*/

*/

Source

ጥላሁን ከተለየን እነሆ ፭ ዓመት ሆነ። እሱንም እንድናስበው በማለት ይቹን ጽፌላችኋለው አንብቧት። ጥላሁን ገሠሠ ጥላሁን ገሠሠ መስከረም 17 ቀን 1934 ዓ.ም ተወለደ፡፡ በ14 ዓመቱ አገር ፍቅር ተቀጠረ፡፡ በ1949 ዓ.ም ክብር ዘበኛ ሙዚቃና ቲያትር ክፍል ገባ፡፡ በ1976 ዓ.ም ደግሞ ብሔራዊ ቲያትር ተቀጠረ፡፡ ከ50 ዓመት በላይ በመድረክ ላይ በሙዚቃ ህዝቡን አዝናንቷል፡፡ 40 ብር ለክቡር ዘበኛ ገንዘብ ቤት አንደኛ መምሪያ ሬዲዩ ጣቢያ አገልግሎት ጉዳዩ፡- ሰለሰራተኛ መቀጠር፡- አቶ ጥላሁን ገሠሠ የተባሉት ግለስብ ከመጋቢት 25 ቀን 1949 ዓ.ም ጅምሮ በወር 40 ብር ደመወዝ ተቀጥረዋልና ከዚህ ቀን አንስቶ ስማቸው በአንደኛው መምሪያ ደመወዝ መክፈያ መዝገብ ላይ ተሞልቶ ሲቀርብልዎ በየወሩ ወጪ እየሆነ እንዲከፈላቸው ይሁን፡፡ ግንቦት 13 ቀን 1949 ዓ.ም፡፡ ጥሬ ቆሎ ለክ/ዘበኛ አንደኛ መምሪያ ሬዲዩ ጣቢያ አገልግሎት ጉዳዩ፡- የደመወዝ ቅጣትን ይመለከታል አቶ ጥላሁን ገሠሠ የተባለው የክፍሉ ሠራተኛ ጥሬ ቆሎ አምጥቶ የሙዚቃ ስራ በሚሰራበት ቀን እየጎረደመና እያስጎረደመ ለሠራተኛውም እያደለ ሥራ በማስፈታት ከአንድ ወር ደመወዙ ላይ 3 ብር እንዲቆረጥበት ይሁን

ሐምሌ 9 ቀን 1949 ዓ.ም

ቁርስ ዘፈኑ ነው ጥላሁንና ፍሬው ሀይሉ በልጅነታቸው ሀገር ፍቅር ተገናኙ፣ የቤት ልጆች ይባላሉ፡፡ ምክንያቱም ህጻናቶች ሰለሆኑ ከዚያ አካባቢ ሰለማይወጡ ነው ፍሬው እንደዚህ ይላል:: “ሁለታችንም ልጆች ነን ዘፈንን እንወዳለን፡፡ ‹እኔ መዝፈን የምጀምረው ከምሳ በኋላ ነው፡፡ ጥላሁን ግን ከጥዋት ይጀምራል፡፡ ቁርሱን ሳይበላ ማንጎራጎር ይጀምርና እስከማታ አይላቀቅም፡፡ አንድ ቀን ቁርስ ላይ ሲዘፍን አለቃችን መጀመሪያ ምግብ ብላ አሉት ለእኔ ምግቤ ዘፈን ነው አላቸው፡፡ ምግብማ ሞልቷል› የሚለውን ዘፈን ሲጫወት የድሮውን (የቁርሱን) ነገር ያስታውሰኛል” ይላል፡፡ ተንኮለኛው መኪና በ1948 ዓ.ም የአገር ፍቅር ዘፋኞች ሬዲዮ ጣቢያ ሰርተው ምሽት ላይ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በወቅቱ ሬዲዮ ጣቢያ ቅጂ ስለሌለው በቀጥታ ስርጭት ነበር የሚያጫውተው፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ የሀገር ፍቅር ሙዚቀኞችን የምትሽኝ ቮልስ መኪና አለች ሰሟም ከበቡሽ ይባላል ችግር ስላለባት ሁል ጊዜ ትገፋለች መግፋት የሰለቸው ጥላሁን “እኔ ቤቴ እዚህ ነው መኪናዋ ተንኮለኛ ነች፡፡ መሄድ አትፈልግም እሷን ብንገፋት ትነሳለች ከገፋናት ሁሌም ግፉኝ ትላለች” ብሎ ጥሏት ሄደ፡፡ ጥላሁን ከመጣ ጦር …. በ1969 ዓ.