኛውም ኮከብ በላይ ለምድር በምትቀርበው ፕሮክሲማ ሴንታዎሪ ውስጥ ቢያንስ ሁለት የሚዞሯት ፕላኔቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንደኛው በጋዝ የተሞላ ሲሆን ሌላኛው ግን ባለው ለውሃ ፍሰት የተስማማ ሙቀት ሳብያ ሰውን ሊያኖሩ ይችላሉ ተብለው ግምት ከሚወሰድባቸው ፕላኔቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህች ፕላኔት ከምድር በ17 በመቶ የግዝፈት ብልጫ ያላት ድንጋያማ ስፍራ ናት፡፡ ፕሮክሲማ ቢ በሚል ስያሜ የምትታወቀው ፕላኔቷ በየ 11 ቀናቱ ኮከቧን የምትዞር ናት፡፡ ሆኖም ለሰው ልጆች ኑሮ አደገኛ ልትሆንም እንደምትችል ይነገራል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት የናሳ ተመራማሪዎች የኮምፒውተር ሞዴልን ተጠቅመው ፕላኔቷ በቀላሉ ለከባድ ጨረር እና ድንገተኛ የኮከብ ብርሃን ነበልባል የተጋለጠች ልትሆን እንደምትችል አሳይተዋል፡፡

ምንጭ፡ The Guardian እና Live Science

11 hours ago · Public · in

Report Page