ም በሱማሌ ጦርነት ወታደሩ በውጊያ ተዳክሞ ነበር፣ ጦሩ እንደገና አንሰራርቶ ለመዋጋት ምን መደረግ አለበት በሚል አለቆች ውይይት ተቀመጡ፣ ከመሣሪያ ድጋፍ አንስቶ ካድሬዎቹ ጦሩን የሚያነቃቃ ሐሳብና ድጋፍ አቀረቡ በሌላ ቀንም ይሄው ጉዳይ ተነሳ ግን ብዙም አጥጋቢ ውጤት አልተገኘም፣ አንድ ሰው እንደዚህ የሚል ሀሳብ አቀረበ “ጥላሁን ገሠሠ ቢመጣ ይሄ ጦር እንደሚያንሰራራ ነው” የሚል ነበር፡፡ ጥላሁንም ተጠርቶ መጣ፣ ዘፈነ፡፡ ጦሩ ሞራሉ ተነሳሳ፣ እያቅራራ ወደውጊያው ገባ በጦርነቱም ድል ተገኘ፡፡ ያሁሉ የወታደር ካድሬ በሞራልና በቅስቀሳ ያስቸገረውን ጥላሁን በቀረርቶ አስታጥቆ ላከቸው፡፡ አንድ ጉዳተኛ ወታደር ሲናገር “ጥላሁን ውሰጣችን ገባ እኛም በሞራል ሄድን እንዳንመለስ እንዳንዳከም አድርጎ ነው የላከን” ብሏል፡፡ በስፖርት ዓለም በ1950ዎቹ መጀመሪያ የክቡር ዘበኛ የክፍል የስፖርት ውድድር በየሳምንቱ ረዕቡ እለት ይካሄዳል፡፡ እያንዳንዱ ሰራተኛ በሚችለውና በተመዘገበበት ስፖርት ይወዳደራል፡፡ ቀሪው ደግሞ በማስ ስፖርት ይሳተፋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠም ለክፍሉ ለእግርና ለመረብ ኳስ ተሳትፏል፡፡ በ1970 ዓ.ም የእናት አገር ጥሪ በአል ሙዚቀኛና ጋዜጠኞች ባደረጉት ጨዋታ ጥላሁን ይሠለፋል ተብሎ ሲጠበቅ በአሠልጣኝነት ነው የታየው፡፡ ታኬት አድርጎ ቁጭ ብሏል፡፡ ታኬታውን የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነው ጌታቸው አበበ (ዱላ) ነው፡፡ ጌታቸውና ጥላሁን ጥሩ ጓደኛማማቾች ናቸው፡፡ጥላሁን ጌታቸውን ሲያፈለልግ ቆየ፡፡ ጌታቸው፡- ለምን ፈለግከኝ ጥላሁን፡- የኳስ ጫማ እንድትሰጠኝ ብዬ ነው ጌታቸው፡- የኳስ ጫማ እያደረግህ መዝፈን ጀመርክ እንዴ ጥላሁን፡- አዎን ጌታቸው፡- ታዲያ የትኛው ይሻልሃል) ጥላሁን፡- የኳስ ጫማ ደግሞ ምን ልዩነት አለው የምታሰመርጠኝ? ጌታቸው፡- የብሎንና የላስቲክ አለ ጥላሁን፡- ለእኔ የሚስማማው የትኛው ነው፡፡ ጌታቸው፡- ለአንተ ሳይሆን ለአየሩ ሁኔታ ነው ጥላሁን፡- አልገባኝም ጌታቸው፡- ዝናብ ከሆነ ብሎኑን ደረቅ ከሆነ ደግሞ ላስቲኩን ነው፡፡ አንዱን ጫማ ጌታቸው ለጥላሁን ይዞለት ሄደ፡፡ ጌታቸው እንዲህ ይላል “የጨዋታ ቀን ጥላሁን አልተሰለፈም፡ ለምን አልገባህም? ስለው ‹‹ለጓደኞቼ ጫማውን ያመጣሁት ከጌታቸው ዱላ ነው ስላቸው የሱ ጫማ ከሆነ ረብሻ ስለሚያሰነሳ አትሰለፍም አሉኝ” ብሎ ነገረኝ በማለት ዱላ ተናግሯል፡፡ ጌታቸው ዱላ በጨዋታ ላይ ረብሻ በማስነሳት የታወቀ ነው፡ ሻይና ዳቦ ሻምበል መኮንን መርሻ ፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ለረጅም አመት በሙዚቃ ክፍል ውስጥ ሰርቷል፡፡ ትራንፔት ተጫዋችና ድምጻዊም ነበሩ፡፡ በመንፈቅለ መንግስቱ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ ነበሩ፡፡ እሳቸው የክቡር ዘበኛ ሙዚቀኞችን እንደ እሰረኛ ይጠብቁ ነበር፡፡ ‹‹ጥላሁን ታስሮ መጣ እኔ ጥበቃ ነበርኩኝ፡፡ ኮረኔል ረታ ደመቀ ከእሰረኞች መሃል አውጥተው ለብቻው አስቀመጡት፡፡ እኔ ሄድኩና በኦሮምኛ አዋራሁት፡፡ ከዚያም ተግባባን፡፡ እስረኛ ቢሆንም በእኔ ሀላፊነት ወደውጪ ይዤው ወጣሁ ፡፡አንድ ቦታ ወሰድኩት ፡፡አባ ጃሌ ሰፈር ይባላል፡፡ ሻይና ዳቦ ገዛሁለት፡ ከዚያ አካባቢ የሚሸጥ ነገር ያለው ይሄ ነው ፡፡ጥላሁን በጣም የማደንቀው ዘፋኝ ቢሆንም እርሱ እሰረኛ እኔ ጠባቂ መሆኔ ለጊዜው ባይመቸኝም በምችለው ሁሉ ተንክባክቤዋለሁ፡፡ በሌላ ጊዜ ስንገናኝ አባ ጃሌ ደህና ናቸው!! ይለኛል ያ ቦታ እስካሁን ድረስ አልረሳውም›› በማለት ይናገራሉ ያም ሲያማ ከተማ ውስጥ ሐሜት በዝቷል፡፡ በተለይ ይሄ ሁኔታ የሚለፋውን የሚሰራውን ሰው አስቸግሮታል፡፡ በሐሜት ከሚቦጨቁት ውስጥ አንዱ ጥላሁን ነበር፡፡ ሐሜትን ለመምታት የውስጥ አንጀትን የሚያርስ ዘፈን አልተገኘም ነበር፡፡ አቶ ተስፋዬ አበበ ይናገራሉ ‹‹በሐሜት ዙሪያ ብዙ ተወራ ይሄን ለመስበር አንድ ስራ ማዘጋጀት ነበረብኝ፡፡ ከስራ ባልደረባዬ ከኮረኔል አያሌው ጋር ተነጋገርን እኔም ግጥሙን አዘጋጀሁ ፡፡አያሌው ዜማውን ሰራው ፡፡ይሄን ማን ቢጫወት ይሻላል ብዬ ሳስብ ጥላሁን በደንብ እንደሚሰራው ገመትኩ ለእርሱም ሰጠሁት›› ይላሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ የፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ይሄን ግጥም ለፖሊስ ዘፋኞች መስጠት ትተው ክቡር ዘበኛ ሄደው ለጥላሁን እንዴት ሰጡት) የሚለውን ሲመልሱ ‹‹የጥላሁን ጠንካራ ጎኑ ጥሩ ስራን ካገኘ ይጫወታል፡፡ እኔም እሱን ፈለኩት እሱም ጥሩ ተጫወተ፡፡ ወሬኛን ለመምታት ዝም ለማሰኘትም ያ ስራ ጥሩ ሚና ተጫውቷል፡፡ አሰፋን አላስገደልኩም

አሰፋ አባተ በሀገር ፍቅር ታዋቂ ዘፋኝ ነበር ፡፡በአሰፋ ሞት የጥላሁን እጅ አለበት ተብሎ ሲወራ ቆይቷል፡፡ በ1993 ዓ.ም. አድማጮች ጥላሁንን በሬድዮ ይጠይቁት ነበር፡፡ አንድ አድማጭ ‹አሰፋ አባተን አስገድለኸዋል ይኼ ነገር እንዴት ነበር)› ብሎ ጠይቆት ነበር ፡፡ጥላሁንም ሲመልስ ‹‹በመሰረቱ እኔ አሰፋ አባተን አላስገደልኩም፡፡ አሰፋ አባተ የሞተው ሀገር ፍቅር እያለ ነው፡፡ እኔ ያለሁት ደግሞ ክቡር ዘበኛ ውስጥ ነው፡፡ ከየት መጥቶ ነው ከነገሩ ጋር የሚገናኘው)›› በሚል መልስ ሰጥቷል፡፡

ልቀቁን እንገባለን
አሰፋ አባተ ድንገት ስለሞተ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡ ብዙ ተወራ፡፡ በመድሀኒት ገደሉት ተባለ፡፡ አሰፋ የተቀበረው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በቀብሩ ዕለት የተፈጠረው ሁኔታ የሀገር ፍቅር ባልደረባ አቶ ግርማ እንዲህ ይላሉ ‹‹ጥላሁንና ፍሬው አሰፋ አባተ እንደልጆቹ ነው የሚቆጥራቸው፡፡ በሙዚቃ ያሳደጋቸውም እሱ ነው፡፡ ጥላሁን አሰፋን አስገደለ የሚለው ነገር የተሳሳተ ወሬ ነው፡፡ አሰፋ ሲሞት ጥላሁን በቦታውም አልነበረም፡፡ እኔ የሀገር ፍቅር ውስጥ ስለምሰራ ሁሉንም ነገር አውቀዋለሁ፣ በእርግጥ አሰፋ አባተ በድንገት ነው የሞተው፣ አቶ እዩኤል ዮሐንስና በሻህ ተክለማርያም ‹ይኼ ነገር ሀሜትን ይፈጥራል› በሚል እሬሳውን ሆስፒታል ወስደው አስመረመሩት፡፡ አሰፋ የሞተው አንጀቱ በመታጠፉና በመቀደዱ ነው፡፡ የሚገርመው እሬሳው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደርሶ ሊቀበር ሲል ለፖሊስ ተደውሎ ነው ወደ ሆስፒታል ሄዶ የተመረመረው፡፡ ሌላው በጣም የሚያስቅ ነገር ያየሁት ጉድጓዱ ተቆፍሮ የአሰፋ ሬሣ ሊገባ ሲል ፍሬውና ጥላሁን ‹ከሱ በፊት› እኛ ጉድጓድ ካልገባን› እያሉ አስቸገሩ እዚያው የሚሰራ ለገሰ በላቸው የተባለ አርቲስት እሬሳው ከመግባቱ በፊት አንድ ጊዜ አቆዩት› በማለት ህዝቡን ዝም አሰኝቶ ጥላሁንና ፍሬውን ‹በሉ አሁን ኑ ግቡ› አላቸው ሁለቱም ወደኋላ አፈገፈጉና አሰፋ ተቀበረ›› በማለት ይናገራሉ፡፡ የአሰፋን ሞት በተመለከተ ሌላው አስገራሚ ነገር ለቀስተኞች እሬሳውን ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ በወቅቱ ሬድዮ የሚተላለፍባቸው ድምጽ ማጉያዎች ጊዮርጊስ (ፒያሳ) አካባቢ ተተክለው ነበር፡፡ ጌታቸው ደስታ በሬድዮ ሙዚቃ የሚያቀርብ ሙያተኛ ነው(በኋላም ዶቼ ቬላ ሰርቷል)፡፡ ከአሰፋ ጋር ይቀራረባሉ፡፡ አሰፋ መሞቱን ግን አያውቅም፡፡ ለቀስተኛው እሬሳውን ይዞ ሲሄድ አዲስ የወጣውን የአሰፋ ሙዚቃን ለቅቆ ለቀስተኛው የአሰፋን እሬሳ ተሸክሞ እያለቀሰ በአንድ በኩል በድምጽ ማጉያ የሚለቀቀውን የአሰፋን ዘፈን እየሰማ ነበር ወደ ቀብር የሄደው፡፡

ቆዳ ሲጠቡ አየሁ የጥላሁን እምባ በሙዚቃ ውስጥ የታየውና ሌላውንም ያስለቀሰው በ1966 ዓ.ም. ነው፡፡ የወሎ ድርቅ ጊዜ በቴሌቪዥን ያዩት ስለ ወሎ ድርቅ ማሰብና መጠየቅ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ ‹ድርቁ ይህን ያህል ነው ጥላሁን እንዲህ እምባ አውጥቶ ያለቀሰው በትንሽ ነገር እምባ ስለሚቀድመው ነው ያሉም ነበሩ፡፡ ጥላሁን ስለሁኔታው ሲናገር ‹‹በወቅቱ ቦታው ድረስ ሄጄ ድርቁን በአይኔ ስለአየሁ ስሜቴም ስለተነካ አልቅሼ ለመስራት ተገድጃለሁ፡፡ አንዲት እናት ግራና ቀኝ 2 ልጆች ታቅፋ እሷ ግን ሞታለች፡፡ ሰውነቷ ደርቆ ልጆቹ የእሬሳዋን ቆዳ ሲጠቡ አይቻለሁ፡፡ ሸዋ ሮቢት መሐል መንገድ ላይ ሁለት አመት የማይሞላቸው ልጆች አንጀታቸውን እያከኩ ሲሞቱ ተመልክቻለሁ፡፡ ይሄን ተመልክቼ ሙዚቃውን ስሰራ ያ ትዝ እያለኝ አልቅሻለሁ፡፡ ያንን አይቼ ስቄ ለመስራት ህሊናዬ አይፈቅድልኝም፡፡››ብሎ ነበር የሽጉጥ ገንዘብ ጥላሁን በ1966 ዓ.ም. ወደ ደሴ ሄደ፡፡ ጓደኛው ከዚያ ሲመለስ መሣሪያ ገዝቶ እንዲመጣ ላከው፡፡ ያን ጊዜ የለውጥ እንቅስቃሴ ስለተጀመረ ራስን ለመጠበቅ ታስቦ ይሆናልና መሣሪያ አስፈላጊ ነበር፡፡ መሣሪያ እንዲገዛ የተላከው ጥላሁን ባዶ እጁን ተመልሶ ገንዘቡንም አጥፍቶታል፡፡ ለመሆኑ ብሩን ምን አደረገው? እንዲህ ያስታውሳል ‹‹ጓደኛዬ ከኤሊዳር ሽጉጥ ገዝተህ እንድትመጣ ብሎ 800 ብር ሰጠኝ ወደ ወሎ እንደሄድኩ ህዝቡ ረግፏል፡፡ ሸዋ ሮቢት ስደርስ የሰውን ሁኔታ ሳይ አላስቻለኝም፡፡ አውቶቡስ እያስገደደን እያስቆምን ህዘቡን መርዳት ጀመርን ያንን ብር መነዘርኩና ኮንቦልቻ ስደርስ ጨረስኩት የአደራ ገንዘብ ቢሆንም ብሩን ይዤ ዝም ማለት አልቻልኩም፣ ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ የላከኝ ሰው ሽጉጡን አመጣህ ወይ ሲለኝ ገንዘቡ መጥፋቱን ነገርኩት በቴሌቪዥን ማየትም እንዳለበት አስረዳሁት፡፡ ዘፈኑ ቲቪ ከመታየቱ አንድ ቀን በፊት ጋዜጠኛ ዲንቢልቢ በመጽሔትና በጋዜጣ ጉዳዩን አዳረሰው፡፡ የኔም ዘፈን በቲቪ ታየ ፡፡ባለሽጉጡም መጥቶ ‹ምን ጉድ አመጣህብን› ብሎ ጠየቀኝ ‹ይሄውልህ ለነኚህ ነው ገንዘቡን የሰጠሁት› አልኩት፡፡ ዘፈኑ እስኪያልቅ ድረስ እሱ ያለቅስ ነገር፡፡ ‹ለጥሩ ነገር ነው ያዋልከው ብሎ መረቀኝ›› በማለት ይናገራል፡፡ ዜማ ፍለጋ ዋ! ዋይ-ዋይ ሲሉ የተባለውን ዘፈን ለመጠንሰስ ብዙ የአእምሮ ጨመቃ አስፈልጓል፡፡ ይሄ ዘፈን ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡ ረሃብና ሞትን የያዘ በመሆኑ ይሄን ሁኔታ ላላየው የኢትዮጵያ ህዝብ በማስረዳት በምን መልኩ ለህዝብ ይቅረብ ስለተባለ ሙዚቃው ጥሩ ገላጭ እንዲሆን አዘጋጆቹን አስጨንቋል፡፡ ጥላሁን እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከወሎ ስንመለስ እኔ ተዘራና ኮነሬል ሳህሌ መኪና ውስጥ ሆነን በማንዶሊን እየተጫወትን ዜማ ይፈለግ ነበር፡፡ ሰዎቹን ስላየን ግጥም ለመስራት አስቸጋሪ አልነበረም ፡፡ዘፈኑ ከብዙ ዜማ ፍለጋ በኋላ ተሰርቶ አለቀ ለቲቪ ሰጥተን በነጋታው ስራው እኛኑ የባሰ አስለቀሰን›› ይላል፡ የኛ ጀግኖች

በ1949 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የሀገር ፍቅር ትያትር ሙዚቃ አባላት ወደ አስመራ ሄደው ነበር፡፡ ጥላሁን ገና ታዳጊ ህፃን ነበር፡፡ ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጉዟል፡፡ አሰለፈች አሸኔ የቡድኑ አባል ነበረች ስለሁኔታው እንዲህ አለች ‹‹አስመራ ሄደን ለሲቪልና ለወታደር ስራችንን አሳየን፡፡ እዚያ የእኛ መስሪያ ቤት ቅርንጫፍ ነበር፡፡ እነሱ ተቀብለውን ሀገሩን እያዞሩ ያሳዩናል፡፡ በሄድንበትም ስራችንን እናቀርባለን፡፡ አቆርዳት ደርሰን ወደ አስመራ ተመለሰን፡፡ ተሰነይ አካባቢ ያሉ ሰዎች እኛን እንዴት አልፈው ይሄዳሉ ብለው አኮረፉ፡፡ ለእነሱ ለማሳየት ስንል ተመለስን፡፡ መሐል ላይ ስንደርስ ሽፍቶች አገኙንና አስቆሙን፡፡ ሴቶቹ ለብቻ በአንድ መኪና ወንዶቹ ደግሞ በሌላ መኪና ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ሽፍቶቹ ጥላሁንን ከመኪና አወረዱትና ‹ይሄ ህፃን እዚህ መኪና ውስጥ ምን ይሰራል› ብለው በጥፊ ይመቱትና ሴቶቹ መኪና ውስጥ አስገቡት፡፡ ስለመቱት በፍራቻ ተንቀጠቀጠ፡፡ እነ እዮኤል ዮሐንስ ለገሰ በላቸውና ሌሎችም መሳሪያ ይዘዋል፡፡ ሽፍቶቹ ትጥቁን አስፈቷቸው፡፡ አስመራ ከገባን በኋላ ጥላሁን ‹የእኛ ጀግኖች አለ በሰዎቹ ላይ እያሽሟጠጠ ‹እኔ እንኳን በጥፊ ተመትቼ ከሴቶቹ ጋር የተቀላቀልኩት እሻላለሁ እናንተ ግን መሳሪያ አስረክባችሁ ተወገራችሁ፡፡አሁን ምንም ወንድነት የለም› እያለ ለብዙ ወራት ሰዎቹን እያየ ይስቅ ነበር፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ክቡር ዘበኛ ሄደ›› ብላለች፡፡

የኮዳው መዘዝ ‹እንጠጣ ነበር ውሃ በአንድ ኮዳ- በጣም ሳዝናል ያመኑት ሲከዳ› የሚለው የጥላሁን ዘፈን ብዙ ውዝግብ አስነስቷል፡፡ ጥላሁን የክቡር ዘበኛ ዘፋኝ ነው፡፡ ክ/ዘ የመራውን መፈንቅለ መንግስት ጦር ሠራዊት ነው ያከሸፈው፡፡ ጦርሰራዊት መፈንቅለ መንግስቱን ለማድረግ ተስማምቶ ‹ከድቷል› ስለተባለ የጥላሁን ‹ያመኑት ሲከዳ› የሚባለው ዘፈን እነሱን ለመጎንተል የተደረገ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ የክ/ዘ የሙዚቃ አባል አቡበከር አሸጌ ‹‹ጦር ሰራዊት ይሄንን ዘፈን ለምን አትተውትም ይሉን ነበር፡፡ ጥላሁንንም ይጎነቱሉታል፡፡ በመንግስት ሰዎችም እያስወቀሰን መጣ ፡፡ጥላሁን በተለያ ቦታ ሄንን ዘፈን መጫወት ጀመረ ፡፡ዘፈኑን የሚጫወተው በሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ ይሄንን ካልተጫወተ ሰዎች አያስቀምጡትም፡፡ አንድ ቀን ሲቪል የለበሰ የጦር ሰራዊት አባል ጥላሁንን ካልተማታሁ አለ፡፡ ለመገላገል የገቡ ሰውውን ደበደቡትና ትልቅ የሆነ ረብሻ ተነሳ›› ይላሉ፡፡ ኮዳ ተያዘ እንጠጣ ነበር ውሃ በአንድ ኮዳ የተባለው ዘፈን ሳንሱር ላይ ጭቅጭቅ ፈጥሮ ነበር፡፡ ኮነሬል ተስፋ አበበ እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹እንጠጣ ነበር ውሃ በአንድ ኮዳ በጣም ያሳዝናል ያመኑት ሲከዳ›› በማለት የተጫወተው ነበር፡፡ ሳንሱር አድራጊው ራሱ በግጥሙ ተደስቶ ጥሩ ነው በሚል ምንም የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለበት አረጋግጦ ይለፍ አሉ፡፡ ልምምድ ላም ታይቶ ጥሩ ነው በሚል የሳንሱር ሰዎች አረጋገጡና ዘፈኑን አፀደቁት፡፡ የኛ ኮሚቴ ሙዚቃውን የሚቀርበው ጳጉሜ 5 ማለትም ለዘመን መለወጫ ዋዜማ እንዲሁም የእነቁጣጣሽ ቀን መስከረም 1 እና ለመስቀል ቀን ነው፡፡ የጥላሁንም ዘፈን ሳንሱር ካለፈ በኋላ የመጀመሪያው ጳጉሜ 5 ቀረበ መስከረም 1 ቀን ወዲያውኑ የሳንሱር ሰዎች መጡና ከለከሉ፡፡ በጣም ነው በዚህ ዘፈን ያዋከቡን፡፡ ምክንያቱም የተዘፈነው በክቡር ዘበኛ ባንድ ነው፡፡ የክቡር ዘበኛን ሙዚቃ ያቋቋመ፣ትና ለትልቅ ደረጃ ያደረሱት ጄነራል መንግስቱ ነዋይ ናቸው፡፤ መፈንቅለ መንግስቱን ክቡር ዘበና ሲካሄድ ጦ ሰራዊት አፈንግጧል ስለተባሉ መጀመሪያ አብረው ጠንስሰው ያኛው አፈንግጧል በሚል ‹በጣም ያሳዝናል ያመኑት ሲከዳ› የሚለው ዘፈን የተዘፈነው ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር በተያያዘ ጦር ሠራዊት ለመንካትና የመንግስቱ ንዋይ ስራዎችን ከፍ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ በሚል የእንቁጣጣሽ ቀን እንዳቀርብ ታገደ›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ጉድጓድ ገባ ጥላሁን በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑ ለዘመን መለወጫ በዓል አንድ ሌት ለ ዝግጅት ተደረገ ሐሳቡን ከመነጩት አንዱ ኮነሬል ተስፋ አበበ ነበሩ፡፡ ‹‹ዝግጅቱ የሚቃርበው ብሐየራዊ ትትር ነው ፊት ለፊት ስቼጁ ማብቂያ ላይ ጉድጓድ አለ፡፡ አሁን ተደፍኗል፡፡ ያንን ቦታ በተመሳሳይ ጨርቅ ተሸፍኖ ጨርቁ ለብሷል፡፡ ጥላሁን ድምጹ ሳይቋረጥ የሚዘፍንበት ቦታ አለ፡፡ በዚህ ደግሞ ህዝቡን የመሳብ ተሰጥኦ አለው፡፡ ጥላሁን መድረክ ላይ እየተጫወተ ሊያልቅ አካባቢ የሸሚዙን ቁልፍ እየፈታ ቦጫጭቆ ቀደደው ህዝቡ ሁሉ በዘፈኑ አክሽን ረማርኮ ያጨበጭብ ነበር፡፡ እየዘፈነ ድምጹን ሳይቆርጥ በሁለት እግሩ ጉድጓድ ውስጥ ገባ፡፡ ልክ ጉድጓድ ውስጥ ሲገባ መብራት ጠፋ ህዝቡ ጥላሁን ሞተ ብሎ እሪ ማለት ጀመረ መጀመሪ ጉድጓድ ውስጥ ፍራሽ እንዲነጠፍ ተደርጓል፡፡ ለዚያም ልምምድ ሰርቷል፡፡ መብራት ሲበራ ህዝቡ አዳራሹን አናወጠው ካላየነው አንሄድም አሉ፡፡ ጥላሁም ወደ መድረኩ መጥቶ እጅ ነሳ፡፡ ህዝቡ ለጥላሁን ያለውን ፍቅር ያወቅነው ያኔ ነው ዘፈኑን መልሱልኝ

ሲራክ ታደሰ በቲያትርና በግጥም ይታወቃል፡፡ ‹ትንፋሼ ተቀድቶ-ይቀመጥ ማልቀሻሽ..... የሚለውን ግጥም ለጥላሁን ሰጠው በኋላ ግን ነገሩ አሳሰበው፡፡ ‹‹ግጥሙን ከሰጠሁት በኋላ ይሄ ሰውዬ ዘፍኖ አንድ ነገር ቢሆን ሟርተኛ ቢሉኝስ ብዬ ለጥላሁን ያንን ግጥም መልስልኝ አልኩት፡፡ እሱ ግን ጥሩ ግጥም ነው በጣም ተስማምቶኛል ብሎ ዘፈነው፡፡ ከ30 ዓመት በኋላ ሳስበው የተናገርኩት ነገር እራሴን አስገርሞኛል›› ብሏል፡፡

Report Page